| ሚኒስቴሩ ያሰለጠናቸውን 124... |
|
|
| Wednesday, 16 April 2008 | |
|
ሚኒስቴሩ ያሰለጠናቸውን 124 መሐንዲሶች ወደ ሥራ አላሰማራም
የፌደራል ሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በ2ዐዐዐ ዓ.ም. ሊያስገነባቸው ላቀዳቸው ቤቶች ግንባታ የፋይናንስ፣ የሲሚንቶና የጠጠር ችግር ስላጋጠመው ያሰለጠናቸውን መሐንዲሶች ወደ ሥራ ለማሠማራት መቸገሩ ተሠማ፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመሬት ዝግጅት ክፍል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ደምረው ሚያዚያ 7 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. "በልዩ ኘሮግራም የተቀናጁ የቤቶች ልማት ተሳታፊ ተቋራጮች" በሚል ተደራጅተው ሚያዚያ 1 ቀን 2ዐዐዐ ሥራ እንደሚጀምሩ የተነገራቸውን መሀንዲሶች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች አዋሳኝ ላይ በሚገኘው ጀሞ በሚባለው አካባቢና በቦሌ ክፍለ ከተማ ሰሚት ሥራና ከተማ ልማት በሚለኒየሙ ለሚያስገነባቸው መኖሪያ ቤቶች አዲስ ለሚደራጁ ተቋራጮች ለመስጠት ባወጣው ማስታወቂያ 124 መሐንዲሶች መመዝገባቸውን፣ ሥልጠና መውሰዳቸውን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ሥልጠናውን የወሰዱት መሀንዲሶች ሚያዚያ 1 ቀን 2ዐዐዐ ሥራ እንደሚጀምሩ በምርቃታቸው ወቅት የተገለፀላቸው ቢሆንም በተፈጠረው የሲሚንቶና ጠጠር ምክንያት እንኳን የ2ዐዐዐ ውን ቀርቶ የ99 ኘሮጀክቶችንም ለመጨረስ ከፍተኛ ችግር እንደገጠማቸው አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡ በሚያዚያ ወር ይጀመራሉ የተባሉት 22ሺ ቤቶችን ለማስጀመር በቅድሚያ ማቴሪያሎችን ማዘጋጀት ሥለሚያስፈልግ፣ ሲሚንቶ ከውጭ ለማስገባት የግዢ ስምምነት መፈፀሙን የገለፁት ኃላፊው፣ "በሚቀጥሉት ሁለት ወራቶች ውስጥ እንጨርሳለን የሚል ግምት አለን" ብለዋል፡፡ ኃላፊው እንደተናገሩት፣ ከ1999 ዓ.ም. በጀት 7ዐ ብሎኮች በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ስላሉ በእጣ እንደሚያከፋፍሉዋቸው ለመሀንዲሶቹ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ መሀንዲሶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን ማስታወቂያ በማመን ሥራቸውን ለቀው እንደተመዘገቡ ገልፀው፣ "ለ70 ብሎኮች ዕጣ ታወጣላችሁ" መባሉ፣ እንደሚያሳዝናቸው ተናግረው፣ ዕጣው ያልወጣላቸውና ሥራቸውን የለቀቁ የቤተሰብ ኃላፊዎች ምን ይሁኑ? በማለት ጠይቀዋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ማስታወቂያውን ሲያወጣ እኩል የተመዘገቡት የክልል መሀንዲሶች ክልሉ ባደረገላቸው እርዳታ ሥራ መጀመራቸውን የገለፁት መሀንዲሶቹ፣ "እኛ ገና ፈቃድ ለማውጣት ካንዱ ቢሮ ወደ ሌላ ስንመላለስ፣ እነሱ (የክልሎቹ) እቃ እየገዙ ተገናኘ፡፡ ድርጊቱ ሁሉ ነገር በተሟላበት ከተማ ላለነው የሚያሳፍር ነው" ብለዋል፡፡ በታህሳስ ወር 2ዐዐዐ በወጣ ማስታወቂያ ተመዝግበው በኦሮሚያ ክልል ጫንጮ ከተማ በአውራ ጐዳና ማሰልጠኛ ማዕከል ለስድስት ቀናት መሠልጠናቸውንና መጋቢት 16 ቀን 2ዐዐዐ በሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ምኒስትር ዴኤታ አቶ አርከበ ዕቁባይ መመረቃቸውን የሚናገሩት መሀንዲሶቹ፣ በምርቃቱ ወቅት የገቡላቸውን ቃል ዛሬ ላይ በግልባጩ ማግኘታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናውን ስንጨርስና ሥራ የምንጀምርበት ቀን ለመጠየቅ ስንሄድ "ሥራ የለንም" አሉን የሚሉት መሀንዲሶቹ፣ በሌላ በኩል ከነሱ ጋር ተደርጅተው ቃል ላልተገባላቸው 35 ተቋራጮች ሌላ ሥራ በመሠጠቱ በቀጥታ ለሚኒስትሩ ክስ መመስረታቸውንና ሥራው መታገዱን ተናግረዋል፡፡ መሀንዲሶቹን ለሰበሰቧቸው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ኃላፊዎችና ለአዲስ ብድርና ቁጠባ ኃላፊዎች ባነሱት ጥያቄ፣ የቤቶች ልማትና ኘሮጀክት ፅህፈት ቤት የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የሚሰጠንን ሰርተፍኬት ይፈልጋል፤ ለምን አይሰጠንም? ከሁለት ወር በኋላ ሥራ ልትጀምሩ ትችላላችሁ የሚባለው ክረምቱን ታሳቢ አድርጋችሁታል? የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የኮድና ስታንዳርድ ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ያለው ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ በመጀመሪያ ማሟላት የሚገባችሁን፣ ንግድ ፈቃድ፣ የሥራ ትስስር፣ የሥራ ማስኬጃ ብድርና ሰርተፍኬት ለማግኘት መጣር እንደሚኖርባቸው፣ ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ በመምዘዝ ይኸ ይኸ ይሟላልኝ ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ሥራ አስኪያጅ አቶ አዋሽ አብተው በሰጡት ምላሽ "ከቤቶች ልማት ኘሮጀክት ጽህፈት ቤት ጋር ውል ያላደረገ ብድር አያገኝም" በማለት የሥራ ውልና የብድር ዋስትና ካልተገኘ ብድር እንደማይሰጥ በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡ በመጨረሻ ቀጣይ ሁኔታዎችን በጋራ ተነጋግሮ ችግሩን ለመፍታትና በዛሬው ዕለት ከሠዓት በኋላ ከ1999 በጀት ዓመት ሊገነቡ ታስበው ባልተገነቡት 7ዐ ብሎኮች ዕጣ ላይ ለማውጣትና ለደረሳቸው ለማከፋፈል ከመሀንዲሶቹ አምስት ሰዎች በመምረጥ ስብሰባቸውን አጠናቀዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |