| "የእርምት እርምጃ ሲወሰድ፣... |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
|
"የእርምት እርምጃ ሲወሰድ፣ ጥፋተኛ ሲቀጣ ሕዝብ በአስተዳዳሪው ያምናል" አቶ ጅብሪል መሐመድ፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ
አቶ ጅብሪል የመጀመሪያና የመጀመሪያና ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ተወልደው ባደጉበት ባሌ ዞን ጋሰራና ጊኒር ነው፡፡ የደርግ ሥርዓት ማብቂያ ሲቃረብ ትግሉን የተቀላቀሉት አቶ ጅብሪል ከዩናይትድ ኪንግደም በርቀት ትምህርት በቢዝነስ አድሜንስትሬሽን ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ በመቀጠልም ከአሜሪካ ኢንተርናሽናል ሊደር ሺፕና ማኔጅመንት ኢንስቲቲዩት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ ሕዝብ ማገልግል የጀመሩት በቀበሌ ሊቀመንበርነት ነው፡፡ አሁን የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ በዞኑ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ አሰግድ ተፈራ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በአስተዳደሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ አገልግሎት ፈላጊ አይታይም፤ አቶ ጅብሪል፡- የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ ከመሆኔ በፊት የዞኑ የፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ ኃላፊ ነበርኩ፡፡ ሥራዬ ከሕዝብ ጋር የሚያገናኝ ስለነበር የሕብረተቡን ችግሮች ለማወቅ እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ አስተዳዳሪ ስሆን ምን መደረግ እንዳለበትና ከየት መጀመር እንደሚገባኝ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ከተሀድሶ በኋላ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነት ያለበት አሰራርን መከተል በድርጅቱም ሆነ በክልሉ መንግሥት የተያዘ አቋም በመሆኑ ይህንኑ ተግባራዊ በማድረጋችን አገልግሎት ፈላጊዎች በአስቸኳይ ስለሚስተናገዱ የአስተዳደሩ ጽሕፈት ቤት ጭር ያለ ሊመስል ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- መሬትን በሚመለከት ባለጉዳይ እያስተናገዳችሁ እንዴት ጭር ሊል ይችላል? አቶ ጅብሪል፡- ለማንኛውም ጥያቄ መልስ ለመስጠት የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለ፡፡ ባለሀብቶች መጥተው ከደቂቃዎች በላይ እንዲቀመጡ አናደርግም፡፡ ወዲያውኑ ይስተናገዳሉ፡፡ አሰራሩ ወጥነት ያለው ስለሆነ ፀሐፊዎች ሳይቀር እንግዳ በማስተናገዱ በኩል ቀጥተኛ ተሳታፊ ናቸው፡፡ የመሬት ጠያቂ በርካታ ቢሆንም ቀልጣፋ ምላሽ ስለምንሰጥ መጨናነቅ የለም፡፡ ሪፖርተር፡- በአብዛኛው ባለጉዳይን ከቢሮ ውጪ ኮሪደር ላይ ያስተናግዳሉ፡፡ አቶ ጅብሪል፡- እድገቴ ገጠር ነው፡፡ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ፡፡ አሁን አስተዳዳሪ ብሆንም ሁለት እርምጃ ወደኋላ ብመለስ ተመልሼ የምገባው እዚሁ አርሶ አደር ጉያ ውስጥ ነው፡፡ መነሻዬን መርሳት አልፈልግም፡፡ ድርጅቴ አምኖብኝ ሕዝብ አስተዳድር ሲለኝ የተቀበልኩት የድርጅቱ ዓላማና ፍላጎት አለ፡፡ ይህንን ዓላማ መሰረት በማድረግ ለመስራት ስስማማ አርሶ አደሩንና ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ያለ አድልዎ ማገልገል እንዳለብኝ አምኜና ታምኜ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለአቤቱታ የሚመጡ አርሶአደሮችን ማየት አልፈልግም፡፡ ከመጡም በአጭር ጊዜ ውስጥ መስተናገድ አለባቸው፡፡ ቢሮ ተቀምጩ በየተራ በፀሐፊዬ በኩል ማስተናገድ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ኮሪደር ላይ መስራት እወዳለሁ፡፡ ምንም ምስጢር ስለሌለ በአደባባይ እያዳመጥኩ በአደባባይ አስፈላጊውን አደርጋለሁ፡፡ ዋናው ትልቁ ጉዳይ ግን አርሶ አደሮቹ ለአቤቱታ ሳይመጡ ባሉበት ጉዳያቸው እንዲያልቅ የሚያስችል ስርዓት መፍጠሩ ላይ መሰራት ስላለበት በዚህ በኩል እየሰራን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- እርስዎን ከማነጋገሬ ከደቂቃዎች በፊት ባለጉዳዮች ነጠላ መሬት አንጥፈው እግርዎት ስር ወድቀው፣ እርስዎም ተንበርክከው ነበር፤ አቶ ጅብሪል፡- የሞጆ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ በቀድሞው አውራ ጎዳና ሲሰሩ ቆይተው ጡረታ ወጥተዋል፡፡ የሰማንያ፣ የሰባ ዓመት አንጋፋ ናቸው፡፡ የሚኖሩት ቀደም ሲል በተሰጣቸው ካምፕ ውስጥ ነበር፡፡ የከተማው አስተዳደር ቦታው ይፈለጋል በሚል ቦታውን ልቀቁ አላቸውና ለአቤቱታ እኔ ዘንድ መጡ፡፡ ተበደልኩ ያሉኝን ነገሩኝ፡፡ በጣም ተጨንቀው ነበር፡፡ ጡረተኛ ናቸው፡፡ እድሜያቸው ገፍቷል፡፡ እነዚህን ሰዎች ከቤት ማስወጣት አግባብ ባለመሆኑ ቦታው ለሌላ ሥራ ቢፈለግ እንኳ እንደ ዜጋ መስተናገድ ስላለባቸው በበነገታው ሞጆ በመሄድ መፍትሄ ስነግራቸው አለቀሱ፡፡ ነጠላቸውን አነጠፉ... ሪፖርተር፡- ሞጆ ለመሄድ የወሰኑት ለምንድነው? አቶ ጅብሪል፡- አቤቱታ አቅራቢዎቹ ደካማ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ በጡረታ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ በሁሉም መልኩ እኔ ከእነሱ እሻላለሁ፡፡ እነሱ ከሚመላለሱ እኔ እዚያ ብሄድ ይሻላል፡፡ መንግሥት የሰጠኝ ተሽከርካሪኝ አለኝ፡፡ በዚህ ላይ ጥያቄያቸው የመጠለያ በመሆኑ ለጉዳያቸው ትኩረት መስጠት ስለነበረብኝ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር፣ ሕብረተሰብ የማገልገል ኃላፊነት ማለት በዚህ መልኩ የሚገለፅ ይመስለኛል፡፡ ሪፖርተር፡- በባለጉዳዮች መካከል የሚቀመጡት ለምንድነው? አቶ ጅብሪል፡- ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡ ባለጉዳዮች ከሚመጡበት ዋና ጉዳያቸው ውጪ አጠገባቸው ለተቀመጠ ስለበደላቸው በነፃነት ይናገራሉ፡፡ አስተዳደሩ ችግር ካለበት ይተቻሉ፡፡ ያስቀየማቸው ሠራተኛ ካለ ይወቅሳሉ፡፡ አንዳንዴ መካከላቸው የምቀመጠው ለማዳመጥ ነው፡፡ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ልምዱ አነስተኛ በመሆኑ ባለጉዳዮች በነፃነት አይናገሩም፡፡ በነፃነት ከተናገሩ የሚቀጡ የሚመስላቸው አሉ፡፡ እንደ ባለጉዳይ ጉዳያቸውን ካጫወቱኝ በኋላ በአስተዳዳሪነቴ ሳነጋግራቸው.... ሪፖርተር፡- ኃላፊነትን ደብቆ ባለጉዳዮችን ማዳመጥ ስሌላ አይመስልም? አቶ ጅብሪል፡- ማንኛውም ዜጋ የመሰለውን በአስተዳዳሪዎች ፊት የመናገር መብት አለው፡፡ ይህን መብት ሕዝብ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ እኔ ባለጉዳይ መስዬ የማዳምጠው የሰዎችን የግል ጉዳይ አይደለም፡፡ ለስራዬ የማይጠቅም ነገር ከተነሳ ማንነቴን ገልጩ እነሳለሁ፡፡ ዋናው አላማዬ ግን... ሪፖርተር፡- ጠቃሚ ጉዳይ አግኝተው ያውቃሉ? አቶ ጅብሪል፡- አስተዳደሩ ራሱን እንዲመረምር፣ በስሩ ያሉትን የአስተዳደሩ አካላት እንዲከታተል የሚያነቁ፣ የሚጠቁሙ ጉዳዮች ያጋጥሙኛል፡፡ በዚያ መነሻ ራሳችንን እናያለን፣ እናጠራለን፡፡ የእርምት እርምጃ ሲወሰድ፣ ጥፋተኛ ሲቀጣ ሕዝብ በአስተዳዳሪው ያምናል፣ በድርጅቱ ይመካል፡፡ በሚመራው መንግሥት ላይ መተማመንን ያሳድራል፡፡ ከተሀድሶ በኋላ በኦሮሚያ ቁርጠኛ አቋም የተያዘበትና የክልሉን ፕሬዚዳንት ጨምሮ በጥብቅ ክትትል የሚያደርጉበት የመልካም አስተዳደርና የልማት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ማለት ገና ተጀመረ እንጂ ሙሉ በሙሉ መልካም አስተዳደር ሰፈነ ማለት አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ የአስተዳደር ችግር ያለበት፣ ሙስና የሰፈነበት፣ ሕገወጥ ተግባራት የሚፈፅሙበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለፅ ነበር፡፡ እርስዎ አስተዳዳሪ ሲሆኑ መጀመሪያ ያደረጉት ምን ነበር? አቶ ጅብሪል፡- ወደ ኃላፈነቱ ስመጣ ይዤ የመጣሁት የድርጅቴን ኦህዴድ አቋምና ውስጣዊ ማንነቴን ነው፡፡ ከዚያም በዞኑ ውስጥ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ የመለየት ሥራ መሥራት ጀመርን፡፡ ያገኘናቸውን ችግሮች እንዴት እንፍታ በሚለው ዙሪያ ሠራን፡፡ የመጀመሪያ እርምጃ የነበሩትን መዋቅሮች በመቀየር ሕዝባዊ እንዲሆኑ ማድረግ ነበር፡፡ ሪፖርተር፡- የመዋቅር ችግር ብቻ ነበር? አቶ ጅብሪል፡- የነበረው መዋቅር ብቻ ሳይሆን የአቅም፣ የአሰራርና የቁርጠኛነት ችግር ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር በዋናነት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥራ ሲሰራ ሕግን የሚጥሱ አሰራሮችንና ግለሰቦችን በመቃወም ነበር... ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ከሕግ የበላይነት ጋር በተያያዘ የቀበሌና የጎጥ አመራሮች በደል ይፈፅማሉ የሚል አቤቱታ አለ፣ አቶ ጅብሪል፡- ሕዝብ የልማት ጥያቄ አለው፡፡ ሕዝብ የሕግ የበላይነት እንዲከበርለት ይፈልጋል፡፡ እኛ ደግሞ ለውጥ ለማምጣት ሕዝቡ እንዴት አብሮን ሊሰለፍ ይችላል? የሚለውን ይዘን ወደ ሕብረተሰቡ ገባን፡፡ ሕዝቡን በየደረጃው ስናነጋግር የተባሉት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ሕዝብ ስታነጋግሩ አንኳር ችግር ሆኖ የቀረበውና ኦህዴድ ራሱን ሲገመግም ዋና ችግር ያለው ምንድነው? አቶ ጅብሪል፡- በዞናችን ውስጥ የነበረው ዋንኛ ችግር የአመራር ነበር፡፡ በአመለካከትና በአቅም ደረጃ የሚፈለገውን ለውጥ የማምጣት ችሎታ አልነበረም፡፡ የዞኑን እምቅ ሀብት ሕብረተሰቡ እንዲገለገልበት የማድረግ እንቅስቃሴ በጣም ደካማ ነበር፡፡ በፓርቲ ደረጃም ያየነው ይኸው ነበር፡፡ የአመለካከት፣ የአሰራርና የአቅም ችግር ነበር ማለት ሕዝቡ እንደሚፈልገው እየተመራ እንዳልነበረና የሚያነሳው የልማት ጥያቄም አልተመለሰለትም ነበር ማለት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በቀበሌ ገበሬ ማኅበራትና በወረዳዎች አካባቢ ብልሹ አሰራሮች እንደነበሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተጠቅሷል፤ አቶ ጅብሪል፡- አሁን ያለው አመራር የቀድሞውን አመራርና መዋቅር ስለወቀሰ ለውጥ አይመጣም፡፡ ችግር እንዳለ አስቀድሜ ገልጫለሁ፡፡ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮች አሁንም ሙሉ በሙሉ ተወግደዋል ማለት ባይቻልም መልካም ጅምር እንዳለ ይታየኛል፡፡ መልካም አስተዳደር የማስፈን ጉዳይ በአንድ ለሊት የሚሆን አይደለም፡፡ እኛም ብንሆን ቀደም ሲል ከተበላሸው አመራር የተቀዳን (የመጣን) በመሆኑ ከፍተኛ ትግል ይጠይቃል፡፡ ሪፖርተር፡- አሁን የተጀመረው የአገልግሎት አሰጣጥ በመልካም ጅምርነቱ አስተያየት ቢሰጠውም በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ነው የሚሉ አሉ፣ አቶ ጅብሪል፡- በዞናችንም ሆነ በኦሮሚያ በምሳሌነት የሚጠቀስ መልካም አስተዳደር እየታየ ነው፡፡ በዞናችን አገልግሎት አሰጣጡ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም ለውጥ አለ፡፡ በፀጥታ ዘርፍ ለውጥ አለ፡፡ በርካታ ሀብት ያለበትና ንግድ የሚንቀሳቀስበት ዞን ቢሆንም የወንጀል ድርጊቱ ቀንሷል፡፡ ከሌሎች ዞኖች ይልቅ የተሻለ ሁኔታ የሚታይበት ነው፡፡ እነዚህ ጅምር ምልክቶች በቀጣይ በስፋት ሊሰሩ ይገባል፡፡ በስፋት ሲሰሩና ወደ ተግባር ሲመነዘሩ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠሉት በጎ ጅምሮች ሕዝባዊ መሰረት እየያዙ ይሄዳሉ፡፡ አሁን ወደዚህ እየሄድን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የክልሉ መንግሥትና የመላ ድርጅቱ አቋም በመሆኑ ወደ ሕዝብ ጠልቀን መግባት ያስችለናል፡፡ ሪፖርተር፡- ከተሀድሶ በኋላ የዞኑ ሕዝብ በልማት ያገኘው ምንድነው? አቶ ጅብሪል፡- ትምህርት በ1987 ዓ.ም ሃያ በመቶ ሽፋን ነበር፡፡ በ96 አካባቢ 69 በመቶ ደረሰ፡፡ አሁን ከመቶ በላይ ሆኗል፡፡ ይህ በአንደኛ ደረጃ ነው፡፡ በከተማ አካባቢ የተገደበ የትምህርት ቤቶች ግንባታ ቀበሌና ጎጥ ድረስ ዘልቋል፡፡ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ውስን ነበር፡፡ ዛሬ በየወረዳው ከፍተኛና ፕሪፓራቶሪ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በጤናው ረገድ የሰማንያ በመቶ ሽፋን አለ፡፡ በቤተሰብ ምጣኔ ከፍተኛ ሥራ በመሰራቱ ኅብረተሰቡ በቤተሰብ ምጣኔ አቋም መያዝ የደረሰበት ደረጃ አለ፡፡ ሪፖርተር፡- ዞኑ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ተጋላጭ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ላይ ምን ሠራችሁ? አቶ ጅብሪል፡- በዞናችን በየትኛውም ክፍል እስከ ጎጥ ድረስ ከጋብቻ በፊት ወሲብ አግባብ እንዳልሆነ የታመነበት፣ ምርመራ ሳይካሄድ ጋብቻ የማይከናወንበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ እዚህ ደረጃ የተደረሰው ብዙ ተደክሞ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ግብርናውን በተመለከተስ? በቁጥር የተደገፈ ለውጥ ተመዝግቧል? አቶ ጅብሪል፡- በ1995/96 የምርት ዘመን በኩንታል 4.3 ሚሊዮን ማምረት ተችሎ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት የመስኖውን ጨምሮ 31 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጠቀሰው ዓመት በመስኖ የለማው 3ሺህ ሄክታር ነበር፡፡ አሁን 39ሺ ሄክታር ደርሷል፡፡ እቅዳችን 65 ሺህ ሄክታር ለማድረስ ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በየቀበሌው ሦስት ሶስት የግብርና ባለሙያዎች አሉ፡፡ አርሶ አደሩ የሚዘራውን በመቀየር ለኤክስፖርት የሚሆኑ ምርቶች እንዲያመርት፣ ገንዘብ ሲያገኙ ሱፐር ማርኬት በመክፈት፣ ኢንቨስትመንት ላይ እየተሳተፉ ያሉና ዘር በማባዛት ሥራ ተሰማርተው እየሰሩ ነው፡፡ ሥራ አጥነትን ለመታገል 100ሺ የሚጠጉ ወጣቶችን በማደራጀት ሥራ እንዲሰሩ የተደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዜሮ ተነስተው እስከ 1.4 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው ተፈጥረዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በየቦታው የተለያዩ ባለሥልጣኖች ሥራ አጦች ተደራጅተው ኑሯቸው ተለወጠ ማለት የተለመደ ሆኗል፤ አቶ ጅብሪል፡- በማስረጃ አስደግፎ መናገር ይቻላል፡፡ ከዜሮ ተነስተው የተደራጁ የአሸዋ አምራቾች ማኅበር አለ፡፡ በስሩ 302 ማኅበራት አሉት፡፡ የተደራጁት በዩኒየን ደረጃ ነው፡፡ ምንም የላቸውም ነበር፡፡ ዛሬ በቢሊዮን የሚቆጠር ካፒታል አላቸው፡፡ ይህ ተጨባጭ ይመስለኛል፡፡ አሸዋ፣ ብሎኬት፣ ቱቦ ያመርታሉ፣ በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና በትምህርት ቤት ግንባታ ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ለሌሎችም ተርፈዋል፡፡ እነዚህ ሥራ ስላልነበራቸው ቀደም ሲል በሰላሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ ዛሬ ግን አስተሳሰባቸው ተቀይሮ በሁለት ዓመት ውስጥ የ60 ገልባጭ መኪኖች ባለቤት ሆነዋል፡፡ በአንድ ወረዳ እስከ 10 ሚሊዮን፣ በአጠቃላይ ከነንብረታቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ይዘዋል፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ ማየት ይቻላል፡፡ ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ድርጅት እንዳቋቋሙ ይነገራል፡፡ ምን አነሳሳዎት? አቶ ጅብሪል፡- የኮንስትራክሽን ድርጅቱ እንዲቋቋም ያሰብኩት በከተሞች አካባቢ የሚነሳውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ነው፡፡ የከተሞችን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለማሟላት ብቻ ሳይሆን ገጠርና ከተማን ለማገናኘት ለሚደረገው ጥረት አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት በአክሲዮን አቋቁመናል፡፡ ከተሞች የጋራ አክሲዮን በመፍጠር ለኮንስትራክሽን የሚሆኑ መሳሪያዎች መግዛት ጀምረዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የሃሳቡ ባለቤት ማን ነው? አቶ ጅብሪል፡- የከተሞች የልማት ጥያቄ በዛ፡፡ የመንግስት አቅም ውሱን ነው፡፡ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የግድ ነው፡፡ ለግል ድርጅቶች ቢሰጥ ዋጋው ውድ ሆነ፡፡ በሌላ በኩል በአገራችን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ውሱን ነው፡፡ ዛሬ የሚነሳው የጠጠር መንገድ ጥያቄ ነው፡፡ ነገ የአስፓልት መንገድ ጥያቄ ይቀርባል፡፡ ከዚህ አንፃር ሐዋስ ኮንስትራክሽን እንዲቋቋም ሀሳቡን ለካቢኔ አቅርቤ ፀድቆ ወደ ሥራ ተገባ፡፡ ሪፖርተር፡- አሁን አቅሙ ምን ያህል ሆነ? አቶ ጅብሪል፡- ለኮንስትራክሽን የሚያስፈልጉ መሠረታዊ መሳሪያዎች ተገዝተዋል፡፡ ከፍተኛ እድገት ያስመዘግባል ብለን እናምናለን፡፡ ሪፖርተር፡- በዘርፉ የተሰማሩ የግል ኮንትራክቶች ወደውታል? አቶ ጅብሪል፡- የገበያ ጥያቄ ከሆነ በኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅም ካለ ስራው ብዙ ነው፡፡ ውድድር በሌለበት የሥራ መስክ ቅሬታ ይቀርባል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ቢኖርም በሕጋዊ መንገድ አክሲዮን አቋቁሞ መስራት የሁሉም መብት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ችግር አለ፡፡ ለምሳሌ ሞጆ በአድልዎ፣ በአማላጅ፣ በጉቦ የሚሰራበት ሁኔታ እንዳለ የሚጠቁሙ አሉ፤ አቶ ጅብሪል፡- በሞጆ ከተማ የተሻሻለ አሰራር እየታየ ነው፡፡ ተፈጠረ የተባለው ችግር በአካባቢው ያለ የመዋቅር ችግር ነው፡፡ ባለሙያዎች የዲሲፒሊን ጉድለት አለባቸው፡፡ ሪፖርተር፡- የዲሲፒሊን ግድፈት ሲሉ፤ አቶ ጅብሪል፡- በተለያየ መልክ ባለጉዳዮችን በማጉላላት፣ ጥቅማ ጥቅምን የመጠየቅ ሁኔታ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል የከተማዋ እድገትና ከተማዋን የሚመራው ሃይል አለመጣጣም አለ፡፡ ሕብረተሰቡና ማዘጋጃ ቤቱ ያላቸው ግንኙነት ጥሩ አልነበረም፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ የቀድሞውን አስተሳሰብ ይዞ የሚሄድ ስለሆነ ይህንን ችግር ለማቃለል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በቴክኒክ አካባቢ የከፋ የዲሲፒሊን ችግር ያለባቸው ተለይተው ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል ሕግ ጠብቀው የሚሰሩትን የማንቋሸሽም ሁኔታ አለ፡፡ ኅብረተሰቡን በዚህም ረገድ እያስተማርን ነው፡፡ በአብዛኛው ባለሀብት ነን የሚሉ ደላሎች በዚህ ተግባር መሰማራታቸው አሳዛኝ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ሕዝብ በማወያየት እየሰራን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በቢሾፍቱ ገበሬዎች መሬት ለባለሀብት ለመስጠት ተስማምተው ከመሬታቸው ሳይሆኑ፣ ካሳ ሳይቀበሉ ህይወታቸው ያለፈበት ሁኔታ አለ፡፡ ለአርሶ አደሮች መሬት ልዩ መታወቂያ ነው፡፡ እርስዎ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ ብለዋል፡፡ እንዲህ ያለውን በደል እንዴት ይገልጹታል? አቶ ጅብሪል፡- ኢንቨስተሮች ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ ትክክለኛ ባለሀብቶችና አቅም ሳይኖቸው መሬት ይዘው ሌላ ባለሀብት የሚያፈላልጉ ደላላ ባለሀብቶች ነን የሚሉ አሉ፡፡ ልማታዊ የሆኑትን የምናግዘውን ያህል ልማታዊ ያልሆኑትን የማመናመን ስራ መሰራት አለበት፡፡ አስካሁን ልማታዊውንና ልማታዊ ያልሆነውን ባለሀብት የመለየት ሥራ አንሰራም ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉንም ነገር በሂደት አውቀነው መለየት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ በቢሾፍቱ ተፈጠረ ስለተባለው ጉዳይ እኛም ጥፋት አለ፡፡ ኢንቨስትመንቱን መቆጣጠር የሚገባቸው ክፍሎች አሉ፡፡ በአግባቡ እንዲሰሩ አላደረግንም፡፡ መሬት ተለክቶላቸው ከተረከቡ በኋላ ካሳ የመክፈሉ ደረጃ ሲደርሱ ካሳ ሳይከፍሉ ይጠፋሉ፡፡ ሪፖርተር፡- የማን ጥፋት ነው? አቶ ጅብሪል፡- ባለሀብት ነን የሚሉት ሰዎች ተፈጥሯዊ ሁኔታና በየደረጃው ያለው አመራር ላይ ያለው ድክመት ለጥፋቱ መንገድ ከፍቷል፡፡ ከልማቱ ጥያቄ ብዛት አንፃር አጋጣሚው አንድ ቢሆንም ድርጊቱ የሚወገዝ ነው፡፡ በፀዳ አስተሳሰብ ልማት ይበልጣል በማለት መሬቱን ፈቅዶ በሰጠ ወገን ላይ እንዲህ ዓይነት ተግባር መፈፀም አግባብ አይሆንም፡፡ ለወደፊቱ ግን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዳይደገም እንሰራለን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እውነትን ተከትሎ መስራቱ ይመረጣል፡፡ ሪፖርተር፡- አርሶ አደሮች መሬታቸው ለልማት ሲወሰድ ለቤተሰቦቻቸውና ለራሳቸው የሚሰጣቸው የመኖሪያ መሬት አለ፡፡ ዱከም ላይ አቤቱታ አቅራቢዎች መሬታችን ሲወሰድ ወዲያውኑ ለእኛ መደረግ የሚገባው አልተደረግልንም ይላሉ፡፡ የአንድ ጠንካራ አስተዳደር መለኪያው መመሪያና ደንብ እንዲከበር ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ አቤቱታ ምን ምላሽ አለዎት? አቶ ጅብሪል፡- እያንዳንዱ አርሶ አደር የከተማ ይዞታ ሰፍቶ መሬቱን ሲያጠቃልልበት 500 ካሬ ሜትር፣ ይዞታውን ሲነካበት 200 ካሬ ሜትር፣ ከዚህ ውጪ በከተማ ውስጥ እንደ ማንኛውም ዜጋ የመኖሪያ ቤት ጠይቆ የመውሰድ ሕገመንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ከከተማ ውጪ ከሆነ የካሳ ክፍያ ይሰጣል፡፡ በገጠር ቀበሌዎች የመኖሪያ ቦታ አይሰጥም፡፡ ይህ በመመሪያ ተቀምጧል፡፡ በአፈፃፀም ደረጃ ግን ችግር አለ፡፡ ይህ በአንድ አካል አይፈታም፡፡ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች በአንድነት የምንፈታው ነው፡፡ የመሬት ጥያቄ ከፍተኛ በመሆኑ ማዘጋጃ ቤቶች ለማስተናገድ ይቸገራሉ፡፡ ይህም ሆኖ በዱከም ከቀረበ ከ6ሺ በላይ የመሬት ጥያቄ 450 የሚሆኑ፣ በደብረ ዘይት 830 የሚሆኑ አርሶ አደሮች የመኖሪያ ቦታ አግኝተዋል፡፡ ፍላጎቱና አቅርቦቱን ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ ሪፖርተር፡- አጭበርባሪ ባለሀብቶችን መሬት መንጠቅ ብቻ ሳይሆን በሕግ የሚጠየቁበት አግባብ መኖር አለበት ለሚሉት ምን ምላሽ አለዎት? አቶ ጅብሪል፡- ባለሀብቶች ሲመጡ የደም ምርመራ በማድረግ ትክክለኛ ወይም ትክክለኛ ያልሆነ ባለሀብት ብለን መለየት አንችልም፡፡ የወጣውን ደንብና መመሪያ ያሟላሉ፡፡ እናለማለን ይሉናል፡፡ እናምናቸዋለን፡፡ ባስቀመጥነው የጊዜ ገደብ እናስተናግዳቸዋለን፡፡ በጣም ጥቂቶቹ ካሳ ሳይከፍሉ ይጠፋሉ፡፡ የድለላ ሥራ ይሰራሉ፡፡ መሬቱን ለሌላ ባለሀብት ለመሸጥ ይሯሯጣሉ፡፡ መሬት ከመንጠቅ ውጪ ሌላ እርምጃ እንድንወስድ የተቀመጠ ሕግ የለም፡፡ በከፍተኛ ወንጀል የሚጠየቁትን አጥፊዎች ያህል ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ራሳቸውን፣ እንዲሁም እኛንና ገበሬውን ከማታለል ቢታቀቡ ጥሩ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |