Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የተመድና የኢራን የኒውክሊየር ውይይት ተላለፈ
የተመድና የኢራን የኒውክሊየር ውይይት ተላለፈ Print E-mail
Wednesday, 16 April 2008
የኢራን የኒውክሊየር ግንባታን በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሊየር መቆጣጠሪያ ድርጅትና በኢራን የኒውክሊየር ጉዳይ ተወካይ መካከል ሊካሄድ የነበረው ውይይት ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን የኢራን የዜና አገልገሎትን በመጥቀስ አሶሽየትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
በዘገባው መሠረት ውይይቱ የተላለፈበት ምክንያት አልታወቀም፡፡ በውይይቱ ኢራንን በመወከል ጎላምሬዝ አግሀዛዳ እንዲሁም ተመድን በመወከል መሀመድ ኢባራዲ እንደሚወያዩ ተገልጾ ነበር፡፡ በቬና ያለፈው ሰኞ ሊካሄድ  በታቀደው በዚሁ ውይይት በኢራን የኒውክሊየር ማበልፀግ ሂደት ዙሪያ ውይይት ለማካሄድ ታቅዶ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል፡፡

የኢራንን የኒውክሊየር ግንባታ በተመለከተ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ያለፈው ወር ባካሄደው ስብሰባ በኢራን ላይ የሶስተኛ ዙር ማዕቀብ ለመጣል መስማማቱ ይታወሳል፡፡ ኢራን በበኩሏ የምትበለጽገው የኒውክሊየር ኃይል ለሲቪል ተቋማት የኃይል ምንጭነት መገልገያ እንደምትጠቀምበት አስታውቃለች፡፡

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አምስቱ ቋሚ አባላት እንዲሁም ጀርመንን ጨምሮ ዛሬ በኢራን የኒውክሊየር ጉዳይ ላይ ውይይት ያደርጋሉ፡፡

የአለም ባንክ የምግብ ዋጋ ንረት አሳሳቢ መሆኑን ገለፀ

የአለም ባንክ ሊቀመንበር ሮበርት ዞሊክ በአለም ላይ የተፈጠረው ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ንረት አንድ መቶ ሚሊዮን የደሃ አገራት ነዋሪዎችን ወደ ድህነት አረንቋ ውስጥ የሚጥላቸው መሆኑን ገልፀዋል ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡

በቅርቡ የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መሪ የምግብ ዋጋ ንረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለከፋ የረሃብ ስቃይ መዳረጉን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ የአለም ባንክ ሊቀመንበር ሮበርት ዞሊክ በምግብ ዋጋ ንረት ምክንያት የድህነት መጠን እንደሚጨምር አስጠንቅቀዋል፡፡ ለዚህም የአለም አቀፉ ማኅበረሰብ የእርሻ ምርት የሚያድግበትን መንገድ ማፈላለግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሮበርት ዞሊክ በቅርቡ ከምግብ ዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ በግብጽ፡ በሀይቲና በፊሊፒንስ ከፍተኛ አመጽ መቀስቀሱን ጠቅሰው፤ "የአለም አቀፉ ማኅበረሰብ አዲስ የምግብ ዋጋ ልውውጥ የህግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል" ብለዋል፡፡ ሮበርት ዞሊክ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ የምግብ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን ጠቅሰው፤ መቶ ሚሊዮን የድሀ አገር ነዋሪዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

የኢራቅ ፓርላማ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ የሚያደርጉትን ቆይታ ይወስናል

የኢራቅ ፓርላማ የአሜሪካ የጦር ኃይል በኢራቅ የሚያደርገውን ቆይታ በተመለከተ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥ ሮይተርስ ከባግዳድ ያሰራጨው ዘገባ አመለከተ፡፡
የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሺያር ዞባሪ የኢራቅና የአሜሪካ ባለሥልጣናት የአሜሪካ የጦር ኃይል በኢራቅ የሚያደርገውን ቆይታ በተመለከተ ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ውይይቱ ሲጠናቀቅ የኢራቅ ፓርላማ የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ሆሻያር ዞባሪ አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካ በኢራቅ ቆይታን አጥብቀው የሚቃወሙት የኢራቅ ሺአቶች ተወካይ የሆኑት የፓርላማ አባላት በአሜሪካ ቆይታ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እየገለፁ ሲሆን፤ በፓርላማ ውስጥ ካላቸው አነስተኛ መቀመጫ አንፃር የሚወሰነውን ውሳኔ ማስቀየር እንደማይችሉ ተገልጿል፡፡

በኢራቅ የአሜሪካ አምባሳደር ሪያን ክሮከር ለአሜሪካ ኮንግረንስ ያለፈው ሳምንት ባቀረቡት ሪፖርት፤ ከኢራቅ ባለሥልጣናት ጋር የሚደረገው ውድድር የአሜሪካ የቆይታ ጊዜና የአሜሪካ ወታደሮችን ቁጥር የማይወስን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት የተሰጣት የኢራቅን ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል፡፡ ከዚህ አንፃር የአሜሪካና የኢራቅ ባለሥልጣናት በቀጣይ ጊዜያት በሁለቱ አገራት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡
 
< Prev   Next >