Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow የባህር ትራንዚት ሠራተኞች የጡረታ...
የባህር ትራንዚት ሠራተኞች የጡረታ... Print E-mail
Wednesday, 16 April 2008
የባህር ትራንዚት ሠራተኞች የጡረታ መብት ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም

ከሥራ የተቀነሱ የባህር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ መብታቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁትን ጥያቄ "ሚኒስትሮች ምክር ቤት ውድቅ አድርጎታል" የሚል ምላሽ ከቦርዱ ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ፡፡

ለፕሬዚዳንቱ፣ የጡረታ መብታቸው የሚጠበቅላቸው ሠራተኞችን በተመለከተ ከባህር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት እንደተገለፀላቸው የመንግሥት ድርጅቶችን ለማዞር በሚደረገው ቅድመ ዝግጅት በሚሰራ መዋቅር የማይታቀፉ ሰራተኞችና እንዲሁም የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል በሚዘዋወሩበት ጊዜ (መዋቅር ሣይሰራ) ባለሀብቱ "ሁሉንም ሠራተኞች ይዤ መጓዝ አልችልም" በሚልበት ጊዜ በሚደረግ ድርድር 20/45 በሚለው መመሪያ መሰረት መሆኑንና የባህር ትራንዚት ከዚህ የተለየ መሆኑን ነው፡፡

ባህር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት አትራፊ በመሆኑና በራሱ መዋቅር ሰርቶ ሰራተኞችን በመቀነሱ "ጡረታ አይገባቸውም" በሚል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውድቅ አድርጎ ለድርጅቱ ደብዳቤ ተፅፏል የሚል ምላሽ ከባህር ትራንዚት ኃላፊዎች ማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ካሳሁን፣ ከሥራ አላግባብ ተሰናብተናል በሚል የመሠረቱትን ክስ አቋርጠው ወደ ድርጅቱ ለመጡ የሥራ ስንብትና የሦስት ወር ደመወዛቸውን እንደሚከፍላቸው መናገራቸውን፣ ክሳቸውን ካላቋረጡ የሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በወሰነው መሰረት (ድርጅቱ የሠራው ትክክል ነው ብሎ ወስኗል) የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ተገልፆልኛል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ የሠራው ሥራ አግባብ አለመሆኑን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ሌሎች የመንግሥት መስሪያ ቤቶች (ለምሳሌ ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ፖስታ ቤት ወዘተ) ለቀነሷቸው ሰራተኞች ሙሉ ደመወዝ እየከፈሏቸው መሆኑንና በቅርቡም ዕድሜያቸው 20/45 የሞላቸውን ጡረታቸው እንዲከበርላቸው እየሠሩ መሆኑንና በባህር ትራንዚት እየተፈፀመ ያለው አሳዛኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ካሣሁን አያይዘውም ከኮንፌደሬሽኑ የሕግ ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር አግባብ ሆኖ ካላገኙት፣ ሠራተኞቹ ክስ ሲመሠርቱ ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን በቁጥር ኢሠማኮ 31/719/2005 ከቁጥር ኢሠማኮ 31/882/2000፣ የካቲት 14/2000 እና መጋቢት 18/2000 ለባህር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጅላቸው ቦርዱን ቢጠይቁም ምላሽ አለማግኘታቸውን አቶ ካሣሁን ገልፀዋል፡፡

ከሥራ የተቀነሱ ከ80 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች ከድርጅቱ ሲቀነሱ ተገብቶላቸው የነበረው ቃል ማለትም ደመወዝ ያለመቋረጥ፣ በሴፍትኔት የማይደራጁትን በ20/45 የጡረታ መብት ማስከበርና የመሳሰሉት ሲሆን ቢሆንም ይኸ ሳያሟላ ከስምንት ወር በፊት በመቋረጡ፣ ልጆቻቸው ትምህርት ማቋረጣቸውን፣ ከተከራዩበት ቤት በመውጣት በዘመድ ቤት ደባል መሆናቸውንና በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ፣ መንግሥት ለዜጎች ካለበት ኃላፊነት አኳያ ሊደርስላቸው እንደሚገባ ተናግረው፣ እስከ 27 ዓመት ያገለገሉበት ድርጅት "የጠየቃችሁት የጡረታ መብት ጥያቄ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውድቅ አድርጎታል" መባሉ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የባሕር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት መስሪያ ቤት ማብራሪያ እንዲሰጥ ተገኝተን ለማነጋገር ብንሞክርም፣ ሥራ አስኪያጁ "ሕዝብ ግንኙነቱን አነጋገሩ" በማለት ለማነጋገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡  

በታምሩ ጽጌ
 
< Prev   Next >