Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow በሊዝ የሚከራዩ ድርጅቶች ይመርመሩ
በሊዝ የሚከራዩ ድርጅቶች ይመርመሩ Print E-mail
Sunday, 13 April 2008
ፍላጎት መሽሻ 
 
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ከሚያዛውርበት መንገድ አንዱ በሊዝ ለተወሰነ ዓመት ማከራየት ነው፡፡ ሊዝ የሚደረገው ድርጅት ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት፣ በባንክ ያለውና በእጅ የሚገኘው ገንዘብ፣ ጥሬ ዕቃ፣ ተመርቶ የተቀመጠና በሂደት ላይ የሚገኝና ሠራተኛውን ከእነመብቱና ግዴታው በአገሪቷ ሕግና ደንብ እንዲሁም የኅብረት ስምምነቱን በማክበር ለማስተዳደር በውል ተገብቶ ነው፡፡

 

ይሁን እንጂ በሊዝ የሚገቡ ባለሃብቶች ምንም ኢንቨስት ሳያደርጉ ባዶ እጃቸውን በኢንቨስተር ስም በጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት እየተሽሞነሞኑ ገብተው የሀገር ሃብትን የሚዘርፉበት፣ ለአገራቸው ዜጋ በብዙ ሺህ ብር ሥራ የሚያስገኙበት የአገሬውን ዜጋ ምስጢራቸውን ካወቀ ፀረ ኢንቨስተር ነው በማለት ሥራ የሚያሳጡበት የሚቀጡበት የሚያስቀጡበት፣ ለጥቂት ባንዳዎች በየጊዜው የደመወዝ ጭማሪ ዕድገትና ሹመት የሚሰጡበትና ተጠያቂነት የሌለበት ነው፡፡

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ በአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር ላይ ተካሂዶ ያለፈውና አሁን እየተካሄደ ያለው አሠራር የአገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚጐዳ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅት ማለት የጥቂቶች መበልፀጊያ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ፣ ግማሹ የሞተ ገሚሱ ለመሞት የተቃረበ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ያልሰጠ አሁንም ደግሞ እነዚህ ቀድሞ የገደሉ በእጅ አዙር በኘራይቬታይዜሽን ሰበብ በሚመጡ በውጭ አገርና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጉያ ተሸጉጠው የሚመዘብሩበት የሚበለጽጉበት ከመሆን ያለፈ አልሆነም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለውጥ አለ የሚል መዝሙር ካልሆነ በስተቀር እውነቱ የተገላቢጦሽ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር በአንድ ወቅት በሊዝ በቱርካዊ ዜጋ ሚ/ር አቲላ ይልድሪም ተይዞ ነበር፡፡ ቱርካዊው የሊዝ ጊዜውን ሳይጨርስ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ባጋጠመው የገንዘብ እጥረትና በወቅቱ በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ውሉ ተቋርጦ በ1994 ዓ.ም. ሹልክ ብሎ ወጥቷል፡፡ ከወጣ በኋላም በስሙ ያልተከፈለ የሊዝ ኪራይ፣ ያልተከፈለ የሠራተኛና ማህበራዊ ዋስትና ገንዘብ፣ የሥራ ግብር፣ ያልተከፈለ የኤሌክትሪክና የውሃ ዋጋ፣ በባንክ የነበረውንና በድርጅቱ ካዝና የነበረውን ገንዘብ፣ የተጠቀመበት የጥሬ ዕቃና ያለቀለት ምርት እና ሌሎች ያልተከፈሉ ዕዳዎች በጠቅላላ ተደምረው ወደ 20.3 ሚሊዮን የሚደርስ ገንዘብ መባከኑ ተሰምቷል፡፡ ተከራዩ ገንዘቡን ተመላሽ ለማድረግ በሕግ ለመጠየቅ የሚገኝበት ትክክለኛ አድራሻ በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ባለመታወቁ የተነሳ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡

በጋዜጣ ጥሪ ተደርጐለትም አልቀረበም፡፡ በፍርድ ቤት የክስ ሂደቱ እየታየ ሳለ (በሌለበት) እንደገና በግልግል ዳኝነት እንዲታይ ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ በቀረበው ሃሳብ መሠረት ጉዳዩ ታይቶ ከነወጪውና ከነወለዱ ተደምሮ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ለአክሲዮን ማኅበሩ ተወስኖ ነበር፡፡ እስከዛሬ ድረስ ገንዘቡ ተዘርፎ ጠያቂና ተጠያቂ በሌለበት እንዲቀር ተደርጓል፡፡

የአዋሳ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር እንደ ዕድል ሆኖ ለሚ/ር ሀበቨ ናሪን ቱርካዊ ዜግነት ላላቸው በ1998 ዓ.ም. በድጋሚ በሊዝ ተሰጠ፡፡ እኚህ ተከራይ ገና ከመከራየቱ በፊት ባቀረበው ቢዝነስ ኘላኑ ላይ ተሰብሳቢ ገንዘብ የቀድሞ የሊዝ አክሲዮን ማኅበሩ የሂሳብ መዝገብ በማይሰበሰብ ሂሳብ ሥም እንዲሰረዝ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ይህ ገንዘብ ባክኖ መቅረት የለበትም ብለው ተከራዩ ከመምጣቱ በፊት ጀምሮ የሚጠይቁ ሠራተኞችና ማኔጅመንቱ ከሥራ እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡ ይህን ገንዘብ የሥራ አመራር ቦርዱ እንዲከታተለው አልተደረገም፡፡ የውሳኔ ሃሳብ በተከራዩና በማኔጅመንታቸው እጅ ሆኖ ለመንግሥት ተጠሪ ለሆነው ቦርድ አልቀረበም፡፡ ይህን ምስጢር የሚያውቁ የቦርድ አባላት ባልታወቀ ሁኔታ በሌላ ይተካሉ፡፡ ያሉትም ቢሆኑ እንዲያሰባስቡ ለማድረግ በማኔጅሜንታቸው አማካይነት ሪፖርት በጊዜ ስለማቅረብ የተለያየ መሰናክል ይፈጠራል፡፡ ተከራዩም ሆነ ማኔጅመንታቸው ስለ ቦርድ ኃላፊነትና ተግባር የገባቸው አይደሉም፡፡ አልፈው ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡

እኝህ ተከራይ (ሁለተኛው) በሊዝ አክሲዮን ማኅበሩን ሲረከቡ ከአይ.ዲ.ኤፍ 8 ሚሊዮን ብር ለሥራ ማስኬጃ በብድር ከአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ በኋላ በሦስት ዓመት ክፍያ እንዲጨርሱ ነበር፡፡ እስካሁን ግን ክፍያው አልተጀመረም፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን የሚሉት የአክሲዮን ማኅበሩን የባንክ ዕዳ (የቆየ) ከፍያለሁና በዚያ ይታሰብ ዓይነት ነወ፡፡ ይህ የባንክ ዕዳ የተከፈለው ዕድሜ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኤክስፖርት የሚገባውን ገንዘብ እየጠበቀ ከአካውንታችን እየቆረጠ ከተከራዩ ፍላጐት ውጪ በመውሰድ ለአክሲዮን ማኅበሩ በማዋሉ ነው፡፡ ከተጠቀሰው ገንዘብ ውጪ ሌላ ስምንት ሚሊዮን ብር ለመለዋወጫ ግዥ የማይመለስ ግን በአግባቡ ለተባለው ዓላማ መዋሉ ሲረጋገጥ ማለትም የቆሙ የማምረቻ መሣሪያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት (ለማንቀሳቀስ) በመጨረሻም በሚቀርበው ግዥ ሰነድ እና ኤል ሲ የተከፈተበትን ሲያቀርብ የሚወራረድ ተብሎ የተሰጠ ቢሆንም ተገዝቶ የገባው ዕቃ የጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ ግዢውም የግዥ ደንብና ሕግ ተከትሎ የተፈጸመ ሳይሆን ከአገራቸው ብቻ ደረጃውን ያልጠበቀ መለዋወጫ በማስገባት ነው፡፡ የገባው መለዋወጫም ቢሆን ቆሞ የነበረውን ማምረቻ መሣሪያ ለማንቀሳቀስ መዋል አለመዋሉን ማረጋገጥ የሚችል የለም፡፡ ከመለዋወጫ ግዢው ጥራት ችግር ጋርና በትክክል ለተባለው ዓላማ መዋል አለበት ከሚል ጥያቄ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች ተባረዋል፣ ታግደዋል፣ አስገዳጅ የዓመት ፈቃድ እንዲወጡ ተደርገዋል ወይም ተንሳፈዋል፡፡ በሌላ በኩል የዓላማው ደጋፊ ሠራተኞች ዕድገት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቀለል ባለ ቦታ ተመድበው እንዲሠሩ ተደርገዋል፡፡ ከውጭም ከአክሲዮን ማኅበሩ ኅብረት ስምምነት ውጭ ተቀጥረዋል፡፡ ተገዝቶ በሚገባው መለዋወጫ ዙሪያ በጥራት ችግር ላይ የሠራተኛ ማኅበሩ ለተከራዩ በግልፅ ደብዳቤ በመጻፍና በአካል በመገናኘት አናግሯቸዋል፡፡ ሠራተኛ ማኅበሩም ለዳይሬክተሮች ቦርድ ይህንን አሳውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እኝህ ተከራይ በጥቂቱ ታማኝ ያልሆኑት የአክሲዮን ማኅበሩ ማለፊያ ፕሮጀክት በሚል የ600 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ቀርፀው አቅርበዋል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ እየተሠራ ያለው ሥራ በውሉ መሠረት ባልሆነበት እንዴት ይህን ያክል ገንዘብ እንሰጣለን በሚለው ሀሳብ ላይ እየተነጋገረ ከበላይ አካል አጽድቃችሁ ላኩ የሚል ደብዳቤ በየጊዜው እየጻፈ ነው፡፡ ተከራዩ ከሁለት ዓመት በላይ ቆይታ ባደረገበት ጊዜ ለአክሲዮን ማኅበሩ የፋይናንሻል ስቴትመንት አቅርቦ አያውቅም፡፡ ወርሃዊ፣ የሩብ ዓመትና ዓመታዊ አፈጻጸም ሪፖርት ወቅቱን ጠብቆ አይቀርብም፡፡ ቢቀርብ እንኳን የፋይናንስ ሕግና ደንብን ባልተከተለ መልኩ የእዳና ተቀናሽ ሂሳብ ሳያካትት ይሠራል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያመርታል፣ ይሸጣል ግን የአክሲዮን ማኅበሩ አካውንት ባዶ ነው፡፡ ገንዘቡ የት እንደሚገባ አይታወቅም፡፡ ወደ አዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ምርት ስለሚሄድ በአዋሳ ገንዘቡ ይገኛል እንዳይባል የአዋሳው ራሱ ከፍተኛ በሆነ የገንዘብ ችግር ውስጥ ነው፡፡ ወደ ውጭ የሚላከው የጨርቅ መጠን አሁን በጣም ቀንሷል፣ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የኤክስፖርት ገንዘብ የግድ በባንክ አካውንት ስለሚገባ ተከራዩ ላልፈለገው ዓላማ ይውላልና ሊዙ ውሉን ስቷል፡፡ ግለሰቦች የፈለጉትን የሚያደርጉበት፣ የፈለጉትን የሚቀጥሩበት ያልፈለጉትን ከሕግ ውጭ ከሥራ የሚያፈናቅሉበት የሚቀጡበት ሆኗል፡፡

ሊዝ በፕራይቬታይዜሽን ስም ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት ከውጪ ዜጐች ጋር ተመሳጥረው የሚበለጽጉበት ሆኗል፡፡ በዚህ ማንም ትኩረት ባልሰጠው መንገድ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሲሸጡና ሲከራዩ ለጥቂቶች የግል መጠቀሚያ፣ ለብዙሃኑ ሠራተኛ ግን በተለያየ መንገድ ሥራውን የሚጠላበት፣ የሚሰቃይበት ሆነዋል፡፡ ስለዚህ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሊዝ በተሰጡ ድርጅቶች ዙሪያ እየተሠራ ያለውን ሙስና ትኩረት ሰጥቶት የአገርን ሀብትና ወገንን ከጥቃት መታደግ አለበት፡፡

 
< Prev   Next >