|
Sunday, 13 April 2008 |
|
የአንበሣ ሜካኒኮች አላግባብ ከሥራ ታገድን አሉ • ድርጅቱ ግን አስተባበለ
አንበሣ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ስምንት ረዳት (አንደኛ ደረጃ) ሜካኒኮች በተሰጣቸው የሥራ መዘርዝር (ጆብ ዲስክሪብሽን) መሠረት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ በመጠየቃቸው ብቻ ከሥራና ከደመወዛቸው መታገዳቸውን አስታወቁ፡፡ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ተወካይ ደግሞ ስሞታውን አስተባበሉ፡፡
ረዳት ሜካኒኮቹ እንዳመለከቱት ከሥራና ከደመወዛቸው የታገዱት ካለፈው ወር መጨረሻ ጀምሮ ነው፡፡ ድርጅቱ በ1992 አዲስ መዋቅር እንዳወጣና በመዋቅሩም መሠረት ለእያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ መዘርዘር እንዳዘጋጀ አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የድርጅቱ መሠረታዊ ሠራተኞች ማኅበርና ማኔጅመንቱ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ መዘርዝሩ እንዲሰጠው መስማማታቸውን፣ ይሁን እንጂ ማኔጅመንቱ በስምምነቱ መሠረት የሥራ መዘርዝሩን ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን አስረድተዋል፡፡
ይህም በመሆኑ ሠራተኛው ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የሠራተኛ አስማሚ ቦርድ ክስ መስርቶ በቦርዱ ትዕዛዝና ውሳኔ መሠረት የሥራ መዘርዝሩን በእጁ ሊያስገባ ችሏል፡፡ የሥራ መዘርዘሩም ለሜካኒኮች ከአንድ እስከ አራት ደረጃዎችን እንዳወጣ ከእነዚህም መካከል ሜካኒክ አንድ ሥራውን የሚያከናውነው በረዳትነት እንደሆነና በሲኒየር መካኒክ የሚታዘዘውን ሁለ እንደሚፈጽም ልዩ ልዩ ዓይነት መፍቻዎችን እንደሚያጥብና ዕቃዎችንም እንደሚያፀዳ በሥራ መዘርዝሩ ውስጥ መካተቱን አስረድተዋል፡፡
ድርጅቱ ግን ከሥራ መዘርዝሩ ውጭ የአራቱንም ደረጃዎች ሥራ እንደሚያሠራቸው፣ በሥራ ሂደት ላይ እንዳጋጣሚ ሆኖ አንድ ጥፋት ቢከሰት "ያለ ሥራህ ደረጃ ገብተህ አጥፍተሃል" የሚል ክስ እንደሚመሠረትባቸው ገልጸዋል፡፡
ያለምድብ ሥራቸው የብዙ ሺህ ብር የመለዋወጫ ዕቃዎችን አውጡ ተብለው እንደሚገደዱ፣ በሥራ መዘርዝሩ ውስጥ ግን ረዳት ወይም አንደኛ ደረጃ ሜካኒክ የታጠቡ ዕቃዎችን ወደ መጋዘን ያስገባል እንጂ ያወጣል የሚል እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡ ዕቃዎቹን ከመጋዘን ማውጣት የሚገባቸው ግን ሁለተኛ፣ ሦስተኛና አራተኛ ደረጃ ሜካኒኮች ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ የዴፖው ኃላፊ እንኳን ዋጋቸው ከአምስት ሺህ ብር በላይ የሆኑ ልዩ ልዩ መፍቻዎችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ማውጣት እንደማይችል ጠቁመው እነሱ ግን የ17 ሺህ ብር መፍቻ በግዳጅ ያወጡበት ወቅት እንዳለ አስረድተዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ የሥራ መዘርዝሩ ባስቀመጠው መንገድ ብቻ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ለፎርማኖች፣ ለዲፖ ኃላፊዎችና ለድርጅቱ የሠራተኛ መሠታዊ ማኅበር በጽሁፍ ማስታወቃቸውንና ችግራቸው ይፈታልናል ብለው በጉጉት በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ የቴክነክ መምሪያው ከደመወዝና ከሥራቸው እንዳገዳቸው አስታውቀዋል፡፡
ተወካዩ አቶ ሸዋረጋ ሳህሉ ስለዚህ ጉዳይ በስልክ ተጠይቀው በሰጡት መልስ እገዳው በአግባቡ መከናወኑን ነገር ግን ረዳት ሜካኒኮቹ ወደ ሥራ እንመለስ የሚል ደብዳቤ ማስገባታቸውን እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡ |