|
Sunday, 13 April 2008 |
 በቀድሞው አጠራር ፈላሾች፣ በአሁኑ ቤተ እሥራኤሎች ተብለው የሚታወቁት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ በብዛትና አንድነት ሠፍረው የሚኖሩባቸው ዋና ዋና አካባቢዎች የሚገኙት በሰሜን ክፍላተ አገር ውስጥ ነው፡፡ የቤተ እሥራኤል መንደሮች የሚገኙት ተራርቀውና ከሌሎች ወገኖች መንደሮች ጋር ተሰባጥረውና ተበታትነው ነው፡፡ መምህር አስረስ ያየህ "ቤተ እሥራኤል በኢትዮጵያ ታሪካቸው፣ ባህላቸውና አኗኗራቸው" በተሰኘው ድርሳናቸው እንደገለጹት ቤተ እሥራኤሎች የተሰማሩባቸው ሙያዎች የብረታ ብረት፣ የሽመና፣ የሸክላ፣ የአናጢነትና የግምበኝነት ሥራዎች ናቸው፡፡
ለአንድ ቤተ እሥራኤል ዋና መቆሚያ መሠረቱ ቤተሰብ ነው፡፡ ቤተሰብ፣ በተለያየ የእርከን ክልል ውስጥ ለሚገኘው ለእያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል ሕይወት መገኛው ስለሆነ እንደ እምብርት ይቆጠራል፡፡
ለአንድ ቤተ እሥራኤላዊ ቤተሰብ ከደስታ ምንጮቹ አንዱ እንግዳ መቀበልና ማስተናገድ ነው፡፡ እንግዳ፣ "የአብርሃም እንግዳ" ነው የሚባለው፡፡ እንግዳ ሲመጣ በምግብና መጠጥ በኩል በቤቱ ከሚገኘው ከሁሉም የተሻለው ተመርጦ እንግዳው ፊት ይቀርባል፡፡
በቤተ እሥራኤል የጋብቻ ዓላማ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ዓላማ ዘር ለማፍራት፣ ወገን ለማብዛት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከልጅነት ዕድሜ የጀመረና እያደገ የሚሄድ በሁለቱ መካከል መተሳሰብና መደጋገፍ እንዲፈጠር ለማድረግ ነው፡፡ ይኽም ለሚወለዱ ልጆች በፍቅርና በሥርዓት ማደግ የተስማማ ቤት እንዲኖር ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል፡፡
እንደ መምህር አስረስ ጥናታዊ ጽሑፍ በቤተ እሥራኤል የወንድ ልጅ ልደትና የሴት ልጅ ልደት ሥርዓት የተለያየ ነው፡፡ ወንድ ልጅ ሲወለድ በቦታው ያሉ ሴቶች ዐሥራ ሁለት ጊዜ እልልልል በማለት ደስታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከስምንት ቀናት በኋላ በኦሪት ሕግ መሰረት እዚያው እመርገም ጎጆ ውስጥ ሆኖ ይረገዛል፡፡ በአካባቢው በሚሰራ ምላጭ ሕፃኑን የምትገርዘው ሴት ስትሆን፣ በወቅቱ ነጭ ወይም ቀይ ዶሮ ይታረዳል፡፡ ልዩ ጸሎትና ቡራኬም ይደረጋል፡፡
ወላጅ እናት፣ በተለይም የድሃ ሚስት ከሆነች በመርገም ጎጆው ውስጥ አርባ ቀናት ትቆያለች፡፡ የሀብታም ሚስት ከሆነች ግን ሰው እንዳያስቸግራት (ብቻዋን ለመሆን እንድትችል) ግሊሊት ጎጆ ተብሎ ወደሚጠራ ሌላ ጎጆ ትዛወራለች፡፡
በመርገም ጎጆ ውስጥ ስምንት ቀናት ትቆይና የተቀሩትን ሠላሳ ሁለት ቀናት ከሰው ተገልላ የምትኖረው በግሊሊት ጎጆ ውስጥ ይሆናል፡፡ ሁለቱም ጎጆዎች የሚሰሩት ከዋናው ቤት አቅራቢያ ነው፡፡
ሴት ልጅ ስትወለድ በሥፍራው ሴቶች ዘጠኝ ጊዜ እልልልልል በማለት ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በቤተ እሥራኤላውያን ዘንድ ሴቶችም እንደ ወንዶቹ ልጆች ይገረዛሉ፡፡ ሴት ስትወለድ እመጫቷ በመርገም ጎጆ ውስጥ የምትቆየው ለ80 ቀናት ነው፡፡ እናቲቱ የሃብታም ሰው ሚስት ከሆነች በመርገም ጎጆው ውስጥ 14 ቀናት ቆይታ ለተቀሩት 66 ቀናት ወደ ግሊሊት ጎጆ ተዛውራ ትቀመጣለች፡፡
ተገልላ የምትቆይበትን ወቅት ስትፈጽም የመንጻት ሥነ ሥርዓት ስታጠናቅቅ ወንድ ልጅ የወለደች ወንዝ ውስጥ አርባ ጊዜ መጥለም ሲኖርባት፣ ሴት ልጅ የተገለለችው እመጫት ግን ሰማንያ ጊዜ ትጠልማለች፡፡ የተቀረው የልደት ሥነ ሥርዓት ለወንድም ሆነ ለሴት ልደት አንድ አይነት ነው፡፡ እንደተለመደው መጠነኛ ድግስ ይደገሳል፡፡ አንድ ካህንና ሌሎች እንግዶችም ይጋበዛሉ፡፡ ሴትየዋ እግሮቿንና እጆቿን ዘርግታ መሬት ላይ በልቧ ትተኛለች፡፡ ካህኑ ለበጦቹን ተቀብለው ከእግሯ እስከ ራሷ ያለውን ሰውነቱን ቀስ ብለው ይመቷትና ለበጦቹን ውጭ አውጥተው ወደ ፀሐይ መውጫ አቅጣጫ ይበትኗቸዋል፡፡
በቤተ እሥራኤል በጎጆ ምሥረታ፣ በሠርግ ጊዜ ሙሽሪት ክብረ ንጽሕናዋን ጠብቃ ድንግል ሆነ ከተገኘች ከሚዜዎቹ ሁለቱ ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ መጥተው ደስታውን ያበሥራሉ፡፡ ይህንን የሚያበሥሩት የድንግልናዋ ምልክት የሆነውን ደም የተነከረውን ጨርቅ በገሐድ በማሳየት ነው፡፡ ከዳሱ የሞላው ሰው ሁሉ ይባርካታል፤ ይመርቃታል፡፡ አባትና እናቷን ታመሰግናለች፡፡ ከእርሷ ጋር የመጡት ዘመዶቿም ይፈነድቃሉ፤ ይፎክራሉ፤ እንዲህ እያሉም ይዘፍናሉ፡፡
"አታፍር አታሳፍር የተቀጣች የተቆነጠጠች ጥሩ እንደ ብርሌ ልቅም እንደ ስንዴ፡፡" በሔኖክ ያሬድ |