|
"እያዩ ነው መውደድ እያስተነተኑ. . ". |
|
|
|
Sunday, 13 April 2008 |
|
በያዝነው የ2008 ዓመት ቻይና ቤጂንግ ላይ የሚካሄደው ሃያ ዘጠነኛው (የሰመር) የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ከዚህ ቀደም ሲል በአቴንስ ግሪክ (2004) በሲድኒ አውስትራሊያ (በ2000) በአትላንታ አሜሪካ (በ1996) በባርሴሎና (በ1992) ተዘጋጅተው የተካሄዱት ተመሳሳይ የኦሊምፒክ ጌሞች የሚለየው ነገር እንዳለ በርካታ ምልክቶች ከወዲሁ እየታዩ ነው፡፡ የዘንድሮውን የቤጅንግ ኦሊምፒክ "ልዩ የሚያደርገው" ቶክዮ (1964) እና ሶል (1988) ካዘጋጁት በስተቀር ከዚያ ወዲህ የጨዋታዎቹ ውድድር በኤሽያ ምድር ሲካሄድ የመጀመሪያውና በ29ኙ የኦሊምፒክ ታሪክ ደግሞ ሦስተኛው መሆኑ አይደለም፡፡ የዓለም አንድ ስድስተኛ ሕዝብ በሚገኝበት አገር ገና ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱ እውነት ቢሆንም ልዩ የሚያደርገው ግን ይህ አይደለም፡፡
ቻይና የጨዋታው ውድድር የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ከሚደረግበት ቀን ልክ አንድ ዓመት በፊት ጀምራ ልክ እንደ እርጉዝ (ይህን ያህል ቀረው እያለች) እስክትቆጥር ድረስ የተዘጋጀችበት ይህ መስተንግዶ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴንም ባልተለመደ ሁኔታ ያስደነቀበትና ያስደነገጠበት ምክንያትም ነበር፡፡ እንደተለመደው የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በየአራት አመቱ የአዘጋጅነቱን ውድደር አሸንፈው በተመረጡት ከተሞች ከዝግጅቱ በፊት ጀምሮ ምን ደረሳችሁ? እያለ ይቆጣጠራል፤ ዞሮ እያየ ዝግጅቱ የደረሰበትን ደረጃ ይመረምራል፡፡ ቻይና አንድ ዓመት ቀረው ብላ ከ365 ቀን ጀምራ ሦስት መቶ ስልሳ አራት . . . እያለች ወደ ኋላ መቁጠር ከመጀመርዋ በፊት አገሪቱን የጎበኘው ዓለማቀፋዊው የኦሊምፒክ ኮሚቴ የተደነቀው ሁሉም ነገር ባልተለመደ ሁኔታና በዚያው ጊዜ ያለቀለት ዝግጁ ሆኖ የተጠናቀቀ በመሆኑ ነበር፡፡ መደነቁ አድናቆቱ ግን ብቻውን አልነበረም፡፡ ከመደነቁም ከመደነቅ በላይም መደናገጥ ነበረበት፡፡
ስታዲየሞቹ በአንድ ዓመት ተዘጋጅቶ ተጠናቅቆ ያገኘው አይኦሲ ቀደም አልቆ ዝግጁ የሆነው ስታዲየም (ለምሳሌ) ደግሞ እንደገና ጥገና እንዲያስፈልገው ብሎ አስደነገጠ፡፡ የዝግጅቱ ፍጥነት እንዲያዘግም ቀስ እያለ እንዲሰራ ጠየቀ፡፡ የዘንድሮውን የቻይና ኦሊምፒክ "ልዩ የሚያደርገው" አሁንም ይህ አይደለም፡፡
አምስተኛው ኦሊምፒክን ስቶክሆልም (ሲዊድን) በ1912 አዘገጅቶ 6ኛውና በ1916 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት ኦሊምፒክ ሳይከበር ሳይካሄድ የቀረው በመጀመሪያ የዓለም ጦርነት ምክንያት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አስራ አንደኛውን ኦሊምፒክ በርሊን (ጀርመን) ላይ በ1936 ተዘጋጅቶ በ1940 እና በ1944 ዓ.ም መካሄድ የነበረባቸው 12ኛውና 13ኛው የኦሊምፒክ ውድድሮች ግን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ሳይካሄዱ ቀርተዋል፡፡
በተለይም ሜክሲኮ ካስተናገደቸው አስራ ዘጠነኛው የኦሊምፒክ ጌምስ በኋላ ከመቶ በላይ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮማሪዎች (አገሮች) የሚሳተፉበት ይህ ሥነ ሥርዓትና ክብረ በዓል ሞንትሪያል ላይ በ1976 (21ኛው ኦሊምፒክ) ወደ 92 አገሮች፣ ሞስኮ ላይ በ1980 (22ኛው ኦሊምፒክ) ወደ 80 አገሮች ዝቅ ያለው አሁንም "በተመሳሳይ ምክንያት" በቀዝቃዛው ጦርነት ሳቢያ ነው፡፡ በተለይም የሞስኮው 22ኛው ኦሊምፒክ በ1980 ያስተናገዳቸው ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ቁጥር 80 የሆነው አሜሪካ የሚመራው ሌላኛው ካምፕ የሶቭየት ኅብረት አፍጋኒስታንን ወራለች ብሎ ባካሄደው ዘመቻ ብዙዎቹን አገሮች ቦይኮት እንዲያደርጉ አድርገው በማሳለፍ ነው፡፡
ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ወዲህ የተካሄዱት ከ25ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድሮች በኋላ ያሉት ኦሊምፒኮች (25ኛውን የባርሴሎና ኦሊምፒክ ጨምሮ) ስታትስቲኮች እንደሚያሳዩት ተሳትፎው የሁሉም እየሆነ፣ የተሳታፊዎች ቁጥር እየበዛ መምጣቱን ነው፡፡
በ1992 ባርሴሎና ላይ በ25ኛው ኦሊምፒክ አንድ መቶ ስልሳ ዘጠኝ አገሮች (ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች) እና ከዘጠኝ ሺህ አትሌቶች በላይ ተሳትፈዋል፡፡ የተሳተፉ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ቁጥር ወደ 197 እና 1999 የተፎካካሪ አትሌቶች ብዛት ደግሞ ከ10ሺህ በላይ ወደ ሆነ ቁጥር ያደገው እንደ ቅደም ተከተላቸው በአትላንታና በሲድኒ ውድድሮች ነው፡፡ በ28ኛው የ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ቁጥር በላይ ያላቸው ያንኑ ያህል ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች (አገሮች) ተሳትፈዋል፡፡ ከ"ቀዝቃዛው ጦርነት" ማከተም ወዲህ ተሳትፎው እየሰፋ የሄደው ዓለማቀፋዊ ሁነት ለመጀመሪያ ጊዜ የ"ወርተራው" ቻይና ላይ ሲደርስ ተቃውሞ ማስነሳቱ፣ "ቦይኮት" የሚባል ነገር እንደገና መምጣቱ ጉዳዩን ልዩ እያደረገው ሄዷል፡፡
ጉዳዩን ልዩ እያደረገው በሄደው በዚህ በቻይና (ቤጂንግ) ኦሊምፒክ ውስጥ አገራችንም ወይም የአገራችን የኢትዮጵያ ስምም ከአገር ድርሻ በላይ ምናልባትም ሳናውቀው ሳይታወቀን፣ ሳይታወቅ "ነገር የቆሰቆሰ" ያህል ያስመዘገበው ነገር መኖሩን ያንን ያህልና ከዚያ እኩል እንደ "ሰበብ" መቆጠራችን በየቦታው እየተወራ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የመንግሥት ሚዲያ በውጭ አገር ዜናም ሆነ በስፖርት ዘገባው አቋም ወስዶ እስከ አሁን የማያነሳው የአቴንስ፣ የለንደን የፓሪስ የሰንፍራንሲስኮ የኦሊምፒክ ችቦ ጉዞና ቅብብሎሽ ቀውስ ውስጥ መግባት የመጣው በዚያ ምክንያትም ባይሆን ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ይህንን ጥቂት ዘርዘን አድርገን እንመልክተው፡፡
በአገራችን የግል ጋዜጦች እንደተዘገበውና እንደነገሩም ቢሆን እንደተነካካው፣ ከዚያ ይበልጥ ደግሞ በመላው ዓለም የሚገኙ ትላልቅ ሚዲያዎች የስፖርት ዘገባና ትንታኔ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ሃተታና ሪፖርት በሰፊው እንዳስተጋባው የአገራችን ታላቅ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ባጋጣሚም ሆነ በ"እቅድ" በቤጂንግ ኦሊምፒክ (ማራቶን) አልሳተፍም ብሎ መግለጫ መስጠት እየተጠቀሰ ጉዳዩ በአገር ደረጃ ምናልባትም ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ፣ የሌሎች "ተሟጋቾች"ም አርአያና መንደርደሪያ ሆኖ መወሳቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ወደ ኋላ ላይ ኃይሌ በጉዳዩ ተለዋዋጭ መግለጫዎችና ማብራሪያዎች የሰጠ ቢሆንም ነገሩ "ከአፍ የወጣ አፋፍ" መሆኑ አልቀረም፡፡ ኃይሌ ታላቅ አትሌት ነው፡፡ ታላቅነቱም ከማውቀው በላይ መሆኑን የተረዳሁት ደግሞ "ሪቪልድ" የተሰኘውን የሲ ኤን ኤን ወርሃዊ ልዩ ፕሮግራም ካየሁ በኋላ ነው፡፡ ከአትሌቲክስ ዘርፍ ውጭም ባለው ፖለቲካዊ ተሳትፎውም በእጅጉ አከብረዋለሁ፡፡ ለአትሌቲክሱ በእጅጉ እየገፋ ነው የሚባል እድሜ ላይ እየተጠጋ መምጣቱ ከሱ እኩል ምናልባትም ከዚያም በላይ እንደ ዜጋ ቢያሳስበኝም በሌላ ዘርፍ ግን ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነው፡፡ የልጅ አዋቂም ነው፡፡ ከዘህ አኳያም ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተከሰተው የአገር ችግር ውስጥ ገብቶ ፖለቲካዊ ቀውሱን ለመፍታት በሽምግልና በአስታራቂነት ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚያስደንቀውና የአገርና የሕዝብ ፍርቅና ክብር ያጎናፀፈው ሌላው ውበቱና ድምቀቱ ነው፡፡
ኃይሌ ከዚህም በላይ መሄድ የነቃና የተጋ ፖለቲካ ውስጥ መግባት መብቱ ነው፡፡ በሚሳተፍበትና በሚታወቅበት አትሌትነቱም ውስጥ ሆኖ ፖለቲካዊ መብቱን መጠቀም ይችላል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ግን በእውቀት ላይ ተመስርቶ ግራ ቀኙን አገላብጦ አይቶ መሆን ይገባዋል፡፡ ሌላው ቢቀር ወይም ሁሌምና ሁሉም የሚያውቀው ሌላ መድረክ እንኳን "እያዩ ነው መውደድ እያስተነተኑ. . ". "አይቶ ነው ለይቶ ነው መውደድ" ይባላል፡፡
ይህን ሁሉ ከቁጥር አስገብቶ አዕምሮ የማመዛዘንን ሕግ ተከትሎ እሚደርስበት መደምደሚያ ላይ ደረሰ፣ ትክክለኛ የሚባል አቋም መውሰድም ብቻውን በቂ አይደለም፡ እውነት ላይ የተመሰረተ እና በትክክለኛ መንገድ የተገኘ መደምደሚያ ይዞ በዚያ መሰረት መረማመድ ተገቢ ነው ወይ? Wisdom አለው ወይ? ብሎ መጠየቁ ያስፈልጋል፡፡ እንዲያውም ሆነ፣ ትክክለኛ ነው ብቻ ሳይሆን ጥበበኛ (ዋይዝ) እርምጃ ነው ብለው ያረጋገጡት ነገርም የሚያስከፍለው ዋጋ እንዳለው ማወቅ ይገባል፡፡ ስለሚያስከፍለው ዋጋ የማወራው በመደበኛ አሰራርና በየትኛውም (የለየለት ፋሽስት ካልሆነ በስተቀር) አገር ዋጋው ውድ ነው አደገኛ ነው ብዬ አይደለም፡፡
በዚህ ረገድ በኦሊምፒክስ ንቅናቄ ውስጥም ሆነ በየትኛውም የአገር ስፖርት የአንድ ስፖርት አሀድ፣ ክለብ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ የትኛውም አትሌት በኦሊምፒክ እንቅስቃሴ የሚሳተፈው በክለቡ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አማካኝነት ነው፡፡ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴው የሚያውቀው አንድ አትሌት ምንም ያህል ብርቅና ድንቅ ቢሆን የዓለም የኦሊምፒክ ንቅናቄ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ የሚችለው ከስር ከመሰረቱ የዚህ ንቅናቄ መነሻና መወጣጫ በሆነው በክለቡ አማካኝነት ነው፡፡
ጉዳዩን ባጭሩ ለማሳየት የስፖርት ክለብ፣ ብሔራዊ የስፖርት ፌዴሬሽን ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የስፖርት ማኅበሮች ናቸው፡፡ በማኅበር የመደራጀት የአንድ ማኅበር አባል የመሆን መብት የማኅበሩን የአባልነት ቅድመ ሁኔታና መመዘኛ ለሚያሟላ ሁሉ ክፍት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ የማኅበር አባል መሆን የሚያስከትለው ግዴታ እንዳለ ሁሉ የማኅበር አባልነትንም አልፈልግም ማለት ያንኑ ያህል አቻ መብት ነው፡፡
ከስፖርት አኳያ በተለይም ከምንመለከተው ጉዳይ ጋር በተያያዘ በየትኛውም የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ውስጥ የመሳተፍ የአንድ አገር መብት ተፈፃሚ የሚሆነው ይኸው እያንዳንዱን አገር የመወከል ብቸኛና ሌላ አካል የማይጋራው የውክልና ሥልጣን ባለው በየአገሩ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የእያንዳንዱ አገር የኦሊምፒክ ብሔራዊ ኮሚቴ አትሌቶችን በመላክ በኦሊምፒያድ ጌሞች የመሳተፍ ግዴታ አለበት፡፡
የእያንዳንዱ አገር አግባብ ያላቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሚያቀርቧቸውን አትሌቶች አይቶና መዝኖ የሚመርጠውም ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ነው፡፡ በዚህ መካከልና መመዘኛውን ካለፉ በኋላ አልሳተፍም ማለት መብት ቢሆንም የሚያስከትለው ግዴታና አንደምታ መኖሩን አለመዘንጋት ከጥበብ መጀመሪያነት በፊት ያለ ተራ ነገር ነው፡፡
እስከ አሁን በምናውቀውና እየተለዋወጠ በሚቀርበው መግለጫ መሰረት ሻለቃ ኃይሌ የ2008ቱን ኦሊምፒክ አልካፈልም አለ የተባለው በቻይና የአየር ብክለት ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ የቻይና የአየር ብክለት ሲባል እንደ ግለሰብ ሯጭ አይመቸኝም ለጤናዬ አይስማማኝም ነው? ወይስ ፖለቲካዊ አቋም ነው? ፖለቲካዊ አቋም ከሆነ፣ ቻይና የኪዮቱን ፕሮቶኮል ባለ መፈረሟ ነው ከተባለ ከመጀመሪያው የበለጠ ልዩ ጥንቃቄና ጥበብ የሚያስፈልገው እርምጃ ነው፡፡ የቻይና ፖለቲካዊ እንከንና ህመም ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የቲቤት፣ የታይዋን የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችም አሉ፡፡ በእነዚህ ላይ ሁሉ ትክክለኛውን ጉዳይ ማወቅ በዚያም ላይ ጥበብ የተሞላው አቋም ወስዶ ይለይለት ማለት ይቻላል ተገቢም ነው፡፡ ኃይሌም ሆነ ሌሎች ሰዎች ይህንን ሁሉ ፈተና የተወጡት አይመስለኝም፡፡
በኃይሌ በኩል በተለይ ይበልጥ አያደረ ብዥታው እያየለ፣ አቋሙ እየተለዋወጠና እየተለሳለሰ ቀስ እያለም ዝምታ ውስጥ እየተዋጠና ድምጽ እየጠፋ የመጣው አንዱ በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኃይሌ "ታላቅ አትሌት ብቻ ሳይሆን ታላቅ ሰው" መሆኑን አስመሰከረ ብለው ተጨማሪ ኃይልና ጉልበት እንሰጥሃለን ያሉትም የአገር ቤት ሰዎችም ጭምር ከአንድ "ነጠላ ዜማ" በላይ መልቀቅ ያልቻሉት ከሌሎች መካከል በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡
በአንድ አገር ውስጥ አንድ ከተማ በየአራት አመቱ የሚካሄደውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ለማዘጋጀት እጅግ በጣም አዳጋችና አስቸጋሪ ፉክክር ውስጥ መግባት ይህንን ማሸነፍ ብዙ ጊዜ፣ ብዙ ገንዘብ፣ ብዙ ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡ ከጊዜ አኳያ እንኳን ብንወስደው አንዳንድ ከተሞችና ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች እናዘጋጀው ብለው ለሚያመለክቱት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ማመልከቻቸውን የሚያስገቡት ከ15 ዓመት በፊት ነው፡፡ ዓለማቀፋዊው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ለብሔራዊ ኮሚቴዎች አመልካቾች እንዲወዳደሩ የግብዣ ጥሪ የሚያቀርበው ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነው፡፡ ከስምንት ዓመት ተኩል በፊት ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች የአመልካች ከተማቸውን ስም ማስተላለፍ አለባቸው፡፡ የዓለማቀፋዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የአንድን የኦሊምፒክ አስተናጋጅ አገር ማንነት ምርጫ አጠናቅቆ የከተማውን ስም ይፋ የሚያደርገው ከሰባት ዓመት በፊት ነው፡፡ ቤጅንግ ቻይና ያለፈችው በዚህ ሥርዓት ውስጥ አልፋ ነው፡፡
ከራሱ ከኦሊምፒክስ ንቅናቄ መንፈስ አኳያ የ2008 የኦሊምፒክ ውድድር አስተናጋጅነት ለቻይና መሰጠቱ ትክክል ነው አይደለም የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኖ አሁን ጊዜው እየተቀረበ ሲመጣና አራት/አምስት ወር ሲቀረው የቲቤት፣ የታይዋን፣ የቻይና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ የአየር ብክለት ጉዳይ የሚነሳው አዲስ ነገር እየተፈጠረ መጥቶ ሳይሆን ምዕራቡ ዓለም በተለይም ብቻውን የቀረው ልዑል ኃያል አገር በሚያስተባብረው የገዛ ራሱ ጥቅም አልፎ በሚመራው ጉዳይ ላይ በመመስረት ነው፡፡ ቻይና እና ሕንድ አንድ የማይናቁ አገሮች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ቻይናን የሚጋተሩበት ቅዳሴው አልቆባቸው ቀረርቶ ያከሉበትን እነዚህን ጥቅም ያወራቸውን አድናቂዎች መከተል እጅግ ጥበብ ያንሰዋል፤ ጥበብ ይጎድለዋል የሚባለው የየትኛውም አገር የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሌላው አገር ጉዳይና ደንታ አይደለም ከሚል በቀር "ፍልስፍና" ላይ በመመስረት ቻይና ውስጥ ችግር የለም ከሚል መነሻ አይደለም፡፡
የምዕራባውያኑ የተለያየና አባይ መሳፈሪያ ቁምና ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በቻይናም ሆነ የዚምባብዌ ጉዳይ ላይ አቋም ለመውሰድ ቻይናም ሆነች ዚምባብዌ ያለውን ችግር ብቻ ሳይሆን በቻይናና በዚምባብዌ ላይ የሚረባረቡትን አስተባባሪዎችና መሪዎች ጥቅምና ፍላጎት (ሞቲቭ) መመርመር ያስፈልጋል፡፡ አንዲት "ጥቅም" ብቻ ነጥሎና አንጠልጥሎ አቋመ መውሰድ ተገቢ አይደለም ብቻ ሳይሆን ትክክልም አይደለም፡፡ ለምሳሌ መንግሥቱ ኃይለማርያም መደበቂያ መሸሸጊያና መጠጊያ እንዲያጣ ከመመኘት አኳያ አለዚያም በአንጻሩ እሱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ከሚል ስጋት አንጻር ብቻ የታጠረና የታወረ ፍላጎት ፀረ-ሙጋቤ ወይም አፍቃሪ ሙጋቤ ቢያደርገን ይህ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ አቋም በጭራሽ ሊሆን አይችልም፡፡
ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ "በቀደደው" የገቡ እንደሆኑ ያለ አግባብና ያለቦታው የሚወራላቸው የአቴንስ፣ የለንደን፣ የፓሪስና የሰንፍራንሲስኮ ተቃዋሚች እውነት የላቸውም፡፡ በእርግጥ አይባሉም፡፡ በአገራችን ደረጃ አቋም ለመውሰድ ግን አሁንም "አስቦ ነው ለይቶ ነው መውደድ. . ". ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የአገራችን የመንግሥት ሚዲያ የእነዚህ ከተሞች ተቃውሞ "የሚያንፀባርቀው አቋም" እጅግ በጣም (ከተለያየ አቅጣጫ) የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ዜና ማለት ዜና ነው፡፡ አቋም አይደለም፡፡ ዜና ውስጥ ተደብቆ የምንሰማውን አቋም በግልጽ አውጥቶ ኦሊምፒክን መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በመሪ ደረጃ በመግቢያው ስነስርዓት ላይ ትገኛለች ማለት ነውር አይደለም፡፡ በ1980 ላይ የሞስኮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ በሆነበት ወቅት የምዕራቡ ዓለም አልሳተፍም ብሎ የመረጠውና የተሳተፊ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ቁጥር ወደ 80 ዝቅ ያለው ሶቭየት ኅብረት አፍጋኒስታንን ስለወረረች ነበር፡፡ አፍጋኒስታን ዛሬ በአሜሪካ ሙሉ ጦር ቁጥጥር ስር ነች፡፡ ኢራቅም ተይዛለች፡፡ ዋንታናሞ የሰብአዊ ጥሰቶች ሁሉ መገለጫ ነው፡፡
እንደ ማንም ዜጋ፣ እንደየትኛውም ሰው አቋም በአንድ አትሌት ወይም ሌላ ሰው ከመብትና ከነፃነት በመነጨ ስሜትና እምነት የተገለፀ አስተያየት ከቻይና ወይም ከሌላ አገር መንግሥት ወይም ባለሥልጣን ጋር እንዳያጣላን ብሎ መስጋት ነገር ካለ መድሃኒቱ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት የአገራችን ሕግ ደንብና ወግ መሆኑን መንገር፣ ይህንንም በተግባር ማሳየት ወዲያውም ከተባለው አገር የተሻለና የበጠለ መሆናችንን በመግለጽ አማካኝነት በሚናገሩት መደናገጥና መሸማቀቅ አይደለም፡፡
አቴንስ፣ ለንደን፡ ፓሪስና ሳንፍራንሲስኮ የሆነውንና የዓለም ዜና ሆኖ ቻይና ውስጥ ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ሊደበቅ ያልቻለውን ግርግር ከዜናችን ውስጥ ቆርጦ ማውጣት፣ እንደሌለ አድርጎ መዘገብ ሌላ የዜና ዘገባ ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል፡፡ መተዛዘብን ያስከትላል፡፡ ስለዚህም ያስገምታል እንጂ በሌላ ሁኔታና በይፋ ልንገልፀው የምንችለውን "የትግል አጋር"ነት አያጠናክርም፡፡ |