|
Sunday, 13 April 2008 |
 ሲስተር ዘውዲቱ በርሄ ለአእምሮ ህመም የቀረቡ፤ ለህክምናው የራቁወደ አማኑኤል ሆስፒታል በሄድኩበት ወቅት ለሴት የአእምሮ ህመምተኞች የፅዳት ቀን ነበር፡፡ ወደ ሴቶች የመኝታ ክፍል በሚወስደው መንገድ ጥግጥጉን ቁጭ ብለው ፀጉራቸውን የሚሰራሩ ሴቶች፣ ከርቀት ቧንቧ አጠገብ መለመላዋን ቁማ ገላዋን የምትታጠብ ሴት ትታያለች፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ሜዳው ላይ ብቻቸውን ተኝተዋል፤ ሌሎች እየተዘዋወሩ ብቻቸውን ያወራሉ በአካባቢው ፀጉረ ልውጥ የሆነን ሰው ለቡና መጠጫ ብር ስጡኝ እያሉ የሚለምኑም አይጠፉም፡፡ ፀጉራቸውን ከሚሰራሩት ውጭ ሌሎቹን በጋራ ሲያወሩና ሲወያዩ አላየሁም፡፡
ሁሉም በየፊናው ያሻውን ያደርጋል፡፡ በሆስፒታሉ ከሚገኙ ሦስት የሴቶች መኝታ ክፍሎች ወደ አንዱ ሳመራ ከስታ የገረጣችና የምትቆዝም ልጅ እግር ሴት አጠገቤ ላለችው ነርስ ሳይካትሪስት ሰላምታ ሰጥታ እንዳቀረቀረች ወደ ክፍሏ ገባች፡፡
ይህች ሴት ወደ ሆስፒታሉ ሄደው ለመታከም እድል ከገጠማቸው ጥቂት የአእምሮ ህመም በሽተኛ ሴቶች መካከል አንዷ ብትሆንም ይሄንን እድል ያገኘችው ለረዥም ገዜ ከተሰቃየች በኋላ መሆኑን ካነጋገርኳት የሆስፒታሉ ነርስ ሳይካትሪስት፤ ሲስተር ዘውዲቱ በርሄ ተረድቻለሁ፡፡ ..ባለትዳር እና የልጆች እናት ነች፡፡ ህመሙ ሲጀምራት ቤት ውስጥ የነበራት ባህሪ ተቀየረ፡፡ ቤት ውስጥ የነበራት ሚና ሁሉ ቀረ፡፡ አልጋዋን ከባለቤቷ ለየች፣ ልጆቿን እንደበፊቱ አትንከባከብም፣ ከቤት አትወጣም፣ ማንንም አታናግርም፣ ቤተሰቦቿንም አትጠይቅም፡፡ ፀባዩዋ ሲቀየር ባለቤቷ ጠይቋት ከሷ ምላሽ ሲያጣ ፣አመሏ ተቀየረ፣ ብሎ ተዋት፤ ዘመዶቿም ተቀይማ ይሆናል እያሉ ሁኔታዋን በቸልታ አለፉት፡፡ ልጅቷ አእምሮዋን እንዳመማት ሳይታወቅላት በዚሁ መልኩ ለሦስት ዓመት ቤት ውስጥ ከርማለች..
ሲስተር ዘውዲቱ እንደሚሉት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት በርካታ ሴት የአእምሮ በሽተኞች ከወንዶች ይልቅ ተጎድተውና ለብዙ ዓመታት ከተሰቃዩ በኋላ ነው፡፡ እቤታቸው ታስረው የኖሩ፣ ለብዙ ዓመታት እቤታቸው ታፍነው የኖሩና በሽታው የበረታባቸው ናቸው፡፡ ይህም ከህብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት እንደሆነ ነው ባለሙያዋ የሚናገሩት፡፡ ..ባል ሚስቱ ብትታመም ይፈታታል፣ ቤተሰብም እቤቱ ወስዶ ነው ድብቆ የሚያስቀምጣት፡፡ በተለይ ወደ ክፍለ ሃገር ይህ የተለመደ ነው፡፡ እቤት ለመቀመጥ ካስቸገረችና ጉዳት የምታደርስ ከሆነ ትታሰራለች ከከፋም ጎዳና ላይ ወጥታ እብድ እየተባለች ትኖራለች..
ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ በሽተኞች መካከል የሴቶች ቁጥር ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት ሲስተር ዘውዲቱ ይህ ማለት ግን አእምሯቸውን የሚታመሙ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ነው ማለት እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ በህመሙ የሚጠቁ ሴቶች ቁጥር ከወንዶች የማይተናነስ ቢሆንም ወደ ህክምና የመምጣት እድል ያላቸው ግን ጥቂቶች መሆናቸውን ባለሙያዋ ገልፀዋል፡፡
በሆስፒታሉ ከ2ዐ ዓመት በላይ የሥራ ልምድ ያላቸው ሲስተር ዘውዲቱ ከበሽተኞች የህይወት ታሪክ በመነሳት ሴቶች በአብዛኛው ለአእምሮ ህመም የሚጋለጡባቸው መንስኤዎች የተለያዩ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አንዳንዶች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ወደ ሰው ሃገር በሚሄዱበት ወቅት በሚደርስባቸው የተለያየ ተፅእኖ ለአእምሮ ህመም ይጋለጣሉ፡፡ በሚሄዱበት ሃገር ቋንቋውንና ባህሉን አለማወቃቸው፣ ከቤተሰብ መራቃቸውና ለአካባቢው አዲስ መሆናቸው፣ በሚሰሩበት አካባቢ የሚፈፀምባቸው ጥቃት ካለ እነዚህ ሁሉ ተደራርበው የሚፈጥርባቸው የብቸኝነት ሥሜትና ጭንቀት የሚያስከትልባቸው ጭንቀት ለአእምሮ ህመም ያጋልጣቸዋል፡፡ በየጊዜው በተለይ ከአረብ ሃገር የሚመጡ ብዙ ሴቶችን እንደሚያክሙም ባለሙያዋ ይናገራሉ፡፡
ሴቶች ላይ የሚፈፀም የአስገድዶ መድፈር ወንጀልም ሌላው ለሴቶች የአዕምሮ ህመም መንስኤ እንደሆነ ባለሙያዋ ያብራራሉ ..ተገዶ መደፈር የደረሰባት ሴት አእምሮዊ ሰላም አያገኙም፡፡ በዛ ላይ ብዙዎች ለቤተሰብ ለመናገር ይፈራሉ፡፡ ችግራቸውን አለማካፈላቸው በራሱ በነሱ አእምሮ ላይ ጫናው እንዲበዛ ምክንያት ይሆናል፡፡ ባህሉም ጉዳዩ እንዲጨነቁ ምክንያት ነወ፡፡ በልጅነቷ ተገዳ የተደፈረች ልጅ ለጋብቻ ስትደርስ ሳትፈልግ መደፈሯ ከፈጠረባት ቁስል በተጨማሪ ክብረ ንፅህናዋን በማጣቷ ባህሉ የሚያስከትልባትን ታውቃለችና ለከፍተኛ ጭንቀት ትደረጋለች፡፡ ይህም ለአእምሮ ህመም አጋልጧቸው ለህክምና የሚመጡ ብዙ ሴቶች እንዳጋጠማቸው ገልፀውልናል፡፡
የአእምሮ ህመም አንዳንዴ በዘር እንደሚተላለፍ የገለፁት ሲስተር ዘውዲቱ ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሁለት እህትማማቾች እናትና ልጅ ታመው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡበት አጋጣሚ መኖሩ ያስረዳሉ፡፡ ወልዶ በማሳደግና ቤት በማስተዳደር በኩል ብዙ ጫናዎችና ጭንቀቶች ሴቶች ላይ መሆናቸው ተጨማሪ ምክንያት ነው፡፡ ለአእምሮ ህመም ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት ከ17 ዓመት እስከ 5ዐዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን በወጣትነት የእድሜ ክልል የሚገኙ ማለትም ከ17-26 ዓመት የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህ ሴቶች ራሳቸውን ለመቻል የሚጥሩበት እድሜ በመሆኑ ህይወትን ለማቃናት በሚያደርጉት ጥረት አለመሳካት ለህመሙ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡
ባለሙያዋ እንደሚሉት ብዙ የአእምሮ ህመምን በተመለከተ የሚደርስባቸው ተፅእኖ ከታመሙ በኋላ ቶሎ ወደ ህክምና አለመሄዳቸው ወይም ጭራሽ ህክምና አለማግኘታቸው ብቻ አይደለም፡፡ እቤት ውስጥ የአእምሮ ህመም የደረሰባቸውን የቤተሰብ አባላት በመንከባከብ በኩል ጫናው ያለው እናቶችና ሴት ልጆች ላይ ነው፡፡ ..የሚጨነቁና ኃላፊነት የሚሰማቸው ወንዶች ቢኖሩም ብዙዎቹ ግን ቸልተኛ ሲሆኑ ይታያል፡፡ ስለዚህ ጫናው ሴቶች ላይ ይበረታል፡፡ የአእምሮ ህመምተኛን ማስታመም ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ሁሌ እንድታዝኚ፣ እንድታለቅሺ ያስገድድሻል፡፡ ብዙ እናቶች ልጆናቸቸውን በማስታመም ደስታ አልባ ይሆናሉ፡፡ ባለመታከማቸው እንጂ ሁሌ ደስተኛ አለመሆን በራሱ የአእምሮ ህመም ያስከትላል..
ሲስተር ዘውዲቱ ሴቶች ምን ያህል የአእምሮ ህሙማን የሆኑ ቤተሰቦቻቸውን በመንከባከብ እንደሚጎዱ ከሥራ ልምዳቸው ያዩትን በመጥቀስ ምሳሌ ሰጥተዋል፡፡ ከጎጃም የምትመላለስ አንዲት እናት ሁለት ሴት ልጆቿ የአእምሮ በሽተኞች ሲሆኑ ሦስተኛው ልጇ የአእምሮ እድገት ዝግመት ተጠቂ ነው፡፡ ባለቤቷ ጥሏት ሄዶ ሌላ ሚስት አግብቷል፡፡ አስተማሪ ብትሆንም ብዙ ጊዜዋን በሽተኛ ልጆቿን በመንከባከብ ታጠፋለች፡፡ ህመማቸው ሲብስባቸው ሁለቱንም ወደ አዲስ አበባ በማምጣት አማኑአል ሆስፒታል ታስገባቸዋለች፡፡ ባለሙያዋ እንደሚሉት ይህች እናት ደስታ የሚባል አይታውባት እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡
ይህ ማለት ግን ሁሉም ወንዶች ቸልተኛ ናቸው ማለት እንደማይቻል ጠቅሰው በተቃራኒው ደግሞ የአእምሮ በሽተኛ የሆኑ ሚስቱንና ሁለት/ልጆቹን የሚያስታምም ባል እንደሚያውቁ ገልፀውልናል፡፡ ..የሰዎቹ ቤት የአጥሩ በር በትልቅ ሰንሰለት ታስሮ ይጠበቃል፡፡ ዘበኛው ዘወትር ትልቅ ዱላ ይዞ ይጠብቃል፡፡ ቤቱን የሚያስተዳድሩት ብቸኛ ጤነኛ ሰው ባል ናቸው፡፡ ህይወታቸው፣ ኑሯቸው በጣም ያሳዝናል..
ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ በሽተኞች ሁሉ በፍጥነት ህክምና የሚያገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸትም በፊት እስከ ሦስት ወር ድረስ ተኝቶ መታከም ይቻል የነበረው አሁን እስከ ሁለት ወር ድረስ ዝቅ እንዳለ ባለሙያዋ ገልፀውልኛል፡፡ ብዙዎቹ በሚደረግላቸው ህክምና ከሁለት ወር በኋላ ተሽሏቸው ቤታቸው ሆነው እየተመላለሱ መድኃኒት በመውሰድ የሚታከሙ ሲሆን ብዙዎቹም እንደማንኛውም ሰው ቢሮ ገብተው ሥራቸውን ማከናወን ይችላሉ፡፡ እንደገና ሲታመሙም ወደ ሆስፒታሉ ይመለሳሉ፡፡ ይሁንና እንደ በሽታቸው ክብደትና ባህሪ ጭራሽ የማይድኑ መኖራቸውን ጠቅሰው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዳይጎዱ መድኃኒት እየተሰጣቸው እንዲኖሩ የሚደረግ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከበር ስገባ ያየኋቸው ፀጉራቸውን ሹሩባ የተሰሩ፣ ረዥም ቀይ ቀሚስና ሁለት ሻርፖችን አደራርበው የለበሱ ሽበታም እናት ከማርጀታቸው የተነሳ ጥርሳቸው ወላልቋል፡፡ እየዞሩ በግልፅ በማይሰማ አማርኛ ለቡና መጠጫ ሳንቲም ይለምናሉ፡፡ እኒህ ሴት በሆስፒታሉ ከ4ዐ ዓመት በላይ የኖሩ እንደሆኑ ከዘበኛው ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ቤተሰብ የሌላቸውና መዳን የማይችሉ ለረዥም ጊዜ እንዲኖሩ ይፈቀድላቸው ይሆን የሚል ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር ..በፊት ለረዥም ዓመታት ይኖሩ ነበር፡፡ በመንግሥት ስር የሚቆዩ አሉ፣ ወደ ገፈርሳ የአእምሮ ህመምተኞች ማገገሚያ ቦታ የሚላኩም አሉ..
ወደ አማኑኤል ከሚገቡ የአእምሮ በሽተኛ ሴቶች መካከል ኤች.አይ.ቪ ፖዜቲቭ የሆኑም መኖራቸውንም ሲስተር ዘውዲቱ ገልፀውልኛል፡፡ ተመርምረው ራሳቸውን በማወቅ የምክር አገልግሎት አግኝተውና ፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ጀምረው የሚመጡ መኖራቸውን ጠቅሰው የአእምሮ ህመሙንም የፀረ ኤች.አይ.ቪውንም መድኃኒት እየተከታተሉ እንዲወስዱ ይቆጣጠሯቸዋል፡፡ ኤች.አይ.ቪን በተመለከተም ፈቃደኛ ለሆኑና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመመካከር የኤች.አይ.ቪ ምርመራ እንዲያደርጉ ለተወሰነላቸው አእምሮ በሽተኞች የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥ ባለሙያዋ ጠቁመዋል፡፡
ባለሙያዋ እንደሚሉት ብዙ ጊዜ ሴቶች በቀላል ነገር ተጣልተው የሚደባደቡበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንዷ አጥባ ያሰጣችውን የውስጥ ሱሪ ሌላዋ ትወስዳለች፡፡ ቫዝሊኗንም ሌሎች ሊወስዱባት ይችላሉ፡፡ ከቤት ተሰርቶ የመጣ ቆንጆ ምግብ ካገኙም አንስተው ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ይሄንን የሚያደርጉት ሜዳ ላይ ያገኙት እንጂ የሰው ንብረት የወሰዱ መስሎ ስለማይሰማቸው ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የሚጣሉበትና ቢሮ ወስደው የሚያስታርቁበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈፅሙ የአእምሮ ህሙማንን ስለኤች.አይ.ቪ ማስተማርና የሰው ምላጭ እንዳይጠቀሙ መምከር ትርጉም አለው ወይ? የሚል ጥያቄ አንስቼላቸው ነበር ..እንመክራቸዋለን፤ ሊሰሙም ላይሰሙም ይችላሉ፡፡ አስቸጋሪ ነው.. የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
ሲስተር ዘውዲቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር ከተመረቁ ሳይካትሪ ነርሶች አንዷ ናቸው፡፡ በሙያውም ለረዥም ዓመት አገልግለዋል፡፡ በራሳቸው ወቅት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ሃይለኛና የሚያረጋጋ መርፌ ቶሎ ካልተሰጣቸውም ንብረት የማውደምና ሰው የመደባደብ ባህሪ ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ እንደመጣ ቶሎ መድኃኒት በክኒን መልክ አልውጥም ብለው ካስቸገሩም በመርፌ ይሰጣቸዋል፡፡ በጣም ስሜታዊ ከሆኑ መርፌው እስኪሰራ ይታሰራሉ፡፡
በበሽተኛ የተደበደቡበት ብዙ አጋጣሚ ቢኖርም ባለሙያዋ የአንድ ቀን ገጠመኛቸውን አካፍለውኛል፡፡ ..አንድ ቀን በኮሪደር ሳልፍ አንዷ ፀጉሬን ይዛ አሽከረከረችኝና ልትመታኝ ስትል አመለጥኳት፡፡ ምነው ስላት ባሌን የቀማሽኝ አንቺ ነኝ፡፡ አስታወሳለሁ ወፍራም ቀይ ሴት አንቺ ነሽ.. አለችኝ፡፡ ባሏን እንደማላውቀው፣ ባለትዳርና የልጆች እናት እንደሆንኩ ነግሬያት አረጋጋኋት፡፡ በመጨረሻ ለሃኪሟ ነግራው አስታርቆኛል፡፡ በትዕግሥት ዘሪሁን |