| የአለም ባንክ በቆጋ መስኖ... |
|
|
| Wednesday, 16 April 2008 | |
|
የአለም ባንክ በቆጋ መስኖ ለደረሰው ኪሳራ ካሳ ሊከፍል ነው
የዓለም ባንክ የቆጋን መስኖ ለመገንባት ተስማምተው ሥራ ጀምረው ለነበሩት የቻይና ኩባንያዎች በጊዜው ክፍያ ባለመክፈሉ ለደረሰባቸው ኪሳራ ካሳ ሊከፍል ነው፡፡ የውሀ ሀብት ሚኒስትር አቶ አስፋው ዴንጋሞ ትናንት በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር የሥራ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት የቆጋ መስኖ ሥራ ከሁለት አመት በፊት በሁለት የቻይና ኩባንያዎች ቢጀመርም በስምምነቱ መሰረት ባንኩ በ28 ቀናት ጊዜ ውስጥ ገንዘቡን ሳይለቅ በመቅረቱ ኩባንያዎቹ ሥራ አቋርጠው ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ የቆጋ መስኖና ተፋሰስ እንክብካቤ ፕሮጀክት ሥራዎች የእቅዳቸውን 52 በመቶ ተካሂደዋል፡፡ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ከእቅዱ በታች ያደረጉት ምክንያቶች የግድቡ ግንባታን በተመለከተ በአበዳሪው ድርጅት በኩል ለሥራ ተቋራጩ ክፍያ ሳይፈጸም በመዘግየቱ ምክንያት በጥቅምት ወር 2000 ዓ.ም ኮንትራቱ የተቋረጠ በመሆኑና እስከ መጋቢት 10 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ ባለመከናወኑ፣ የመስኖ ግንባታን በተመለከተ የአነስተኛ መስኖና የገጠር መጠጥ ውሃ ግንባታ በሥራ ተቋራጩ አቅም ውስንነት ምክንያት በእቅዱ መሠረት ባለመሰራቱ እንዲሁም የ45 ኪሎ ሜትር መንገድ እና አነስተኛ ህንፃዎች ግንባታ የሥራ ተቋራጭ ቅጥር ሂደት ከታሰበው ጊዜ በላይ በመውሰዱ ነው፡፡ ይሁንና ተቋርጦ የነበረው የግድብ ኮንትራት ከአበዳሪው ባንክና ከሥራ ተቋራጩ ጋር በተካሄደው ሰፊና ረጅም ድርድር በኋላ ስምምነት ላይ በመደረሱ ከመጋቢት 10 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ የማሻሻያ ኮንትራት ተፈርሞ የግንባታው ሥራ እንደገና ተጀምሯል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት በውሀ ሃብት ሚኒስቴርና በገንዘብ ሚኒስትር በኩል ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ባንኩ ክፍያውን በማዘግየቱ ላደረሰው ኪሳራ ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል፡፡ የቆጋ ፕሮጀክት ራሱን የቻለ ችግር ያለበትና በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አስፋው የአፈፃፀም ችግር የተከሰተው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስልጣን ውጭ በተከናወኑ ሥራዎች መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለውን የመጠን ውሀ ችግር በማስመልከት ከተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ በከተማዋ ከሚመረተው የመጠጥ ውሀ 35 በመቶ የሚሆነው በፍሰት እንደሚባክን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ህጋዊ ያልሆነ ቅጥያዎች፣ የመገጣጠሚያ ፓምፖች በአግባቡ አለመከናወን፣ ጥራት የሌላቸው ቧንቧዎችና በከተማዋ የሚከናወኑ የተለያዩ ግንባታዎች ለውሀ ፍሰቱ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ እየታየ ያለው የውሀ ችግር ከከተማው ማደግ ጋር ተያይዞ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን ያመኑት አቶ አስፋው በፍሰት የሚባክነውን ውሀ ለመቀነስ ከፈረንሳይ አገር በተገኘ እርዳታ አሮጌ ቧንቧዎች በአዲስ የመተካት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመዲናዋ ለተከሰተው የውሀ ችገር የአጭር ጊዜ መፍትሄ ለመስጠትም የጉድጓድ ቁፋሮ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አቶ አስፋው እንዳሉት የሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት በቅርቡ ባከናወነው ጥናት መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ በጣም ትልቅ የሆነ የከርሰ ምድር ውሀ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ ይህንን ተከትሎም የአለም ባንክ በሰጠው ብድር በመታገዝ እስከ 350 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ከ75 እስከ 100 የሚደርሱ ጉድጓዶች ቁፋሮ ለማከናወን ታቅዷል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በከተማዋ ውስጥ በተመረጡ ቦታዎች 40 የውኃ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡ የውሀ ፓምፕ የመግዛት ሥራም እየተከናወነ መሆኑን አቶ አስፋው ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከጥቂት አመታት በፊት የከርሰ ምድር ልማት ለማልማት በአቃቂ አካባቢ ጉድጓድ ቆፍሮ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ የተቆፈረው የውሀ ጉድጓድ ጥልቀት ስላልነበረው በሁለት አመት ጊዜ ብቻ መጠኑ እንደቀነሰ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚታየውን የውኃ ችግር ለመፍታት የረጅም ጊዜ እቅድ ተብሎ በሚኒስትሩ የተገለፀው የገፈርሳነና የለገዳዴ ግድቦችን የውኃ አቅርቦት ከፍ ማድረግ ነው፡፡ በኃይሌ ሙሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |