|
Sunday, 13 April 2008 |
|
የዚምባቡዌ መንግሥትና ተቃዋሚዎች ድርድር ሊያካሂዱ ነው
በቅርቡ ዚምባቡዌ በተካሄደው ምርጫ ዙሪያ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት መንግሥትና ተቃዋሚዎች ድርድር ለማካሄድ መዘጋጀታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫውን ማሸነፋቸውን ሲገልፁ የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ አስተዳደር በበኩሉ የድምፅ ቆጠራው ዳግም እንዲካሄድ አሳስቧል፡፡ በዚህም የፕሬዚዳንቱ አመራር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ለሁለተኛ ዙር እንዲካሄድ አሳስቧል፡፡
ያለፈው ሀሙስ በደቡብ አፍሪካ ጀሀንስበርግ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የምርጫው ውጤት ሳይገለፅ እንዲዘገይ መደረጉ ፍትሀዊ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሙቭመንት ኦፍ ዴሞክራቲክ ቼንጅ ፓርቲ ቃል አቀባይ ቴንዲያ ቤቲ "ምርጫውን አሸንፈናል፡፡ ስለዚህ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ማካሄ አያስፈልግም" ብለዋል፡፡
"""""///"""""
የኡጋንዳ አማፅያን የሰላም ስምምነቱን አለመቀበላቸውን ገለፁ
የኡጋንዳ አማፅያን ከመንግሥት ጋር የጀመሩትን የሰላም ስምምነት እንደማይቀበሉ ማስታወቃቸውን የኦሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ አመለከተ፡፡
በዘገባው መሰረት የሎርድ ረዚስታንስ አርሚ መሪዎች ቁልፍ ያሏቸውን ቅድመ ሁኔታዎች መንግሥት ካላሟላ የሰላም ስምምነቱን እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ያለፈው ሀሙስ በደቡብ ሱዳን በመንግሥትና በተቃዋሚዎች ይካሄዳል ተብሎ የተጠበቀው የሰላም ስምምነት ተስተጓጉሏል፡፡
በኡጋንዳ ከሀያ አመታት በላይ በመንግሥትና በአማፅያን መካከል በተካሄደ ጦርነት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወቃል፡፡
"""""///"""""
ፕሬዚዳንት ቡሽ በኢራቅ ላይ በያዙት አቋም ተተቹ
ፕሬዚዳንት ቡሽ በኢራቅ የያዙት አቋም "ግትር" ነው ሲሉ የአሜሪካ ፖለቲከኞች መተቸታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የተወዳዳሪዎች ትችት የተሰነዘረው ፕሬዚዳንት ቡሽ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ የሚያደርጉትን ቆይታ በተመለከተ ከሰኔ በፊት ለውይይት እንደማይቀርብ ከገለፁ በኋላ ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ የሚያደርጉትን ቆይታ የፕሬዚዳንትነቱን ስልጣን እስኪለቁ ድረስ ላለመወሰን የሚያደርጉት ጥረት መሆኑ ተገል"ል፡፡
የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች ሂላሪ ክሊንተንና ባራክ ኦባማ የፕሬዚዳንቱ አቋም ግትር መሆኑን በመጥቀስ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ ከእጩ ተወዳዳሪዎች በተጨማሪ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ "ፕሬዚዳንት ቡሽ የአሜሪካውያን ቁልፍ ጥያቄ የሆነውን የኢራቅን ጉዳይ ለመመለስ አልደፈሩም" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
"""""///""""
የተመድ ዋና ፀሐፊ የቤጂንግ ኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ አይገኙም
የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪሙን በቻይና ቤጂንግ በሚካሄደው የኦሎምፒክ መክፈቻ በአል ላይ እንደማይገኙ የድርጅቱን ቃል አቀባይ በመጥቀስ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
በዜና አገልግሎቱ ዘገባ መሰረት ዋና ፀሐፊው በኦሎምፒክ መክፈቻ በዓል ላይ አይገኙም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ማሪ ሙካቢ ዋና ፀሐፊ በሌላ ፕሮግራም ምክንያት በመክፈቻ በዓሉ ላይ እንደማይገኙ ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ኬንያዊቷ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዋ ዋንጋሪ ማታይ በቲቤት ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም በታንዛንያ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ችቦ አቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ እንደማይገኙ ተዘግቧል፡፡
ዘገባው የኦሎምፒክ ውድድሩ የፖለቲካዊ ገፅታ እየያዘ መሆኑን አመልክቷል፡፡ አንዳንድ የአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለሙያዎች የኦሎምፒክ ውድድር ከፖለቲካ ነፃ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ "የቤጂንግ ኦሎምፒክ የፖለቲካ እሰጥ አገባ መድረክ ሆኗል" ሲሉ ተችተዋል፡፡ |