Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow በ152 ሳምንቶች መካከል
በ152 ሳምንቶች መካከል Print E-mail
Wednesday, 16 April 2008
የግንቦት 7/1997 ዓ.ም ምርጫ ከተካሄደ ከሁለት ዓመት አስራ አንድ ወር በኋላ (ልክ በ152 ሳምንቱ) የተደረገው የማሟያና የክልል እንዲሁም ከዚያ በታች ያሉ ምክር ቤቶች የ2000 ዋርጫ እንዳለፈው ምርጫ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር ቤት የብዙዎችን ትኩረት ማግኘት የቻለ አይመስልም፡፡ የበርካታ አገሮች ምርጫዎች፣ ከእነዚህም መካከል የኔፓል፣ የጣሊያን፣ የአሜሪካ ከአፍሪካ ደግሞ የኬንያ፣ የዚምባብዌ የምርጫ ወሬዎች የትላላቅ የዓለም የመገናኛ ዘዴዎችን ቀስፎ በያዘበትና ርዕሰ ዜና በሆነበት ወቅት የኢትዮጵያ ምርጫ የትም ቦታ ርዕሰ ዜና ሆኖ ሲነገር መስማት አልቻልኩም ወይም አላጋጠመኝም፡፡
 
አንድ ወይም ሁለት ቁልፍ ቃላት ሲሰጡት እነዚህን ማዕከል አድርጐና በእነሱ ዙሪያ በዓለም ዙሪያ ያሉትን የሰማይ የምድሩን ሁሉ እንደ “ጥምብ አንሳ” የሚያሰባስበው ጐግል የተባለው የታወቀው (የኢንተርኔት) ሰርች ኢንጂን እንኳን በዚህ ርዕስ ስር ፈልጌ አገኘሁ ብሎ የሚዘረግፈው የኢትዮጵያ ምርጫ የ1997ቱን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዌብሳይት ራሱ ለመጨረሻ ጊዜ ወቅታዊ የተደረገውና በዚያው ያቆመው በ1997 ዓ.ም ነው፡፡ የ1997 ዓ.ም ምርጫ እየተቃረበ በመጣበት አፍላ መዳረሻው ወቅት ውስጥ በገባበት ወቅት የቢቢሲ ቴሌቪዥን የሀርድ ቶክ አዘጋጅ አዲስ አበባ መጥቶ አቶ መለስ ዜናዊንና አቶ ኃይሉ ሻውልን በተከታታይ የሀርድ ቶክ ፕሮግርሙ ያቀረባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

ቢቢሲ ቴሌቪዥን ላይ የ2000ውን ምርጫ በተመለከተ ለምልክትና ለመሀላ፣ ያገኘሁት ዜና ቢኖር ይኸው ቴሌቪዥን በግርጌ የጽሑፍ ዜናው a helo around the sun starteed people in Ethiopia during Sunday election with some seeing it as a miracle ሲል ብቻ ነው፡፡ ትርጉሙም በፀሀይ ዙሪያ ያለ ፀዳል እሁድ በምርጫው ዕለት ብዙዎቹን አስደንቋል፡፡ ለጥቂቶቹም እንደ ተዓምር ታይቷል የሚል ነው፡፡ አገር ቤት ውስጥ ሆኜ ያላየሁት ያልሰማሁት በአገር የመገናኛ ብዙሃን ዜና ሆኖ ያልመሰከርኩት ይህ ጉዳይ ትርጉሙን ምንነቱን ያላወቅሁት ቢሆንም በዚህ አማካኝነት የአገራችን ምርጫ አሁን 2000 ላይ የተሰጠውን ቦታ ግን ይህን ያህል መሆኑ የሚገርም ቢያንስ ቢያንስ የሚጠበቅ ነው፡፡

የአገራችንን የመገናኛ ብዙሃን በተለይም የመንግሥት ሬዲዮና ቴሌቪዥን በተለይም ምርጫ 97ትን በተመለከተ ከፍ ሲል ከተጠቀሰው ሀርድ ቶክ ጋር በተያያዘ የሚባልና የማይዘነጋ አንድ የቅርብ ጊዜ ትዝታ አለኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን እና ኢንጂነር ሃይሉ ሻውልን ያነጋገራቸውን የስቲቨን ታከርን ሀርድ ቶክ ፕሮግራሞች በራሱ በቢቢሲ ቴሌቪዥን ከተከታተልን በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሁለቱንም ዝግጅቶች “ተርጉሞ” ወዲያው አከታትሎ አቅርቦልን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ያንኑ ያህል የማይዘነጋው እኛ በራሱ፣ በቴሌቪዥኑ ጣቢያ “ይሉኝታ አዋቂዎች” ዘንድም በቸልታ ታልፎ ያልቀረው ትርጉም ተብሎ የተላለፈው የሁለቱም የፖለቲካ ፓርቲ ሹማምንት የሀርድ ቶክ የቢቢሲ ፕሮግራም የአማርኛ ቅጅ እንደተፈለገ ተቆራርጦ ተበጣጥሶ የቀረበ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም የትርጉም ችግሩ እንዳለ ሆኖ በትርጉም ውስጥ አሁንም ይጠፋ፣ ይተን ይበን ዘንድ የተደረገው መልዕክት ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የዝግጅቱ ሙሉ ቃል የተባለው እንዳለ ቀረበልን፡፡ እንደገና የቀረበበት ምክንያት እንደተለመደው (በሕዝብ ጥያቄ) ተብሎ ግን አይደለም፡፡

ምርጫ 2000ን ከምርጫ 1997 የተለየ የሚያደርገው ግን የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋንና ዘገባ አለማግኘቱ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙበት በአገር ቤትም ውስጥ ምርጫ 2000 እንደምርጫ 97 የሕዝብን ሞቅ ደመቅ ያለ እንቅስቃሴ ተሳትፎና ትኩረት አግኝቷል ተብሎ በሙሉ ልብ አፍን ሞልቶ የሚነገርለት አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹ ብንጠቅስ አንደኛው ምርጫ 97 ከምርጫ 2000 የሚለይበት አንድ መሠረታዊ ጉዳይ መኖሩ ነው፡፡ ምርጫ 97 አነሰም በዛም የመንግሥት ሥልጣን የሚመሰረትበት አገራዊና ክልላዊ መንግሥት ማቋቋሚያ ምርጫ ስለሆነ ነው፡፡ ምርጫ 2000 ግን (ከአዲስ አበባው በስተቀር) የማሟያ እና የበታች እርከኖች ምርጫ ነው፡፡

ምርጫ 2000 በተለይም በዕለቱ እንደምርጫ 97 ሞቅ ደመቅ ያለ አልሆነም ሲባል የሚሰጠው ሌላው ምክንያት ምርጫ 2000 ከምርጫ 97 ተምሮ ባሻሻለው ምርጫን የማካሄድ ድምፅ የመስጠት አሰራር ላይ የተመሰረተ ነው የሚለው ነው፡፡ ብዘዎቻችን የምናየውንና የምንሰማውን የአዲስ አበባን ሁኔታ ብንመለከት በ1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ የድምፅ መስጠት ሥነሥርዓት ቀኑን ሙሉ ረዥም ሰልፍ አስይዞ የቆየ መሆኑን በመደበኛው አሰራር 12 ሰዓት ከምሽቱ የሚዘጋው የምርጫ ጣቢያ እንዲራዘም መደረጉ የተራዘመውም የድምፅ መስጫ ሰዓት ጥቂት በማይባሉ ከተሞች እስከንጋቱ መዝለቁ ከዚያም የተነሳ የምርጫ ቦርድ በዚህ ረገድ የአፈጻጸም ብቃቱን የማስፈጸም አቋሙን ማጐልበት ይገባዋል የሚል በጊዜው የተሰጠ ምናልባትም ሁሉም የተስማማበት ሀሳብ መቅረቡ የሚታወቅ ነው፡፡

በዚህም የተነሳ አሁን ሲነገር እንደምንሰማው ለምሳሌ የአዲስ አበባ የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ወደ 1717 ከፍ እንዲሉ መደረጉን ይህም በቁጥር በምርጫ 97 ወቅት ከነበሩት የምርጫ ጣቢያዎች በእጅጉ መጨመሩን በእያንዳንዱም የምርጫ ጣቢያ ከአንድ በላይ የድምፅ መስጫዎች እንዲኖሩ መደረጋቸውን እየተነገረን ነው፡፡ ይህ መኖር የሚገባውን ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ የሰውን ሰልፍ ይዞ መዋልና ማደርም ያስቀራል፡፡ አዲስ አበባን ተዘዋውረው የተመለከቱ በሁለቱም ምርጫዎች ድምፅ የሰጡ ሰዎች እንደሚታዘቡት ግን ምርጫ 2000 እንደ ምርጫ 97 ሞቅ ደመቅ ያለ እንዳይሆን አድርጐታል የሚሉት የዘንድሮው ምርጫ ካለፈው ምርጫ ተምሮ ያስመዘገበው የሎጂስቲክስ ድል ብቻ አይደለም፡፡

አሁንም አዲስ አበባን በዋነኛነትና በምሳሌነት ይዘን እንቆይ፡፡ አዲስ አበባ ከሕገ መንግሥቱ መውጣት በኋላ የመጀመሪያውን ምርጫ ያየችው በምርጫ የተመሰረተ (የተባለ) መንግሥት ያገኘችው በ1992 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ የአዲስ አበባ መንግሥት የአምስት ዓመቱ ዘመን ሳያበቃ፣ በ1995 አካባቢ ተበተነ፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደር ይዞት የ1997 ምርጫ ተካሄደ፡፡ በ1997 ምርጫ የአገሪቷን ርዕሰ ከተማ የመንግሥት አስተዳደር ስለማሸነፍ በአንጻሩም ገዢው ፓርቲ አዲስ አበባ ላይ ከፉኛ ስለመሸነፍ ከሞላ ጐደል ገና እሁድ መንፈቀ ሌሊት አካባቢ የተረጋገጠ ቢሆንም አዲስ አበባ ግን የምርጫ ውክልና ባገኘው ፓርቲ መተዳደር አልቻለችም፡፡ በምርጫ 2000 አዲስ አበባን ማን አሸነፈ የሚለው ጥያቄ በዕለቱ በምርጫው ወቅት ያልተነሳው አዲስ አበቦች እንደ ግንቦት ሰባቱ ምሽትና በማግስቱ ሰኞ ጠዋት እንዳደረጉት የጥያቄውን መልስ ሲያነፈንፉ ሲንሾካሾኩ ያልተደመጡት ከምርጫው ቀደም ሲል ድመፅ ከመስጫው ቀን በፊት የአዲስ አበባ መንግሥት የሥልጣን ባለመብት ሆኖ የሚመረጠው ማን እንደሆነ የታወቀ ነው ብለው ስለገመቱና ስለሚያውቁ ነው፡፡

ሚያዚያ 5 ከጧቱ ጀምሮ እስከ ምሽቱ ድረስ መላውን ከ12 ሰዓት ጀምሮ ያለውን የሁለት ሰዓት ጊዜ የአዲስ አበባን ሰው ሲያጓጓ፣ ሰውን እንደ አሰላለፉ ለሁለት ከፍሎ ሲያወራርድ ሲያሟግትና ሲቃ አስይዞ የቆየው መጨረሻም ላይ ከፍለን ከምጡ የገላገለው ሌላውን ኋላ ላይ ቁርጡ የታወቀውን መርዶ ነግሮ እርሙን እንዲያወጣ ያደረገው ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሴናል ተጫውተው ጨዋታው በማንችስተር 2 ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቅቆ የመጨረሻው ፊሽካ ሲሰማ ነው፡፡

ምርጫ 2000 የአዲስ አበባ ከተማ ምስረታና የከተማው የተወካዮች ምክር ቤት ማሟያ ምርጫ በተካሄደበት በሚያዚያ 5/2000 ላይ ብዙ ሕዝብ አንድ ላይ ተሰባስቦ ያየነው የአዲስ አበባ አብዮት አደባባይን ሕዝብ ሳይጨምር በየቀበሌው በየጓዳ ጐድጓዳው ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ ጨዋታውን ከተመለከተበት አካባቢ እየወጣ ወደየቤቱ ወደየ ቦታው ሲገባ ነው፡፡ ለጥበቃ የተሰለፈውም ፖሊስ ቁጥር የሚናቅ አልነበረም፡፡

አዲስ አበባ ላይ ስንት የምርጫ ጣቢያዎች ነበሩ? አዲስ አበባ ውስጥ የማንችስተር ዩናይትድንና የአርሴናልን ጨዋታ ከቤተሰብ ቁጥር በላይ ለሆነ ሕዝብ ያሳዩ የቴሌቪዥን ማሳያ ቤቶች ቁጥር ስንት ነው? ማለትን በእርግጠኛነት መመለስ ባይቻልም የሰው ልብ የትኛው ላይ ነበር ማለትን ግን ብዙ ሰው የሚያጣው የሚስተው አይመስለኝም፡፡  

የዚህ ምክንያት ብዙዎቻችን አንዳንድ ጊዜ ሲቸግረን አለዚያም ሌላ መሸሸጊያና መከራከሪያ ስናጣ እንደምንለው ወይም አንዳንድ ኤፍ ኤሞች እንሰብካለን ብለው ሲለፉ እንደሚውሉት የብሔራዊ ስሜት ጉድለትና ጉዳይ አይደለም፡፡ ምርጫ 97 የፈጠረው በኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ነባራዊና ባለቤታዊ ሁኔታዎች ኢትዮጵያውያንንም የውጭ አገር ሰዎችንም ያስደነቁና አምሳያም የሌላቸው ነበሩ፡፡ ይህ ግን ወጥቶ ወጥቶ መልሶ እንደሙቀጫ ተንከባለለ፡፡ በሚያሳዝንና በሚያስደነግጥ ሁኔታ ወደነበረበት፣ ከነበረበትም ይበልጥ ወደ ከፋና ወደ ባሰ ሁኔታ ተመለሰ፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ከምክንያቶች ይልቅ የተለያዩ መገለጫዎች እንዳሉት ግልጽ ነው፡፡

አንዳንዶችን ለመጥቀስ ያህል በአንድ በኩል ሕዝቡ ቢያንስ ቢያንስ አዲስ አበባ ላይ ሙሉ በሙሉ የመረጠው ፓርቲ መሪ በሚገርምና የፓርቲው ሌሎች አመራሮች ጭምር በወቅቱ ዝም ብለው ባለፉት ሁኔታ አዲስ አበባ ውስጥ ምርጫው የተጭበረበረ መሆኑን ገልጸው ለቢቢሲ መግለጫ ሰጡ፡፡ ኋላም የአዲስ አበባን አስተዳደር ስለመረከብና ስላለመረከብ ጉዳይ ውክልና  የሰጠውን ሕዝብ ምክር ስብሰባ ውስጥ መፈለግ ገቡ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተሰናባቹ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባን አስተዳደር ሥልጣን ከየአቅጣጫውና በየዘርፉ የሚገዘግዝ እያወጣ መጣ፡፡ አዲስ አበባን ያሸነፈው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና ዘመቻ ባደረገበት መልክ፣ ባሸነፈበት ቅርጽና ይዘት እንዲሁም የፖለቲካ ፕላትፎም መቀጠል አንችልም ተብሎ በአንድ በኩል በመንግሥት በሌላ በኩል ደግሞ በራሳቸው በ"ተቀናጁት" ቡድኖች አማካኝነት ይፈረካከስ ገባ፡፡

አሁን ላይ ሆነን አዲስ አበባን እንዲያስተዳድር ሕዝቡን ራሱን በሚያስደንቅና ሁሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ የተመረጠው ፓርቲ አገሪቷን በመላ አሸንፎ ቢሆን ኖሮ ወይም አሸንፏል ቢባል ኖሮ አገር ምን ይውጠው ነበር የሚለውን ሀሳብ እንደ ሀሳብ እንኳን ስናነሳው ጉዳዩ ይበልጥ አስደንጋጭ ይሆንብናል፡፡ ብዙ ሰዎች ከዚህ በመነሳት ተቃዋሚዎች እንኳንም የመላ አገሪቷን ሥልጣን አልያዙ ማለታቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ስሌት እንኳንም ያሸነፉትን የአዲስ አበባን ሥልጣን አልተረከቡም ይላሉ ብዬ ግን አልገምትም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለራሳቸው ፖለቲካዊ አቋማቸውን የሚገነቡበት፣ የፒያሳውን መንግሥት ይዘው ከአራት ኪሎው መንግሥት ጋር በሰላማዊ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ትግልና ፍጭት ውስጥ ገብተው የኃይል ሚዛን የሚጠብቁበት ልጓም ሆነው በሚያገለግሉበት በዚህም ሂደት ውስጥ እንደ ባለተረቱ "ረዥም ጦር ባይወጉበትም ያስፈራሩበት" ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ ኢትዮጵያ አይታ ባላጣች ነበር፡፡

እንደ ብዙዎች እምነት ምርጫ 97 እንዲያ እንዳማረበት ሳይዘልቅ የቀረበት ምክንያት ምርጫ 2000ም በማንችስተር ዩናይትድና በአርሴናል ጨዋታ ተዋጠ፡፡ "ድምፁ" እንዳይሰማ የሆነበት ምክንያት በአንዱ ወይም በሌላው ፓርቲ "ክፋት" "ጥፋት" ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ የእኛም የሰውም አስተዋፅኦ አለበት፡፡
 
< Prev   Next >