| የተባበሩት መንግሥታት ለኢትዮ-ኤርትራ... |
|
|
| Wednesday, 16 April 2008 | |
![]() የኢትዮ-ኤርትራ የሠላም አስከባሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባንኪሙን የኢትዮ-ኤርትራ የሠላም አስከባሪ ኃይል የወደፊት እጣ ፈንታን አስመልክቶ ካቀረባቸው አራት አማራጮችን መካከል ኤርትራ በጣለችው እገዳ ምክንያት የሠላም አስከባሪ ኃይሉ ሙሉ በሙሉ ስራውን የሚያቆምበትን ሁኔታ እንደሚገኝበት ተጠቆመ፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዋና ፀሐፊው ሪፖርት ኤርትራ የሕግ ጥሰት አሳሳቢነትና አደገኛነት ያሳነሰ ነው በሚል ቅሬታውን ገልጿል፡፡ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ተልዕኮውን በተመለከተ አማራጭ ያሉትን አቅጣጫዎች ባለፈው ሳምንት በቀረበው የድርጅቱ ልዩ ሪፖርት ላይ ዘርዝረዋል፡፡ ባንኪሙን ኤርትራ በሠላም አስከባሪ ኃይሉ ላይ የጣለችውን የኃይል አቅርቦት እገዳ ካነሳች፤ የሰላም አስከባሪ ቡድኑ ተልዕኮ ሳይለወጥ የሚቀጥልበትን ሁኔታ በመጀመሪያ አማራጭነት አስቀምጠዋል፡፡ ያለበለዚያ የቡድኑ ተልዕኮ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ማድረግ በሁለተኛ አማራጭነት ሲቀርብ፤ በሀገሪቱ መካከል ያለውን የጦርነት ውጥረት የሚያረግብ አነስተኛ የክትትል ቡድን በድንበር አካባቢ ማስፈር በሦስተኛ አማራጭነት ቀርቧል፡፡ ዋና ፀሃፊው ሁለቱ ሀገራት እ.ኤ.አ በ2000 የደረሱበትን የሰላም እንዲሁም የድንበር ማካለል ስምምነትን አስመልክቶ ተግባራዊ ለማድረግ እገዛ የሚያደርግ ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባና በአስመራ ማቋቋም የመጨረሻ አማራጭነት አስቀምጠዋል፡፡ ዋና ፀሃፊው ያቀረቡት አማራጭ አቅጣጫዎች ያላቸውን ጠቀሜታና ጉዳት በሪፖርቱ ላይ አመላክተዋል፡፡ በዚህም የሰላም አስከባሪው ኃይሉ ተልዕኮውን ሙሉ በሙሉ የማቋረጥ አማራጭ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት ሊቀሰቅስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ የተሻለ የሚሉትን በተመለከተ የውሳኔ ሀሳብ በአፋጣኝ እንዲያቀርቡ ዋና ፀሃፊው ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም "ለቀጠናው ሰላምና ደህንነት እንዲሁም አሸናፊ በሌለው ግጭት የሚደርሰውን ጥፋት ከግንዛቤ በማስገባት፤ ሀገራቱ የተቀበሉትን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ባንኪሙን፤ በሐምሌ 24/2000 ዓ.ም. የሰላም አስከባሪ ኃይሉ የቆይታው ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ከሀገራቱ ጋር ውይይት በማካሄድ ተጨማሪ ሪፖርት ለፀጥታው ምክር ቤት የሚያቀርቡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ባለፈው አርብ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ በ1998 ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችውን ወረራ ከመቃወም ወደኋላ ማለቱን አስታውሶ፤ ከዚያ በኋላም በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡ በዚህም ምክር ቤቱ ኤርትራ በቀጠናው ሰላም ለማስፈን የተደረሰውን ስምምነት በመፃረር ያደረገችውን እንቅስቃሴ ለማስቆም ያደረገው እንቅስቃሴ አነስተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡ መግለጫው እ.ኤ.አ ሰኔ 2000 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገ የሁለትዮሽ ውል መሠረት ግጭት የማጥፋት ስምምነት መካሄዱን አስገንዝቧል፡፡ በዚህም ስምምነት ኤርትራ እ.ኤ.አ ግንቦት 1998 የጀመረችውን ጦርነት ለማስቆም ተኩስ አቁም መደረጉ፣ የሁለቱ ሀገራትን ወታደሮች ለመለየት ጊዜያዊ የደህንነት ቀጠና መካለሉንና ቀጠናውን የመቆጣጠር ኃላፊነት ለሠላም አስከባሪ ኃይሉ መሰጠቱ ይታወቃል፡፡ ስምምነቱ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ በአካበቢው የመንቀሳቀስ እንዲሁም አስፈላጊውን የመገልገያ አቅርቦት የማግኘት መብት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የፀጥታው ምክር ቤት በስምምነቱ የተቀመጠውን ግዴታ የጣሰ አገር ላይ ማዕቀብ የሚጥል መሆኑን በስምምነቱ ክፍል ሰባት ላይ መገለፁት መግለጫው አብራርቷል፡፡ ኤርትራ እ.ኤ.አ ከመጋቢት 2ዐዐ4 ጀምሮ በሰላም አስከባሪ ኃይሉ ላይ የተለያዩ እገዳዎችን በመጣሏ፤ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ አካባቢ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ጊዜያዊ የደንነት ቀጠናውን ለመልቀቅ መገደዱን ጋዜጣዊ መግለጫው ገልጿል፡፡ ኤርትራ ጊዜያዊ የደህንነት ቀጠናውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯንም አስታውቋል፡፡ በዚህም ኤርትራ የዓለም አቀፍ ህግን እንዲሁም ለፀጥታው ምክር ቤት ተገዢ የሆነውን የሁለትዮሽ ውል መጣሷን መግለጫው አመላክቷል፡፡ ለዚህም የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ ያለፈው ሳምንት ለፀጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ፣ ኤርትራ ህግ መጣሷን መግለፃቸውን የሚያጣቅሰው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የዋና ፀሃፊው ሪፖርት ኤርትራ ያካሄደችውን የህግ ጥሰት አሳሳቢነትና አደገኛነት በማሳነስ ማቅረቡን አውስቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሪፖርቱ የኤርትራ ህገወጥነት በአልጀርሱ ስምምነት ላይ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው የሰላም ስምምነት ሂደት ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ አለማገናዘቡን መግለጫው ተችቷል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የፀጥታው ምክር ቤትና የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ ኤርትራ የምታካሂደውን ህገወጥ እንቅስቃሴ እንዲያስቆሙ ኢትዮጵያ ጥሪ ማድረጓን አስታውቋል፡፡ በዚህም የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ የጣሰችውን ህግጋት በሙሉ እንዲያስከብር አሳስቧል፡፡ በተጨማሪም ለአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊነት የጊዜያዊ የደህንነት ቀጠናው ነፃ መሆንና የሰላም አስከባሪ ኃይሉ በአካባቢው ሊጀምር እንደሚገባ መግለጫው አሳስቧል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |