| ከሽልማት ሥራ ይቅደም |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
|
በአሁኑ ሰዓት የእግር ኳሳችን ሞት አፋፍ ላይ ሆኖ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰማ ባለበት፣ በየክልሎቹ ዘመናዊ ስታዲየም ለመስራት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንደተመደበ በዜና ማሰራጫዎች እየሰማን ነው፡፡ የስታዲየሞቹ ግንባታ መጠናቀቅና አገልግሎት መስጠት መጀመር ለእግር ኳሳችን ትንሳኤ ሊሆን ስለሚችል መሠራታቸው ጥሩ ነው፡፡ ለስታዲየሞቹ ማሰሪያ የሚሆን ገንዘብ ከልማት ድርጅቶች፣ ከባለሀብቶችና ከድኃው ሕዝብ በመሆኑ ጥሩ ነው፡፡
በመቀሌ ዘመናዊ ስታዲየም እየተሠራ ነው፡፡ ስታዲየሙ 3ዐ ሺህ ተመልካች እንደሚይዝና ከ8ዐ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ይገመታል፡፡ ለስታዲየሙ ማሰሪያ ገንዘብ ለማሰባሰብ በመቀሌና በአዲስ አበባ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን ከጀመረ ከራርሟል፡፡ በመቀሌ የሚገኙ የተወሰኑ የመንግሥት ቢሮ ሠራተኞች ለግንባታው የሚሆን ገንዘብ ከደመወዛቸው ተቆርጦ እንዲወሰድ ፈቃደኝነታቸውን ገልፀው ነበር፡፡ ነገር ግን የስታዲየሙ ግንባታ አሁንም ድረስ አልተጀመረም፡፡ ሼክ መሐመድ አልአሙዲ በየካቲት ወር መቀሌ መጥተው በነበረ ጊዜ 5ዐ ሚሊዮን ብር እንደሰጡ በቴሌቪዥን መስኮት አይተናል፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ በሰጡ ማግስት ምንም ሥራ ባልተሰራበት የገንዘብ እጥረት አጋጠመን ማለቱ ምን ይሆን መልእክቱ? (ኤልያስ ሚካኤል፣ ከመቀሌ) አስተማማኝ የሆነ የኃይል አቅርቦት አለመኖር ለኢንቨስትመንት ሳንካ ባለፈው እሑድ በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ ተሟገት ገጽ “ያልታሰቡ ነገሮች እስከመቼ ሲጠርጉን ይኖራሉ” በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሁፍ ለአስተያየቴ መነሻ ሆኖኛል፡፡ ከጽሁፉ እንደተረዳሁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚያስመዘግቡትን ፈጣን ዕድገት ያገናዘበ ዕቅድ አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕቅድ ቢኖረውማ የአሁኑ ኢንዱስትሪያዎች ብዛት በዚህ ደረጃ ይሆናሉ ብሎ ባሰበና ለዚህም የሚውል የኃይል ፍላጎት ለማሟላት በቻለ ነበር፡፡ ኢንቨስትመንት እያደገ ሲሄድ በዚያው መጠንም ኃይል እንደሚያስፈልግ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ዓይነቱ ፈጣን ዕድገትና ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ዕቅድ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገራችን ለመሳብ መሟላትና መመቻቸት ከሚገባቸው በርካታ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የማይቆራረጥና ቀጣይነቱ አስተማማኝ የሆነ የኃይል አቅርቦት መኖርን ማረጋገጥ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ አሁን ከሚያካሂደው እንቅስቃሴ አንፃር ግን እንኳንስ የውጭ ባለሀብት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሙዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ይበረታታሉ ማለት አያስችልም፡፡ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አለመኖር በኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለሚያሳድር ኮርፖሬሽኑ የቤት ሥራውን ይሥራ፡፡ (ከበደ አብርሃም፣ ከካዛንቺስ) ውሳኔ የመስጠት ድክመት በኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት ቦታ የተቀመጡ ሰዎች ምን ያህል ውሣኔ ለመስጠት በራስ መተማመን እንደሚጐድላቸው ታዝቤያለሁ፡፡ ጥቃቅን የሆኑ የሠራተኛ መብቶች እንኳን ሲጠየቁ እከሌ ጋ ሂድ/ሂጂ ከማለት ውጭ በራሳቸው አይወስኑም፡፡ ከጥቂቶቹ በስተቀር፡፡ በመሆኑም ሠራተኛው ከመዋቅር ለውጡ በኋላ መብቱን ለመጠየቅ ሲፈራና ተስፋ ሲቆርጥ ይታያል፡፡ ኃላፊዎቹ የመወሰን ችግር ያለባቸው በደንበኞች አገልግሎት ላይም ነው፡፡ ለምሳሌ በአለም አቀፍ የፖስታ ስምምነት መሠረት ዕቃ የጠፋበት ደንበኛ ካሣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያገኛል፡፡ እኛ መሥሪያ ቤት ግን ደንበኛው ከወራት በላይ ይመላለሳል፡፡ ዕቃው የጠፋበት ሀገር ፖስታ ቤት ፍቃደኛ መሆኑን ከገለፀ ብቻ ነው ካሳ የሚከፈለው፡፡ ከዚያ ውጭ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ከመፃፃፍ የዘለለ እርምጃ አይወስድም፡፡ በሌሎች ሀገሮች ግን ቀጥታ ሂሳቡን ቆርጠው ለደምበኛ ካሳ በመስጠት ሂሳቡን እንድናወራርድ ነው ደብዳቤ የሚልኩት፡፡ በዚህ የደንበኞች አያያዝ ድክመት ብዙዎቹ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡ በብዛት የታሸገ ዕቃ የሚልኩ ደንበኞች በሌሎች ድርጅቶች መጠቀም ጀምረዋል፡፡ ድርጅቱ ወደ ኪሣራ ከመሄዱ በፊት አሠራሩን ማስተካከል ይኖርበታል፡፡ (ኤስ.ዋይ፣ ከድርጅቱ ሠራተኞች አንዱ) እውነትን የመናገር ድፍረት ማጣት ሰሞኑን ትኩረት የሳበው የኦሊምፒክ ችቦ የቅብብል ሩጫ ነው፡፡ በተለያዩ ከተሞች በሚያደርገው ጉዞ እክል እያጋጠመው መሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ተዘግቧል፡፡ በሪፖርተር ጋዜጣም አንብበናል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በስፖርት ኘሮግራሙም ሆነ በዜና እወጃው ስለ ቤጂንግ ኦሊምፒክ ችቦ ጉዞ የተሟላ መረጃ እያስተላለፈ አይደለም፡፡ በለንደንና በፓሪስ እንዲሁም በሳንፍራንሲስኮ ከተሞች ችቦው ሲገባ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ያሰራጨው ዜና ከእውነታው የራቀ ነው፡፡ ቻይና በቲቤት ላይ እያደረሰች ያለውን ጫና አስመልክቶ ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጥሞ እያለ አዛብቶ ማቅረብ ከመያ ሥነ ምግባር ውጭ ነው፡፡ (ትርሲት ዓለሙ፣ ከፒያሳ) ግልፅ ልዩነትን መፍጠር በደል ነው በአገራችን የተከሰተው የኑሮ ውድነት በተለይም በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ተፅእኖ በመጠኑም ቢሆን ለመከላከል መንግሥት አቅምን ያገናዘበ የደመወዝ ማስተካከያ አድርጓል፡፡ የደመወዝ ማስተካከያው በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ የሚካተቱም ሆኑ የደመወዝ ጭማሪውን ለሠራተኞቻቸው በፈቀዱ ለምሳሌ እንደ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በመሳሰሉት የተሰጠው ለሁሉም ቋሚ ሠራተኞች ነው፡፡ አንዳንድ ተቋማት ከሥራ ለቀነሷቸው ሆኖም የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ደመወዝ ለሚከፈላቸው ሠራተኞቻቸው ጭምር ጭማሪውን መስጠታቸው ይታወቃል፡፡ ማንኛውም ሠራተኛ አሁን በሚከፈለው ደመወዝ ያለውን የኑሮ ውድነት ሊቋቋም እንደማይችል ታስቦ ድጋፍ ለማድረግ በመታቀዱ ነው፡፡ ይህ እቅድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን ተጥሷል፡፡ ንግድ ባንኩ የኑሮ ውድነት ማካካሻውን ለሠራተኞቹ ሲሰጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቹ ቀደም ሲል በባንኩ በተደረገው የመዋቅር ማሻሻያ መሠረት ሲሰሩባቸው የነበሩ የሥራ መደቦች ሲታጠፉ በያዙት መደብ አንድም ይሁን ከዚያ በላይ ዝቅ ባሉ ሥራዎች እንዲሰሩ ለተደረጉ ሠራተኞች የኑሮ ውድነት ማስተካከያ ጭማሪውን አልሰጠም፡፡ ይህ ድርጊት መንግሥት ለኑሮ ውድነት መቋቋሚያ እንዲሆን ሠራተኛውን ለመታደግ የተከተለውን መርህ የሚጋፉ ይመስለኛል፡፡ ባንኩ የኑሮ ውድነት ማካካሻ ማለት አመት እየተቆጠረ የሚሰጥ የደመወዝ እርከን ወይም ልዩ ጥቅም አለመሆኑን አልተገነዘቡም፡፡ ማካካሻውን ያላገኙ ሠራተኞቹ ቢራቡ፣ ቢቸገሩ፣ የበይ ተመልካች ቢሆኑ ግድ እንደሌለው፣ በተለይ አመራሩ ለራሱ ካገኘ ለሌላው የማይጨነቅ መሆኑን ያሳያል፡፡ (ከባንኩ ሠራተኞች) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |