| ራስ ሳይጠና ጉተና |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
|
የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ውጭ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆንዋን ያሳወቀች አገር ኢትዮጵያ! በቅርብ ዓመታት ውስጥ እስከደቡብ አፍሪካ ድረስ ሊደርስ የሚችል ኃይል ማመንጨት የምትችል መሆንዋ የተነገረላት ኢትዮጵያ! ያላት የውሃ ሃብት ለራስዋ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ብርሃን በብርሃን ሊያደርግ የሚችል የሃይድሮ ፓወር ማመንጫ ግድቦችን ለመስራት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠብቃት መሆንዋን በአደባባይ የገለፀች አገር! በበልግ ዝናብ እጥረት ሳቢያ ለራስዋ የሚሆን የኃይል ምንጭ ማግኘት አልቻለችም ከሚያስፈልጋት ኃይል 8ዐ ሜጋ ዋት ጐደለባት ሲባል ለእኛ ሳይሆን ወደፊት የእኛን የኤሌክትሪክ ኃይል ይሸምታሉ የተባሉ አገራት ምን ሊሉ እንደሚችሉ እግዜር ይወቀው፡፡ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትና በማሰራጨት የሚታወቀው ብቸኛው የአገሪቱ መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች የኃይል እጥረት መኖሩን እያወቁና ኃይሉን በፈረቃና በኮታ እያከፋፈሉ ስለመሆናቸው ያሳወቁን ቆይተው፤ ያውም ከየአቅጣጫው ግፊት ስለበዛባቸው መሆኑ በራሱ ትልቅ ስለመሆኑ ኃላፊዎቹ ራሳቸው ያምኑበታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ያላት የውሃ ሃብት ምሥራቅ አፍሪካን አልፎ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ሊዘልቅ የሚችል የኤሌክትሪክ ኃይል ልታመነጭ ያስችላታል እየተባለ በሚነገርበትና ለዚህም ተግባራዊነት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን በሰማንበት ጆሯችን ለራስዋ የሚሆን የኤሌክትሪክ ኃይል አጠራት ሲባል መሸማቀቃች ባይቀርም ችግሩ ነገም ተነገ ወዲያም እንዳይደገም መመኘታችን ግን እንዳለ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ስለገጠመን እንደድርሻችን ለመከፋፈል የፈረቃ ስርዓት ተዘርግቶልናል፡፡ መሆን የማይገባው ቢሆንም ተቀብለነዋል፡፡ ከመንግሥት ድርጅቶች በገቢ መጠኑ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም ከኃይል እጥረት ጋር በተያያዘ የገጠመውን ችግር ለማቃለል አለመቻሉ በራሱ ኮርፖሬሽኑ ላይ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ የኃይል እጥረቱ ደንበኞቹን አገልግሎት ተቀባዩን ሸማቹን በጥቅሉ ሁሉንም እንደፈለገው እንዳይሸምትና እንዳይገለገልም እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይሉ በፈረቃ መሆኑን በይፋ ከመነገሩ በፊት ለሳምንታት ኃይል በፈረቃ ሲደርሰን እንደበርና በዚህም ምክንያት ሥራ ሲስተጓጐል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት የሚቋረጥ መሆኑን ነግሮን ኃይሉን የሚለቅልን ከ2፡30 በኋላ ነው፡፡ ይህም ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ ድርጊት ምንም አይደለም ብለን ብንቀበላቸውም እየፈጠረ ችግር ግን ባርካታ ነው፡፡ ጀኔሬተር የሌላቸው ዳቦ መጋገሪያዎች በበቂ ሁኔታ ዳቦ ማምረት ባመቻላቸው ሸማቾች እየተቸገሩ ነው፡፡ ፋብሪካዎች ምርት ለመቀነስ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሸማቹ በፈለገው መጠን የሚፈልገውን ምርት አያገኝም፡፡ ፋብሪካዎቹ ጀኔሬተር ይጠቀማሉ ቢባል እንኳን ጄኔሬተሩ የሚፈጀው ነዳጅ የማምረቻ ዋጋውን ስለሚጨምር ፋብሪካዎቹ የዋጋ ጭማሪ ቢያደርጉ ይህንን እዳ እንዲሸከም የሚደረገው ሸማቹ ይሆናል፡፡ ጄነሬተር የሌላቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ደንበኞቻቸውን በስርዓቱ ማስተናገድ አልቻሉም፡፡ ችግሩ እስከመቼ እንደሚቆይ አይታወቅም፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይሉ መቋረጥ ሸማቾች አገልግሎት ሰጪና ተቀባዩ ላይ ከሚያሳድረው ተፅእኖ አልፎ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፈው ተፅእኖም ቀላል አይደለም፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጣራ በጨመረበት በዚህ ወቅት ለጄኔሬተሮች የሚወጣው የነዳጅ ወጪ ለሌላ አገልግሎት ማዋል ይችል ነበር፡፡ ጀኔሬተሩም ሆነ ነዳጁ የሚገዛው በውጭ ምንዛሪ በመሆኑ የችግሩን ስፋት እንድንመለከት ያደርገናል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ራሱ ከኃይል እጥረቱ ጋር በተያያዘ ለሚጠቀምባቸው ጄኔረተሮች በወር 100 ሚሊዮን ብር ያህል እያወጣሁ ነው ማለቱ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረቱ እያስከተለ ያለው ችግር ግምት ውስጥ ገብቶ ለመጪው ጊዜ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ከወዲሁ መታሰብ ይኖርበታል፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |