Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ የሱፍና...
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ የሱፍና... Print E-mail
Wednesday, 09 January 2008

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ የሱፍና የሶማሊላንድ ተገንጣይ መሪ በአንድ አውሮኘላን ተጓዙ

የሶማሊያ ሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አብዱላሂ የሱፍ አህመድና ከሶማሊያ በመገንጠል ሂደት ላይ ያለችው የሶማሊላንድ መሪ ዳሂር ሪያል ካሂን ባለፈው ቅዳሜ ወደ ለንደን ባደረጉት ጉዞ በአንድ አውሮኘላን ውስጥ መጓዛቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ዋቢ በማድረግ ጋረወ ኦንላይን ድረገፅ  ዘገበ፡፡

ሁለቱም ወገኖች በዚሁ የበርካታ ሰዓታት የአዲስ አበባ - ለንደን ጉዟቸው ወቅት መነጋገራቸውንና አለመነጋገራቸውን ማወቅ አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ምንጮች እንደጠቁሙት የሱፍና ሪያል እንዲሁም የእያንዳንዱ ልኡክ ቡድን በአውሮኘላኑ ውስጥ በአንደኛ ማዕረግ ክፍል በጋራ መጓዛቸው ድረገፁ አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ምንጮች ለድረገፁ እንደጠቆሙት ከሆነ ይህ የሁለቱም መሪዎች የጋራ ጉዞ ያልታቀደና በአጋጣሚ መሆኑ ነው፡፡

ሶማሊላንድ ከሶማሊያ ለመገንጠል ጥያቄ በማቅረብ ላይ ስትሆን በራስዋ ፍቃድ ነፃነትዋን ካወጀች እነሆ ከ10 ዓመት በላይ አስቆጥራለች፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት የሽግግር መንግሥቱን በኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል ድጋፍ የእስላማዊ ፍ/ቤቶች ኅብረት ከበታተነ በኋላ የሶማሊላንድ ..ክልል.. ነፃነት እንደማይቀበል የገለፀ ሲሆን፣ የሶማሊላንድ መሪዎች በበኩላቸው በአገራቸው ነፃነት እንደማይደራደሩ ገልፀዋል፡፡ ሶማሊላንድ በዓለም ማህበረሰብም ህጋዊ እውቅና እንዲሰጣት እየጠየቀች ትገኛለች፡፡

በተለይ በአንዳንድ ግዛቶች ውዝግብ ምክንያት ሁለቱም ወገኖች ባለፈው ዓመት የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ከሣምንት በፊት ፕሬዚዳንት የሱፍንና ሪያል በሚድያ አማካኝነት እርስ በርሳቸው ተወነጃጅለዋል፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የሱፍ አብዱላሂ የሶማሊላንድ ወታደሮች ባለፈው ዓመት ከፑንትላንድ (የፕ/ቱ የትውልድ ቦታ) ግዛት በኃይል የተቆጣጠሯት ሱል የተባለችው ግዛት ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ የሶማሊላንድ መሪ ዳሂር ሪያል በበኩላቸው ለዚሁ የፕሬዚዳንት የሱፍ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፣ ..ፕሬዚዳንት የሱፍ ሁሉን በማስፈራራት የሱልን ግዛት በኃይል ለመውሰድ ፍላጎት አላቸው.. ብለዋል፡፡

ሁለቱም ተቀናቃኝ መሪዎች በአንድ አውሮኘላን ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ በተመሳሳይ ክፍል ይጓዙ እንጂ ወደ ለንደን ያደረጉት ጉዞ ለተለያየ ዓላማ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ የሱፍ ወደ ከተማው የሄዱት የጤንነታቸው ሁኔታ ለመከታተል ሲሆን፣ የሶማሊላንድ መሪ ደግሞ ከ1983 ዓ.ም ነፃነትዋን ያወጀችው ግን እስከ አሁን የዓለም ማህበረሰብ ዕውቅና ያልቀናት ግዛታቸው ዕውቅና ለመጠየቅ ከሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት አካል ነው፡፡ ኘሬዚዳንቱ ቅዳሜ ወደ ለንደን ከማምራታቸው በፊት ዓርብ ዕለት እዚሁ አዲስ አበባ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተዋል፡፡

ሁለቱም ወገኖች እርስ በርሳቸው አንዱ ለሌላው ዕውቅና አይሰጡም፡፡ ፕሬዚዳንት የሱፍ የሶማሊላንድ ግዛት የዋናው ሶማሊያ አካል አድርገው የሚቆጥሩት ሲሆን፣ የሪያል ..መንግሥት.. በበኩሉ የሶማሊያ ሽግግር መንግሥትን ስልጣን አይቀበልም፡፡

ሪያል በቅርቡ ለአንድ የሬዲዮ ጣቢያ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የሚደግፉ ሲሆን ለሽግግር መንግሥቱን ግን ዕውቅና አይሰጡም፡፡ 

በ1983 ዓ.ም በራስዋ ፍቃድ ነፃነትዋን ያወጀችው ሶማሊላንድ እስከ አሁን የዓለም ማህበረሰብ ይፋዊ ዕውቅና ባታገኝም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዴሞክራሲያዊ የሚባል ምርጫ ያደረገችና በአፍሪካ የተሻለች ዴሞክራሲያዊት አገር መሆንዋን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የተቀረው የሶማሊያ ክፍል ከ1983 ዓ.ም ከሳይድ በሬ መንግሥት ውድቀት በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት ሲታመስና መንግሥት አልባ ሆኖ የቆየ ሲሆን ባለፈው ዓመት የእስላማዊ ፍ/ቤቶች ኅብረት በማሸነፍ ስልጣን የተቆጣጠረው የሽግግር መንግሥቱ እስከ አሁን ሙሉውን የሶማልያ ግዛት በቁጥጥር ሥር አውሎ ሠላምና ፀጥታ ለማስፈን ጥንካሬው አስተማማኝ አይደለም፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

 
< Prev   Next >