|
Sunday, 13 April 2008 |
 ቅዱስ ያሬድ ከአፄ ገብረ መስቀል ፊት ሲዘምር "አልቦ እምቅድሜሁ፣ ወአልቦ እምድኅሬሁ" ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ፤ እርሱን የመሰለ አልተገኘም፡፡ ማን? ማኅሌታይ ያሬድ፡፡ ዛሬ ሚያዚያ 5 ቀን 2000 ዓ.ም ቅዱስ ያሬድ የተወለደበት ቀን፡፡ 1495 ዓመቱ ላይ ደርሰናል፡፡ በስሙ በታነጹት አብያተ ክርስቲያናት እንደሚታሰብ ይታመናል፡፡ በተዛባው የሺሕ ዓመት አቆጣጠርና አከባበር ላይ ልዩ ልዩ መሰናዶዎች እንዳሉት የሚያወጋው ብሔራዊው ጽ/ቤትም ሆነ የመዲናዋ ኮሚቴና ቤተ ክህነት ስለ ዝክረ ዕለቱ ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡ በስሙ የተሰየመው ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትም ድምፁ አልተሰማም፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ የታላቁ ኢትዮጵያዊ ሥራዎችን በማንሳት ዕለቱን ትዘክራለች፡፡
* * * "ፈልቀሽ የተገኘሽ ከሹበርት ራስ ከቤቶቨን ናላ ከሞዛርት መንፈስ ከሾፐን ትካዜ ከያሬድ ልቡና መዓዛ የሞላብሽ የብስጭት ቃና ረቂቋ ድምፅ ሆይ ውቢቷ ሙዚቃ ውብ እንደ ፀሐይ ንጽሕት እንደ ጨረቃ"
ስመ ጥሩ ገጣሚ ከበደ ሚካኤል ስለ ሙዚቃ ከገጠሙት የተወሰደ ነው፡፡ ያሬድ የሙዚቃ ልቡና መሆኑን ያጠይቃል፡፡
በስድስተኛው ምእት ዓመት የተነሳው ቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ አምስት ዐበይት መጻሕፍትን በመድረሱ ከዜማው ጋር አብሮ ይወሳል፡፡
የድጓና የማኅሌት አባት ያሬድ፣ አሮድዮን እንደሚባለው ወፍ ዜማው ልብ የሚመስጥ እጅግ ድምፀ መልካም ስለሆነ የዜማው ደራሲ ያሬድ፣ ወፉም ዖፈ ያሬድ መባሉን ርእሰ ደብር ጥዑመ ልሳን ካሳ በመጽሐፋቸው ገልጸውታል፡፡
አንድ የጎጃም ባለቅኔ ይኸንን በማስመልከት "አእመርናሂ ከመ ሀሎ በቀራንዮ ገነት፣ ያሬድ ዘወለዶ ሄኖክ ማኅሌት፡፡" ብሎ ተቀኝቷል፡፡ ትርጉሙ ያሬድ የወለደው ሄኖክ ማኅሌት በቀራንዮ ገነት እንዳለ አወቅን፣ ተረዳን ማለት ነው፡፡ ምሥጢሩም ሲብራራ ሄኖክ እንደ ኤልያስ በሥጋ ወደ ሰማይ አርጎ እንደሚኖር ሁሉ ማኅሌትም የተገኘው ከሰማያውያን መላእክት ዘንድ መሆኑን ለማነጻጸር ነው፡፡
በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት (515-529) ስለነበረው ማኅሌታይ ያሬድ የተለያዩ የታሪክ ምንጮች ሲኖሩ አንዳንዶቹ የሚመሳሰሉበትና የሚለያዩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ለምሳሌ ወላጆቹን በተመለከተ የተለያዩ ስሞች አሉ፡፡ አባቱ አብዩድ፣ ይስሐቅ፣ አዳም፣ እምበረም እናቱን ደግሞ ታውክልያ፣ ክርስቲያን እያሉ የጻፉ አሉ፡፡
ያሬድ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዜማ ያደራጀና ለ1500 ዓመታት በተከታታይ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ነው፡፡ የያሬድ ዜማ አደራረስ ትረካ ወደ ሚቶሎጂ ደረጃ ከመወሰዱም በላይ ድርሰቱም ሰማያዊ በረከት በመሆኑ ቅድስና ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ ወደ ሚቶሎጂ ያመራው አንዱ ነጥብ በስንክሳር ግንቦት 11 ቀን ምንባብ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ "እግዚአብሔርም መታሰቢያ ሊያቆምለት በወደደ ጊዜ ከኤዶም ገነት ሦስት አፅዋፍን ላከለት፡፡ እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ከእነርሱ ጋራ አወጡት፡፡ በዚያም 24ቱ ካህናት ሰማይ የሚያመሰግኑትን ማኅሌታቸው ተማረ፡፡"
ይህቺንም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት፡፡ የቃሉንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ንጉሡም፣ ንግሥቲቱም፣ ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ የመንግሥት ታላቆችና ሕዝብ ሁሉ ወደርሱ ሮጡ፤ ሲሰሙትም ዋሉ፡፡ ከዚያም በኋላ ከዓመት እስከ ዓመት፣ በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፣ በመጸውና በጸደይ በአጽዋማትና በበዓላት፣ በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በዓል በነቢያትና በሐዋርያት፣ በጻድቃንና በሰማዕታት፣ በደናግልም በዓል የሚሆን አድርጎ በሦስቱ ዜማው በግእዝ፣ በዕዝል፣ በአራራይ ሠራው፡፡"
ያሬድ ለዜማው መሠረት የኾኑት ድርሰቶች አምስት ናቸው፡፡ እነሱም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕት፣ ምዕራፍ ናቸው፡፡ ከዘመነ አክሱም ጀምሮ እስካሁን የዘለቁት ንዋያተ ማኅሌት (የዜማ መሣሪያዎች) መቋሚያ፣ ጸናጽልና ከበሮ ናቸው፡፡
የዜማ ስልቱም (ሜሎዲ) በሦስት መሠረታዊ መደብ ግእዝ፣ ዕዝልና አራራይ ተብለው ይከፈላሉ፡፡ የድጓው ድርሰት በአራቱ ክፍላተ ዘመን (ወቅቶች) ተመሥርቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የክረምትና የመጸው ድርሰቶቹን እነሆ፡፡
ክረምት
"ደምፀ እገሪሁ ለዝናብ ሶቦ ይዘንብ ዝናብ ይትፌስሑ ነዳያን ደምፀ እገሪሁ ለዝናብ ሶበ ይዘንብ ዝናብ ይፀግቡ ርሁባን" (ሲተረጐም) የዝናብ ኮቴ ተሰማ፤ ዝናብ በዘነበ ጊዜ ነዳያን ይደሰታሉ፤ የተጠሙ የተራቡ ይጠግባሉ፡፡
መፀው/መከር "በጊዜሁ ኀለፈ ክረምት ቆመ በረከት ናሁ ጸገዩ ጽጌያት" (ሲተረጐም) ክረምቱ በጊዜው አለፈ አሁን የበረከት ጊዜ ይሆናል አበባዎችም ያብባሉ፡፡
የትንሣኤ በዓል በመጣ ቁጥር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን እየተቀባበሉ የደስታ መግለጫ የሚያሰሙበት የትንሣኤ ምልልስ የደረሰውም ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡
"ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዐቢይ ኃይል ወ ሥልጣን አሠሮ ለሰይጣን አግአዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ይኩን ሰላም፡፡" (ሲተረጐም) ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሳ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ሰይጣንን አሠረው አዳምን ነፃ አወጣው በዚህም ሰላም ይሁን፡፡
የታሪክ ማዕምሩ ዶክተር ሥርግው ሀብለ ሥላሴ በጥናታቸው ለኢትዮጵያ ባህላዊ ዕድገት ማኅሌታይ ያሬድ ያደረገውን አስተዋጽዖ ይዘረዝራሉ፡፡
ሀ) የቅኔው ወጣኒ (ጀማሪ"ና የባህላዊ ትምህርት መሥራች ይሉታል፡፡ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የተጀመረው በቅኔ መልክ ሆኖ በኋላ ወደ ዝርው (ስድ) ተሻገረ፡፡ የያሬድ ድጓ የቅኔና የዝርው ስብጥር ነው፡፡
ሁ) በሥነጽሑፍ ረገድ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ልዩ ቦታ አለው፡፡ ታላቁ ድርሰት ድጓው የ"ኤፒክ" ቅርጽ ወይም ዓይነት ያለው የመላእክትን፣ ቅዱሳንና ሰማዕታትን ትግል አጉልቶ በቅኔያዊ ቋንቋው ያሳያል፤ ይገልጣል፡፡
ያሬድ ስለ ጥበብ ያለው አተያይም በድጓው ውስጥ ይስተዋላል፡፡ "ጥበብ ትኄይስ እምብዙኅ መዛግብት ኢወርቅ ሤጡ ወኢብሩር ተውላጡ ጥበብ ክቡራት ዕንቁ መሠረት አልቦ ለጥበብ ዘይመስላ፡፡"
ጥበብ በዋጋ የማትተመን የሰው ልጅ ስጦታ ናት፡፡ በዚህች ዓለም ከጥበብ ጋር የሚወዳደር አንዳች ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ሀብትን ከመሰብሰብ ይልቅ ጥበብን መጠየቅ ይሻላል፡፡ ወርቅ፣ ብር፣ ዕንቁ ወይም ማንኛውም የተከበረ ደንጊያ ከጥበብ ጋር ሊተካከሉ ሊመሳሰሉ አይችሉም፡፡
ሰው ሊመረምር፣ ሊያውቅ እንደሚገባ ያሬድ አጽንዖት ሰጥቶ ጽፎበታል፡፡ በድጓው ውስጥ ዘመነ ዮሐንስ በተሰኘው ክፍል ውስጥ የጠቀሰው "ዑቅ ወጤይቅ፣ አእምር ወለቡ" (እወቅና ጠይቅ፣ አውቀህም አስተውል) ይህንኑ ያሳያል፡፡
ቅዱስ ያሬድ ከድጓ ደራሲነቱ ሌላ ለዝማሬ እንዲመች ምልክት (ኖታ) አበጅቶላቸዋል፡፡ በኋላ ዘመን በዘመነ ጎንደር በ17ኛው ምእት ዓመት ታካይና ተጨማሪ ምልክቶች ሊቃውንቱ አዘጋጅተውለታል፡፡ ፀሥሩ ምልክቶች ይዘት፣ ደረት፣ ርክርክ፣ ድፋት፣ ጭረት፣ ቅናት፣ ሂደት፣ ቁርጥ፣ ድርስ፣ አንብር ይሰኛሉ፡፡
ያሬድ ማኅሌታይ በድርሰቶቹ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና የታሪክ፣ የሥነ ምኅዳር (ስለ አካባቢ ጥበቃ - ኢኮሎጂ) ፍሬ ጉዳዮችን የመረመረበትና ያመለከተበት ሁኔታ ጎልቶ ይታያል፡፡ ስለ ሥነ ምኅዳር ከነገረ መለኮት ጋር አያይዞ በግንባር ቀደምትነት "ኤ"ኮቴኦሎጂ" (ኢኮሎጂና ቴኦሎጂ) ጽንሰ ሐሳብ ያስተዋወቀ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤኮቴኦሎጂ የበላይ ጠባቂ (ዘፓትረን ኦፍ ኢትዮፒያን ኤኮቴኦሎጂ) ተብሎ ሊጠራ፣ ሊታወጅለት ይገባል፡፡
ስለ ቅዱስ ያሬድ ታላቅነት መታሰቢያ ምን ሠራን? በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በስሙ "ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት" የተሰየመ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ውስጥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መካከል ላይ ያለው ዐውራ ጎዳና "ያሬድ መንገድ" ተብሎ ተሰይሞለታል፡፡ ሐውልት ግን የለውም፤ ለምን? ቦሌ መድኃኔ ዓለም አካባቢ ያለው አደባባይ ላይ (የአንድ ተቋም በርሚልን ለማስተዋወቅ የደንጊያ ክምር በተተከለበት ጊዜ በአንድ መድረክ የቀረበ አስተያየት) ሐውልቱ እንዲተከል ሐሳብ ቢቀርብም ከቤተ ክህነትም ሆነ ከቤተ መንግሥቱ (ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር) ከቁብ የቆጠረውም የለም፡፡ የቀድሞው የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ዳይሬክተር መራሔ መዘምራን (ኮንዳክተር) አማኒ ኢብራሂም በ1970ዎቹ አጋማሽ በአንድ መጽሔት ስለ ት/ቤቱ ተጠይቀው ሲመልሱ ስለ ቅዱስ ያሬድ ታላቅነት አውስተው "ሐውልት ቢቆምለት በወደድኩ" ብለው ነበር፡፡ ያኔም ሆነ አሁን ያዳመጠና ወደ ተግባራዊነት ለመሸጋገር የሞከረ የለም፡፡ አሁንም ድምፃችንን እናሰማለን፡፡ ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ለኢትዮጵያ ሺሕ ዓመት መታሰቢያ ይሆነው ዘንድ "ሙዚቃ ሕይወቴ" ብለ ባወጣው አልበሙ ቅዱስ ያሬድንና ሥራውን በዜማው አስታውሶታል፡፡
በ1970ዎቹ አጋማሽ የኢትዮጵያ ደብተራዎች ያሬዳዊ ዜማን ለማሰማት ወደ አውሮፓ የተለያዩ ከተሞች አምርተው አስደናቂውን ዜማ አሰምተው ነበር፡፡
የቢቢሲ ራዲዮ "ፎከስ ኦን አፍሪካ" አዘጋጅ ፕሮግራሙን ተከታትሎ ከተረዳ በኋላ ምን እያላችሁ ነው? በስድስተኛው ምእት ዓመት አፍሪካዊው ያሬድ በራሱ ድርሰት፣ በራሱ ኖታና የዜማ መሣሪያ ከነ ሞዛርት፣ ቤቶቨን በፊት ዜማ ደርሷል ማለታችሁ ነው፡፡ ምነው እስካሁን ደበቃችሁት? ወይ የያሬድ ሰዎች ያሬድን አታውቁትም፤ አሊያም ንፉጎች ናችሁ ብሎ መናገሩን አስታውሳለሁ፡፡ በሔኖክ ያሬድ |