| በውሃ ጥም የተደፈቁ ቀበሌዎች |
|
|
| Wednesday, 16 April 2008 | |
በሳምንት ውስጥ እናደርሳለን ውሃና ፍሳሽ ወ/ሮ ተዋበች በ7ዐ ዓመት ዕድሜያቸው፣ ለረጅም ዘመን በኖሩበት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 18 እንደአሁኑ አይነት የውሃ እጥረትና ችግር ገጥሟቸው አያውቅም፡፡ በውሃ እጥረት ምክንያት በአቅመ ደካማነታቸው ከሽሮ ሜዳና ከስድስት ኪሎ ውሃ ለማስቀዳት ለአንድ ጀሪካን ውሃ እስከ አራት ብር ድረስ ይከፍላሉ፡፡ ለዚህ ሁኔታ የተዳረጉት ለአካባቢው የሚላከው የውሃ ስርጭት በሦስት ወይም በአራት ሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ የሚላክና ለፍጆታቸው የማይበቃ በመሆኑ ነው፡፡ "እኔ በዚህ አቅሜ ለውሃው አንድ ብር፣ ለሚያመጣልኝ ሰው ሦስት ብር፣ በጠቅላላ አራት ብር፣ ለአንዲት ጀሪካን ውሃ እከፍላለሁ፡፡ አቅም የለኝ ተሸክሜ አላመጣ ነገር፡፡ ኑሮው እንዲህ ያለ፡፡ እንዴት ይዘልቃል? መላ ፍጠሩልን ነው የምንለው . . . " ይላሉ ባልቴቷ፡፡ የጉለሌዎቹ ቀበሌ 18 እና 19 ነዋሪዎች በከፍተኛ የውሃ እጥረት ተይዘዋል፡፡ በቦታው በደረስንበት ባለፈው ሳምንት ሰፈርተኞቹ በከተማ ነዋሪዎች መሆናቸው ቀርቶ፣ ውሃ ለማግኘት ከሩቅ ርቀት በጀርባቸው አዝለው የሚጓዙትን የገጠሬዎች ኑሮ ዓይነት ሆኗል፡፡ ብዙዎቹ ሴቶች ጀሪካኑን በሻርፓቸው፣ ጀሪካኑን በጀርባቸው አዝለው፣ ወንዶች በትከሻቸው ተሸክመው ወደ ሰፊር ይገባሉ፡፡ ሸክማቸው ከሽሮ ሜዳ ወይም ከስድስት ኪሎ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለመሸከሚያ የሚያውሉት ሻርፓቸው እላያቸው ላይ ተቀዷል፡፡ ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ውሃ ካገኙ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከሁለት ወር ወዲህ፣ ከሦስት ጊዜ በላይ ውሃ አልመጣላቸውም፡፡ ያውም ቢሆን ሌሊት የምትመጣና አነስተኛ ፍጆታ ያላት በመሆኗ ችግራቸውን የባሰ እንዳደረገው ይናገራሉ፡፡ "ውሃ የለንም፤ ምንም የለንም፤ አቅም በሸክምም በመኪናም ያመጣል፤ እኛስ ምን እንሁን . . . " ሲሉ በዝቅተኛ ኑሮ ያሉት የሰፈሩ ነዋሪዎች ችግራቸውን ይዘረዝራሉ፡፡ ከርቀት የሚያመጡት ውሃ እንደባልቴቷ ሁሉ ጉዞው ብቻ ሳይሆን ወጪውም ክፉኛ አንገዳግዷቸዋል፡፡ "ስድስት ኪሎ ሄደን ውሃውን ከአንድ ብር በላይ እንገዛለን፤ በታክሲ ለማምጣት ሁለት ብር ከነሰውዬው፣ ከሽሮ ሜዳ ከሆነ አንድ ብር ከነሰውዬው፣ ሁለት ብር እንከፍላለን፡፡ መሸከም ያልቻሉ ወደ ሰፈር ለመግባት ሁለትና ሦስት ብር ይከፍላሉ፡፡ በጠቅላላ ለ2ዐ ሊትር ውሃ 4 ብር እንከፍላለን፡፡ አሁን እኛ መንግሥት ያውቀናል ማለት ይቻላል ወይ?" ትላለች ሌላዋ ሰፈርተኛ፡፡ "ከአዲስ አበባ ነዋሪ በተለየ መልኩ ችግር ደርሶብናል፣ አስታዋሽም አጥተናል፤" የሚሉት የቀበሌው ነዋሪዎች፣ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ለቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ድርሻ በሕብረት ሄደው ማመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅዋም በቦታው ተገኝተው እንደሚያዩት ነግረው ቢመልሱዋቸውም እንዳልመጡላቸው በቅሬታ ይናገራሉ፡፡ ደጋግመው ለባለሥልጣኑ ቢናገሩም መፍትሔ አልሰጡም፡፡ አንድ ጊዜ የውሃዎችን ጉድጓድ ለማየት ከመጡት የመሥሪያ ቤቱ ሰዎች ሌላ መፍትሔ የሚያመጣ ሰው ቀርቶ የሚያነጋግራቸው እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የቢዝነስ ዲቨሎኘመንት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰዒድ ይመር፣ በአካባቢው ከፍተኛ ችግር መኖሩን እንደሚረዱ፣ በሥፍራው ተገኝተውም ነዋሪዎች እንዳነጋገሩና ለመፍትሔው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በአካባቢው ያገለግል የነበረው ጉድጓድ ለመጠጥነት ሊሆን ባለመቻሉ የእጥረቱ መነሻ እንደሆነ የሚገልፁት አቶ ሰዒድ ባለሥልጣኑ ጉድጓዶች በመቆፈር ችግሩን ለማስወገድ እየጣረ መሆኑንም ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡ "አሁን ሃምሌ 19 የተቆፈረው ጉድጓድ አልቆ ፓምፑ ተተክሏል፡፡ የመስመር ግንኙነት ሥራው አልቋል፡፡ መብራት ኃይል የመስመር ሥራውን እንደጨረሰ ወደ ተራራው ገብተን በግራቪቲ ውሃ እንሰጣለን . . . " ይላሉ አቶ ሰዒድ፡፡ በዚህ ረገድ ለቀበሌ 18 እና 19 በዚህ መንገድ የሚሰጠው ውሃ እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ይጠናቀቃል የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ እስከዚያው ድረስም በዛሬውና በነገው ቀን፣ የፈረቃ ኘሮግራም ጀምረው የአካባቢው ሰዎች ውሃ እንዲያገኙ ለማድረግ የታቀደ መሆኑን አቶ ሰዒድ ገልፀዋል፡፡ እንደ እንጦጦ አካባቢ ባሉ ከፍተኛ ቦታዎች ውሃ ለማዳረስ ከፍተኛ ግፊት የሚያስፈልግ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋነኛው ተጠቃሽ ይሆናል፡፡ የውሃ ሥርጭት ከየማጠራቀሚያዎቹ በቅብብሎሽ የሚሰራ እንደሚሆኑ በየቦታው ባሉ ማጠራቀሚያዎች የመብራት ተራ በገቡ ቁጥር አንዳንድ ሰፈሮች እንደሚጎዱ ከባለሙያዎች ያገኘነው አስተያየት ያስረዳል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በበኩሉ ለውሃ ስርጭት ቅድሚያ በመስጠቱ ባለሥልጣኑ በመረጣቸው ቦታዎች ዲዝል መትከሉን መጠባበቂያም ማስቀመጡን ይናገራል፡፡ ባለሥልጣኑ በጠየቀው መሠረት እንጦጦ አካባቢ የኬብል ሥራው መጨረሱን ተግባራዊ ለማድረግ ከአንድ ቀን በላይ እንደማይፈልግ አቶ ሞገስ በላቸው የኮርፖሬሽኑ የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም እና የደንበኞች አገልግሎት ድጋፍ መምሪያ ኃላፊ ይናገራሉ፡፡ አሁንም የውሃ ሥርጭት ቅድሚያ ስለሚሰጠው በሚያስፈልግበት ቦታ ኃይል ለመስጠት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ለቀበሌ 18 እና 19 ግን የሁለቱ መሥሪያ ቤቶች መጠያየቅም ሆነ መደጋገፍ እስካሁን መፍትሔ አልሆናቸውም፡፡ ለነዋሪዎቹ መፍትሔ የሚሆነው ጥማቸውን የሚቆርጥ ውሃ ሲያገኙ ነው፤ ለዚህም "በአንድ ሳምንት ውስጥ" ውሃውን እንደሚያደርሱ አቶ ሰዒድ የተናገሩትን በታላቅ ጉጉት ይጠብቁታል፡፡ ከጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |