| ልንፈታው የማንችለው... |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
ልንፈታው የማንችለው ችግር አላጋጠመንም!በአሁኑ ጊዜ በየቤታችን፣ በየቢሯችን በየካፌውና በየመዝናኛው የምናወራቸው ችግሮች አሉ፡፡ የነዳጅ ዋጋ መናር፣ የምግብ እህል ዋጋ መናር፣ የዕቃዎች ዋጋ ውድነት፣ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችና መሣሪያዎች ዋጋ ንረት፣ የወርቅ መጭበርበር፣ የአበባ ሽያጭ ወደ አገር ተመልሶ አለመግባት፣ የሙስና መስፋፋት፣ በቢሮክራሲው መልካም መስተዳድር መጥፋት ወዘተ. ወዘተ. ወደ ውጭ ወጣ ካልን ደግሞ የሶማሊያ ችግር፣ የኤርትራ መንግሥት፣ አደገኛ ቦዘኔነት ወዘተ. ወዘተ. ፍላጎትና ወኔ ካላጠረን በስተቀር እነዚህ ችግሮች አንዳቸውም ቢሆኑ ልንፈታቸው የማንችል ችግሮች አይደሉም፡፡ ልንፈታው የማንችል አላጋጠመንም፡፡ በርበሬ፣ ጨው፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ ሙዝ፣ ወዘተ. የምግብ ምርቶች በብዛት እንዲገኙና ዋጋቸው እንዲቀንስ ማድረግ እውነት ይሳነናል ወይ? ፖሊሲያችንን ፈትሸን ማስተካከያ ፖሊሲ ካወጣንና ተግባር ላይ እንዲውል ከጣርን ለሁሉም የሚበቃ ምርት ማምረትና ሕብረተሰቡ ሊሸከመው በሚችለው ዋጋ መሸመት እንችላለን፡፡ አንዱ መንገድ ከአነስተኛ የአርሶ አደሩ እርሻ ጎን ለጎን ትላልቅ ኮሜሪሺያል እርሻ ማስፋፋት ማጠናከር ነው፡፡ መንግሥት እንደዚሁ ዓይነት ሰፋፊ መካናይዝድ እርሻ እንዲስፋፋ ማድረግ የሚሳነው ነገር የለም፡፡ አርሶ አደሩ በምርቱ ተጠቃሚ መሆን አለበት፡፡ ማድረግም አለብን፡፡ ሕብረተሰቡ ሊሸከመው የማይችለው ዋጋ በመጠየቅ ግን አርሶ አደሩም ተጠቃሚ መሆን አይችልም፡፡ ይህን ግምት ውስጥ ያስገባና ያጣጣመ አሰራርና ፖሊሲ በመያዝ አርሶ አደሩም ሸማች፣ ሕዝቡንም ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡ ፖሊሲን የማስተካከል፣ አሰሪውን የማውጣት አወቃቀርና ባለሙያን የማዘጋጀት ጉዳይ ነው፡፡ ይቻላል፡፡ ከውጭ የሚመጣ ነዳጅ ርካሽ እንዲሆን ማድረግ አልቻልንም፡፡ የራሳችን ነዳጅ ይኑረን ብለንም እንዲኖረን ማድረግ አንችልም፡፡ ነገር ግን የነዳጅ ዋጋ ንረትን ለመቋቋም የሚችል የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ይቻላል፡፡ የአፍሪካ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች የዓለም ቦታዎችም የነዳጅ ዋጋ በኢትዮጵያ ከሚቀርበው የበለጠና የናረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዓይነቱን የነዳጅ ድጎማ የማይሰጡ በርካታ አገሮች አሉ፡፡ አይሰጥ ማለታችን አይደለም፡፡ ይሰጥ.. ለድጋሚ ለሚወጣው ወጪ የሚሸፍን ግን ኢኮኖሚን መገንባት ይቻላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማጠር አንድ ችግራችን ነው፡፡ ሕገ ወጥ የውጭ ገንዘብ ምንዛሪም አሉታዊ ድርሻ እየተጫወተ ነው፡፡ ፖሊሲን በማስተካከል ግን ልንቋቋመው የምንችልበት እድል አለ፡፡ ዶላር የሚመነዝሩ ሕጋዊ ሱቆችና ድርጅቶች ለምን አይፈቀድም? በግልፅ ዶላር እንመነዝራለን ብለው ሕጋዊ ፈቃድ ይዘው፣ ግብር የሚከፍሉ “ፈሬክስ ቢሮ” ለምን አይፈቀድም፡፡ መንግሥትም አገርም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ የሚጎዳ ወገን የለም፡፡ ዲያስፖራ ያለው ኢትዮጵያዊ፣ በኢትዮጵያ ባንክ ማስቀመጥ የሚችለው እስከ አምሳ ሺ ዶላር ብቻ ነው የሚል ሕግ አለን፡፡ የውጭ ምንዛሬ በእጅጉ የሚያስፈልገን ከሆነ እንደፈለጋቸው አምጥተው ቢያስቀመጡ ምን ችግር አለበት? በሕንድ አገር የውጭ ምንዛሬ ያስገኘ ዲያስፖራ፣ ለየት ያለ ማበረታቻና ወለድ ሲታሰብለት እኛ ከአምሳ ሺ ዶላር በላይ ወደ አገር አስገብተው ማስቀመጥ አይቻሉም፡፡ ለምን ይባላል፡፡ ይህም ይስተካከል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ለኤክስፖርተሮች ጥብቅ ትዕዛዝና የተንዛዛ መመሪያዎች እያወጣ ነው፡፡ ከልማት ባንክ በኩል በውሉ መሠረት ገንዘብ ይመልስ ብሏል፡፡ ይህ ቀደም ብሎ መደረገ የነበረበት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቶች ፖሊሲዎች ሊቀጥሉና ሊበዙ ይገባል፡፡ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችና መሣሪያዎች በእጅጉ ተወዷል፡፡ ንሯል.. በብዛትና በተመጣጣኝና አሳማኝ ዋጋ ለማስመጣትም ነጋዴውም ፍርሃት፣ ፍርሃት እያለው ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሃብት የኮንስትራክሽን መሣሪያ ማምጣት ከከበደው የውጭ ባለሃብት እንዲያመጡ ይፈቀድ፡፡ የውጭ ሰው ማስመጣት አይችልም፡፡ ወደ ሃገር ማስገባት የሚቻለው ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው እየተባለ ለምን የኮንስትራክሽን ዘርፉ እንዳያድግ ይደረጋል? የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ይህን በሚመለከት እየጀማመረው ያለው አዳዲስ ፖሊሲ የሚደገፍ ነው፡፡ የመብራት ችግር አለ፣ ኤሌክትሪክ በፈረቃ ሆነ እያልን ብንጨነቅ፣ ብንጠበብ በርግጥ ችግር አለ፡፡ ግን ጊዜያዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ወደ ውጭ ኤክስፖርት የማድረግ አቅም አላት፡፡ ለዚሁም እየተዘጋጀች ነው፡፡ የአሁኑ ፈረቃ ይህን ሃቅ አይቀበለውም፡፡ መደረግ ያለበት ጊዚያዊ ችግሩ የረዥም ጊዜ ችግር እንዳይሆን መቀላጠፍ ነው፡፡ መሯሯጥ ነው፡፡ የፍትሕ ችግር፣ የሙስና ችግር ፣ ቆራጥ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ሰርቆና ዘርፎ ሊያመልጥ የሚችል ሰው እንዳይኖር መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ግልፅ መልዕክት ሊያስተላልፉ ይገባል፡፡ መንግሥት ራሱን ሊያክም የሚችል የራስ መዋቅርና የሰው ሃይል ፈትሾ ያፅዳ፡፡ የዚህ ፅሑፍ አላማ ችግሮችን መዘርዘርና ለያንዳንዱ ችግር መድሃኒት ማዘዝ አይደለም፡፡ ብንፈልግም አንችለውም፡፡ ነገር ግን ልንፈታው የማንችለው ችግር እንደማይኖር ለመጠቆም ነው፡፡፡፡ በአሁኑ ጊዜ የበርበሬ፣ የጨው፣ የብረት፣ የሲሚንቶ፣ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የዶላርና የነዳጅ ችግር ቢያነጋግርም መንገድ እየተሰራ ነው፡፡ መሰረተ ልማት እየተስፋፋ ነው፡፡ ልማት ላይ ነን፡፡ ለቅሶ አልተቀመጥንም፣ ሀዘን አልጠበቀንም፡፡ ፖሊሲዎች እንከተላለን፣ ተገቢ ተቋሞች እየገነባን፣ ሥራና ሰራተኛ እያገናኘን ተጠያቂነትን እያጠናከርን፣ የአመራር ብቃትን እያጎለበትን ከሄድን ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይሆን ተአምርም መስራት እንችላለን፣ ኢትዮጵያን እናኮራታለን!! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |