| የሃይል እጥረቱ ለምርት... |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
|
የሃይል እጥረቱ ለምርት መስተጓጉልና ለወጪ እየዳረገ ነው
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የኤሌክትሪክ ሃይል በፈረቃ እንዲሰራጭ በማድረጉ የማምረቻ ተቋማት የምርት መጠን እንዲቀንስና አንዳንድ ኩባንያዎችን ደግሞ ለተጨማሪ ወጪ ዳርጓቸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ካነጋገርናቸው መካከል የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ይግዛው አስፋው እንደገለፁት፣ “ችግሩ የሁሉም ሆኗል፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪውንም ሆነ ሌሎች ሃይልን በፈረቃ እንዲያገኙ የተደረጉ ኢንዱስትሪዎች ሁሉ ማምረት የሚገባቸውን ያህል ሊያመርቱ አያስችላቸውም፡፡ እንዲህ ያለ የሃይል መቋረጥ ሲያጋጥም የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ችግር ሲከሰት ግን ቀድሞ ይነገረንና እንድንዘጋጅ ይደረግ ነበር፡፡ አሁን ግን ድንገተኛ መሆኑም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆኗል...” ባይ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ሀይል በፈረቃ እንዲከፋፈል ሲደረግ ለቆዳ ኢንዱስትሪው ሃይል እንዳይቋረጥ ይደረግ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ይግዛው፣ ዘንድሮ ግን በተለየ መልኩ ምንም አይነት መረጃ ሳያገኙ ፋብሪካዎቹ በፈረቃ እንዲሰሩ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉና ጄኔሬተር ያላቸውም ቢሆኑ ከጀኔሬተር የሚያገኙት ሃይል አንዳንድ መቆም የሌለባቸውን መሳሪያዎች ከማንቀሳቀስ ባለፈ ሙሉ ምርት ሊያመርቱ አቶ ይግዛው ጠቁመዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የቆዳ ፋብሪካዎች ምርት በአብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ በመሆኑ ብዙዎቹ አምራችና ላኪ ፋብሪካዎች ምርታቸውን አምርተው የሚያስረክቡበትን ቀን በማስታወቅ ውል የፈፀሙ በመሆኑ በሃይል እጥረቱ ሳቢያ ስምምነቶች አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል አቶ ይግዛው ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ በወቅቱ ምርቱን አለማድረሱ አገሪቱ ልታገኝ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ከማድረጉም በላይ በወቅቱ ምርቱ ያልቀረበለት ኩባንያም ስምምነቱን ከመሰረዝ አልፎ ምርት ለማቅረብ የተስማማውን ፋብሪካ ሊያስቀጣ እንደሚችልም ተገል..ል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሃይል እጥረቱ ሳቢያ ፋብሪካዎች እየገጠማቸው ያለውን ችግርና በቆዳ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች የሃይል እጥረት ምን ያህል ምርት እንዳስቀረባቸው የሚያሳይ መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን ያስረዱት አቶ ይግዛው የሃይል አቅርቦቱ ችግር መጠነ ሰፊ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የሚደርሱ የንግድ ድርጅቶች የሃይል እጥረቱ በገበያቸው ላይ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ወሎ ሰፈር አካባቢ ያነጋገርናቸው የአነስተኛ ካፌ ባለቤት መብራት በሌለ ቀን ከቡና ሻይና ከመሣሠሉት ያገኙት የነበረው 120 ብር እንዲቀርባቸው አድርጓል፡፡ የኤሌክትሪክ በሌለበት ሰዓት ሻይ በቡታጋዝ አፍልተው በፔርሙዝ ለማቅረብ የተገዱና ከዚህ የሚገኘው ሽያጭም እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ የሃይል እጥረቱን ለተጨማሪ ወጪዎች ከዳረጋቸው መስሪያ ቤቶች መካከል አንዱ የባንክ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ባንኮች በአሁኑ ሰዓት በኔትዎርክ የተገናኙና አገልግሎታቸውም ኮምፒውተራይዝድ በመሆኑ በጄኔሬተር መጠቀም ግድ እየሆነባቸው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የህብረት ባንክ አንድ የሥራ ሃላፊ የሃይል እጥረቱና ኤሌክትሪክ በፈረቃ እንዲደርሰን መደረጉ ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረጋቸው ያመለክታሉ፡፡ እንደ ሃላፊው ገለፃ ከሆነ ባንኩ እያንዳንዱ ቅርንጫፎች በኔትዎርክ የተሣሠሩ በመሆኑና አገልግሎቱም ያለ ኤሌክትሪክ ሃይል ስለማይሰራ ምናልባት የኤሌክትሪክ መቋረጥ ቢከሰት አገልግሎቱ እንዳይሰተጓጎል ለብዙዎቹ ቅርንጫፎች ጄኔሬተር ገዝተን ተክለናል፡፡ በተለይ የኔትዎርኩን የሚያንቀሳቅሰው ዋናው ሰርቨር በሚገኝበት የዋናው መስሪያ ቤት ከፍተኛ ሃይል የሚያመነጭ ጄኔሬተር ተተክሏል፡፡ ሆኖም ግን አሁን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሲደጋገም ሀይል በፈረቃ እንዲሆን ሲደረግ ለሁሉም ቅርንጫፎች ጄኔሬተር በማስፈለጉ ለሁሉም ቅርንጫፎች ገዝተው መትከላቸውን ለዚህም ቀላል የማይባል ወጪ ማውጣታችንን እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡ ለነዚህ ጄኔሬተሮችም ለእያንዳንዳቸው በቀን ከ300 ብር ያላነሰ ነዳጅ ስለሚያስፈልግ ለነዳጅ የሚወጣው ወጪም በቀላሉ እንደማይገመትም አመልክተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የሃይል እጥረቱን የጄኔሬተር ገበያ ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡ ፒያሣ አካባቢ ያሉ የኮንስትራክሽንና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች መሸጫዎች የጄኔሬተር ገዥዎችና ተጠቃሚዎች መበራከታቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በጄኔሬተር ግዥ ላይ ያነጋገርናቸው የአንድ መስሪያ ቤት ግዢ ሠራተኛ እንደገለፁት ደግሞ የሃይል እጥረቱን ተከትሎ የጄኔሬተር ዋጋ ከፍ ማለቱን ይገልፃሉ፡፡ ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም የገዙዋቸውና ጉልበታቸውም ሆነ የጄኔሬተሩ አይነት ተመሣሣይ የሆነ ምርት አሁን ዋጋው በትንሹ ከ20 በመቶ በላይ መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡ ከጄኔሬተር ገበያ ጋር በተያያዘ ተዘዋውረን የተመለከትናቸው የጄኔሬተር መሸጫ መደብሮች ሽያጫቸው አድጓል፡፡ በሁለት ወር ውስጥ አንድ ጄኔሬተር ሳይሸጡ የቆዩ መደብሮች አሁን በሁለት ሣምንት ልዩነት ውስጥ ሦስትና አራት ጄኔሬተሮች መሸጣቸውን ይገልፃሉ፡፡ ቢገዙም ባይገዙም የጄኔሬተር ዋጋ የመጠየቁ ቁጥር ከሰሞኑ በርክቷል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |