| ከጨረር ጉዳት የሚከላከል መድኃኒት |
|
|
| Wednesday, 16 April 2008 | |
|
የሰው ልጅ አካል በጨረር እንዳይጎዳ የሚከላከል መድኃኒት መሥራታቸውን የአሜሪካ ሳይንቲስቶች አስታወቁ፡፡
የጨረር ህክምና ጤናማ ሴሎችን የመጉዳትና ካንሰር የማስከተል ባህሪ ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ የጨረር መከላከያ መድኃኒት መገኘቱ ደግሞ የጨረር ህክምናን የተሻለ ወጤት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ሳይንቲስቶቹ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም መርዛማ ቦምቦች ወይም የኒውክሊየር አደጋ በደረሰበት አካባቢ መድኃኒቱን መጠቀም አዋጭ ይሆናል ብለዋል፡፡ ሲ.ቢ.ኤል.ቢ.ኤስ.አይ የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የጨረር መከላከያ መድኃኒት በእንስሳት ላይ ተሞክሮ ባሳየው ውጤት ጤናማ ሴሎች በጨረር እንዳይጎዱና ጤናማነታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ የማድረግ ኃይል አለው፡፡ በጨረር ህክምና ጊዜ ጨረር ከሚደረግበት እጢ አካባቢ ያሉ ጤናማ ሴሎችን ሊገድል ይችላል፡፡ በመሆኑም የጨረር ህክምና ሰጪዎች በተቻላቸው አቅም ሁሉ እጢው ባለበት የተወሰነ ቦታ ብቻ ማተኮር አለባቸው፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው ሲ.ቢ.ኤል.ቢ.ኤስ.አይ የተሰኘው መድኃኒት መቅኒ ውስጥ የሚፈጠሩ ጤናማ ሴሎችን ከጨረር አደጋ መከላከል የሚችል ቢሆንም ቀደም ብለው ጤናማነታቸው የተጓደሉ ሴሎችን ለመፈወስ የሚችል አይደለም፡፡ በአይጦችና ጦጣዎች ላይ በተደረገ ጥናት እንስሳዎቹ ለጨረር ከመጋለጣቸው ከ45 ደቂቃ እስከ 24 ሰዓት ባለ ጊዜ ውስጥ መድኃኒቱን በመርፌ መልክ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ ውጤቱም መድሃኒቱን የወሰዱት እንስሳት ካላገኙት ይልቅ ለረዥም ጊዜ መኖር ችለዋል፡፡ መድሃኒቱ ይህ ነው የተባለ ተጓዳኝ ችግር የሚያስከትል መሆኑ በአይጦች ላይ በተደረገ ሙከራ ተረጋግጧል፡፡ ይሁንና ትንሽ ችግር ያለባቸው ሴሎችንም ቢሆን እንዳይሞቱ ሊከላከል ስለሚችል ችግር ያለባቸው ሴሎች አለመሞታቸው ደግሞ ቆይተው ወደ ካንሰርነት ሊለወጡ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ፡፡ ራስን ለማጥፋት የሚገፋፉ ድረ ገፆች ስጋት ፈጥረዋል ራስን ስለማጥፋት የሚተነትኑ መረጃዎችን ለማግኘት ድረ ገፆችን የሚጎበኙ በርካታ ናቸው፡፡ ሰዎች ራስን ለማጥፋት የሚደግፉና የሚያበረታቱ መረጃዎችን ማግኘታቸው ስጋት ፈጥሯል የሚለን ቢቢሲ ነው፡፡ በእንግሊዝ የህክምና ጆርናል በወጣው ፅሁፍ አጥኚዎቹ አራት ፈታሽ ማሽኖችን በመጠቀም ስለራስን ማጥፋት የሚያወሩ ድረ ገፆችን ፈትሸዋል፡፡ ከመካከላቸው ሦስቱ ድረ ገፆችም ራስን ማጥፋትን የሚያበረታቱና የሚደግፉ መሆናቸውን በተደረገው ፍተሻ ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ራስን ማጥፋትን የሚቃወሙ ድረ ገፆች እንዲከፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አእምሮ ጤና ላይ የሚሰሩ አካላትም የተከፈቱት ድረ ገፆች ራሳቸውን ለማጥፋት ቅርብ ለሆኑ (በተለይም የአእምሮ ጭንቀት) ያለባቸው ሰዎችን ወደ አደጋ የሚመሩ ናቸው ሲሉ ማውገዛቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያትታል፡፡ አንዳንድ አገሮች እነዚህን ድረ ገፆች ያገዱ ቢሆንም እንግሊዝን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አገሮች ራስ ማጥፋትን የሚደግፉ ድረ ገፆችን አላገዱም፡፡ በተደረገው ጥናት ከራስ ማጥፋት ጋር ተያያዥነት አላቸው የተባሉ 24ዐ ያህል የተለያዩ ድረ ገፆች የተገኙ ሲሆን ከመካከላቸው 9ዐ ያህሉ በትክክል ራስን ስለማጥፋት የሚያወሩ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ደግሞ ራስ ማጥፋትን የሚደግፉ፣ የሚያበረታቱና ራስን ለማጥፋት የሚያመቻቹ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ድረ ገፆቹ ማበረታቻውን የሚሰጡት አጓጊ በሆኑ ቃላት አንድ ሰው ራሱን ለማጥፋት ምን ዓይነት ዘዴዎችን ቢጠቀም የተሻለ እንደሆነ በማስረዳት ነው፡፡ የጥናቱ መሪ ሉሲ ቢድል እንደሚሉት የዚህ ዓይነት ህገ ወጥ ሥራ በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የተስፋፋው ራስን ሳንሱር ማድረግ በሚለው ህግ ምክንያት እንደሆነ ገልፀው በነዚህ ድረ ገፆች ላይ አንድ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ጉግልና ያሁ የድረ ገፅ ማስታወቂያቸውን ሊጋሩ ነው በዓለም ላይ ታላላቅ የሚባሉት ጉግልና ያሁ ድረ ገፆች የማስታወቂያ ቦታ ለመጋራት ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በስምምነቱ መሠረት በያሁ ድረ ገፅ ላይ ጉግል ሦስት በመቶ የማስታወቂያ ቦታ ይጋራል፡፡ ተንታኞች እንደሚሉት ስምምነቱ ያሁ ድረ ገፅን በ44.6 ቢሊዮን ዶላርና ከዛ በላይ ለመግዛት ሃሳብ ያቀረበውን ማይክሮሶፍት አስፈርቶታል፡፡ እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ከሆነ ማይክሮሶፍትና ኒውስ ኮርኘ የተሰኙ ካምፓኒዎች ያሁን በጋራ ለመግዛት ተወያይተዋል፡፡ ሃሳቡ በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎበኙ ማይ ስፔስ፣ ያሁ እና ኤም ኤስ ኤ ዶት ኮም የተሰኙ ሦስት ድረ ገፆችን በአንድ ላይ የሚያዋህድ መሆኑን ኒውዩርክ ታይምስ አስታውቋል፡፡ ማይክሮሶፍት ያሁ ከጉግል ጋር ያደረገውን የማስታወቂያ ቦታ የመጋራት ስምምነት ተቃውሟል፡፡ ማሊሺየስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኮምፒውተሮችን አጥቅቷል የኮምፒዩተር ቫይረሶች አንድ ሚሊዮን ኮምፒውተሮችን እንዳጠቁ ተገለፀ፡፡ አዲስና እየተስፋፋ ያለው ማሊሺየስ ኘሮግራም በተለይ በደህንነት ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ቫይረስ መሆኑን የዓመቱ የኢንተርኔት ደህንነት ሪፖርት ጠቁሟል፡፡ ማሊሺየስ በመባል የሚታወቀውና የተስፋፋው የቫይረስ ኘሮግራም በተለይ ባለፈው ዓመት የተፈጠረ መሆኑም ታውቋል፡፡ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2007 ሁለተኛው አጋማሽ ዓመት ብቻ ከ500 በላይ የሚሆኑ አዳዲስ የማሊሺየስ ኮድ ያላቸው ቫይረሶች ተሰራጭተዋል፡፡ ቁጥሩ እንደሚያሳየውም በመጀመሪያው የ2007 አጋማሽ ከነበረው የቫይረስ ቁጥር የ136 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ በአውሮፓ በበረራ ወቅት የሞባይል አጠቃቀም ህግ ወጣ በአዲሱ የአውሮፓ ኮሚሽን ህግ መሠረት በአውሮፓውያን የአየር ክልል ውስጥ በሚደረግ በረራ የሞባይል ስልኮችን መጠቀም እንደሚቻል ተገለፀ፡፡ በአንድ ጊዜ በረራ በ3000 ሜትር ከፍታ ላይ ብቻ መጠቀም እንደሚቻል በውሳኔው የተፈቀደ ሲሆን ከአውሮፓውያን ህግ አውጭዎች ምክክር በኋላ አገልግሎቱ በቀጣዩ ወር ይጀምራል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ቴሌኮምስ ኮሚሽነር ቫይቪን ሬዲግ ኦኘሬተሮች ክፍያቸውን ተመጣጣኝ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ "ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ዋጋ ከተጠየቁ አገልግሎቱ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ በተጨማሪም በበረራ ወቅት የሚደረጉ ጥሪዎች ተጓዦችን የማይረብሹና ምቹ እንዲሆኑ ለኦኘሬተሮች ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ኮሚሽን ምቹ የቴክኒክ አቅርቦት ህግ አስተዋውቋል፡፡ በተጨማሪም ህጉ ብሔራዊ ፍቃድ ያላቸውን የግል የበረራ አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ አገልግሎቱን የመስጠቱ ውሳኔ በግል የበረራ አገልግሎት ሰጪዎች እጅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከቴክኖሎጂው ጋር መስማማታቸውን የሚያረጋግጥ ህግ ይኖራል፡፡ የአውሮፓ የበረራ ደህነነት ወኪል ግን የበረራ ሂደቶችን የሚያውክ የሃርድ ዌር አቅርቦት ላለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል፡፡ አገልግሎቱ የሚገኘውም ከበረራው መነሻ እስከ ማብቂያ አገልግሎት የሚሰጥና በኋላም ሊጠፋ የሚችል አነስተኛ ሞባይል በማስቀመጥ ነው፡፡ በነዚህ ስልኮች የሚደረጉ ጥሪዎች በአቅራቢያው ካለ ኔትወርክ በሳተላይት ይገናኛሉ፡፡ የአውሮፓ ሬዲዮ ዘርፍም የቴክኖሎጂው አጋር ነው፡፡ አገልግሎቱ አውሮኘላኑ የአውሮፓን ምድር (ክልል) እንደለቀቀ የሚቋረጥ ይሆናል፡፡ የሚስ ሬዲንግ ቢሮ ቃል አቀባይ ማርቲን ሶልማየር እንደሚሉት ስልኮቹን ማቋረጥ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አብራሪዎች አገልግሎቱን ማቋረጥ ይችላሉ፡፡ አገልግሎቱ ለሁለተኛ ትውልድ ብቻ የሚቀርብ ቢሆንም ፍላጐት ታይቶ ለሦስተኛም ትውልድ እያደገ የሚሄድ ይሆናል፡፡ በአውሮኘላን በረራ ወቅት ለሚደረጉ የሞባይል ጥሪዎች ክፍያ በምድር ላይ ከሚከፈለው የበለጠ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮኘላን በረራ ወቅት የሞባይል ስልክ ጥሪንም ሆነ መደወልን የፈቀደው ኢምሬትስ አየር መንገድ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |