Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ማስተማር በወጣት...
ማስተማር በወጣት... Print E-mail
Wednesday, 16 April 2008
Image
ወጣት ብሌን አሰምሬ
Image
ወጣት ያሬድ ንጉሴ
ማስተማር በወጣት መምህራኑ እይታ

ትምህርቷን በ1999 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ፋኩልቲ 3.5 አጠቃላይ ውጤት በማስመዝገብ አጠናቅቃለች፡፡ ወጣት ብሌን አሰምሬ በአሁኑ ወቅት እዚያው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ፋኩልቲ ውስጥ በመምህርነት በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡
ማስተማር የጀመረችው በያዝነው አመት መጀመሪያ ላይ ሲሆን ሕግ የመጀመሪያ ምርጫዋ እንደነበርና የአስተማሪዎቿ የማስተማር ብቃትና ትጋት እዚያው ዲፓርትመንት ውስጥ ጥሩ ውጤት በማምጣት አስተማሪ ሆና የመቅረት ፍላጐት እንዳጫረባት ታስታውሳለች፡፡ "የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ከሆንኩ ጀምሮ ይህ ፍላጐቴ ይበልጥ ጨመረ፡፡ መምህሮቼ እንዴት ሥራቸውን ጥሩ አድርገው ይሠሩ እንደነበር፣ የሚሰጡት ትምህርት እንዴት ይገባኝ እንደነበር ስመለከት ከፍተኛ ፍላጐት አደረብኝ" ብላለች፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተማረችው የአንደኛ አመት ተማሪዎችን ሲሆን በእድሜ ከነሱ ብዙም የማትበልጥ መሆኑን ሲያስተውሉ አብዛኞቹ ተማሪዎች ፈገግ በማለት የመገረም ሁኔታ ማሳየታቸውን አስታውሳለች፡፡ በተወሰነ መልኩ ፍርሀት ቢሰማትም ለሌሎች ነገሮች ትኩረት ባለመስጠት ማስተማር በሚገባት መልኩ ማስተማሯን ስትቀጥል ማስተማር የመጀመሪያዋ በመሆኑ ተፈጥሮባት የነበረው ጫና እንደጠፋ ገልፃለች፡፡ ከዚህ በኋላ በማስተማርና ከክፍል ውጭ የሚሰሩ መመዘኛዎችን በመስጠት የማስተማር ሂደቱ እየተጠናከረ መምጣቱን በመጠቆም ሥራዋን በአግባቡ ከመሥራት በስተቀር ተማሪዎች እንዲያከብሩአት የምታደርገው ነገር እንዳልነበር ትናገራለች፡፡

በተማሪዎችና በእሷ መካከል ያለው የእድሜ መቀራረብ ተማሪዎቹ ያላቸውን ማንኛውንም ጥያቄ ያለምንም ፍርሀት እንዲጠይቁ ነፃ የመማርና የማስተማር ሂደትን እንደፈጠረ የምትናገረው ብሌን በማንኛውም ሰው እንዲሁም በራሷ እንደተረዳችው አንድ ሰው ሥራውን በአግባቡ እየሠራ ከሆነ ሌላኛው ወገን ይቀበለዋል፣ ያከብረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የወጣት ጀማሪ መምህራንን መበራከት፣ ከዚህም ባሻገር አዲስ በተከፈቱ ዩኒቨርሲቲዎች ዲን የሆኑ አዳዲስ ተመራቂዎች መኖርን በመጥቀስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተማሪነት በቀጥታ መምህር ወይም ዲን መሆን ልምድ አይጠይቅም? ስንል ጠየቅናት፡፡ ..በከፍተኛ የትምህርት ተቋም በቀጥታ ከተማሪነት ወደ መምህርነት መሸጋገር ፈታኝ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ እኔና መሰል መምህራን እድሜ የሚያመጣው የእውቀት ብዛትም እርጋታም አይኖረንም፡፡ ጥንቃቄና ጥረት ካለ ደግሞ ማስተማርም ይቻላል ብዬ አስባለው፡፡ የሚጀምረውም ከዚህ ነው፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ዛሬ ላይ ባለን አቅም ሙሉ በሙሉ ማስተማር ከቻልን መልካም ነው፡፡ መጥፎው ነገር ዛሬ ላይ ከአቅሜ በታች ያስተማርኩ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ዲን መሆን በተለይም ብዙ ሥራ በሚጠበቅበት አዲስ ዩኒቨርሲቲ ከባድ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከማስተማር ባሻገር በርካታ አስተዳደራዊ ኃላፊነቶችን መሸከም ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ደግሞ እድሜና ልምድ ይጠይቃል.. በማለት ማስተማር በራሱ ከማስተማር ውጭ የተለያዩ ጥናቶችን ማካሄድ የሚጠይቅ በመሆኑ ልምድ ላለውም ለሌለውም ፈታኝ መሆኑን አመልክታለች፡፡

የማስተማር ፍላጐት ያለውና ጥሩ ተማሪ መሆን የቻለ ጥሩ መምህር መሆን ይችላል የምትለው ወጣት ብሌን አንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች የግድ ልምድ የሚጠይቁ መሆናቸውን፣ እሷና እንደሷ ያሉ ጀማሪ መምህራንም እንዲያስተምሩ ሲመደቡ ይህ ከግንዛቤ ውስጥ ገብቶ እንደሆነ አልደበቀችም፡፡ ልምድ ካላቸውና ከቆዩ መምህራን ጋር ያላት ግንኙነት ከተማሪነቷ ጀምሮ መልካም እንደነበርና እነሱ ሞክረዋቸው የተለያየ ተፅእኖ ስላስከተሉ እርምጃዎች ወይም አካሄዶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለእርሷና ለጓደኞቿ እንደሚገልፁላቸው አመልክታለች፡፡ ጀማሪ መምህራን እያሉ ከማስተማርና ውጤት ከመስጠት ጋር ተያይዞ የገጠማቸውን ሁኔታ መናገራቸው ጠቀሜታ እንዳለውም ገልፃለች፡፡

ወጣት ጀማሪ እንዲሁም ሴት መምህር በመሆኗ እስካሁን የገጠማት አስቸጋሪ ሁኔታ የለም፡፡ ምናልባት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዙ ወጣት ሴት መምህራን ስለሌሉ የእሷ ወጣት ሴት አስተማሪ መሆን በሴት ተማሪዎች ላይ ጥሩ ስሜት ይፈጥራል ብላ ታምናለች፡፡

ወጣት ያሬድ ንጉሴ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነው፡፡ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በ1998 ዓ.ም. ሲሆን በቢዝነስ ኤዱኬሽን ዲፓርትመንት በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ከነበረበት የዲፓርትመንት ክፍለ ትምህርት 3.75 በማምጣት እዚያው ሊቀር መቻሉን የሚናገረው ወጣት ያሬድ ሊመረቅ ሁለት ዓመት ሲቀረው በየትኛው ዩኒቨርሲቲ በሚለው እንጂ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ መምህር እንደሚሆን እርግጠኛ እንደነበር ያስታውሳል፡፡፡ "መምህሮቼ በማስተማር፣ ፈተናና ማርክ በመስጠት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በደንብ እከታተል ነበር፡፡ ከዚህ ውጭም አንድ መምህር ስንት ክፍል ጊዜ መያዝ እንዳለበትና ደሞዝን በሚመለከት ሁሉ መረጃ ነበረኝ፡፡ እንደተማሪ ሆኜ እገነዘብ ከነበረው ውጭ መምህር ሆኜ የገጠመኝ አስቸጋሪ ነገር የለም" በማለት በማስተማር ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ጀማሪ መምህራን የሚጠበቅባቸውን በመስራት መጋፈጥ እንደሚችሉ ያስረዳል፡፡ ማንኛውም ሰው የሚጠበቅበትን ከሰራ ሌሎች ሰዎች ያን ሰው ከመቃወም ይልቅ ወደ መቀበል ያመዝናሉ ብሎ ያምናል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስተማር የተመደበው በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሰማንያ ተማሪዎች ባሉበት ክፍል እንደነበር የሚያስታውሰው ያሬድ አብዛኞቹ ተማሪዎች በእድሜ ከእሱ ከፍ ያሉ ስለነበሩ ፣አስተማሪያችሁ እኔ ነኝ፣ ሲላቸው በመገረም ፈገግ ማለታቸውን ይናገራል፡፡ ከዚያ በኋላ የማስተማር ችሎታውን፣ ለሠዓት የሚሰጠውን ግምትና ለእነሱ ያለውን አክብሮት ሲመለከቱ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት መልካም እየሆነ መምጣቱን አመልክቷል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማስተማር ልምድ አስፈላጊነትን እንዴት ታየዋለህ? "በማስተማር ሂደት ውስጥ ልምድ አስፈላጊ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ልምድ ማግኘት ለሁሉም ሰው የሚወስደው ጊዜ ግን እኩል ነው ብዬ አላስብም፡፡ ለምሳሌ እኔ ተማሪ እያለሁ አስተማሪ እንደምሆን አውቅ ስለነበር አስተማሪዎቼ ሲያስተምሩ ራሴን በእነሱ ቦታ በማስቀመጥ የማይበት ሁኔታ ነበር፡፡ ስለዚህ ማስተማር ፍፁም አዲስ አልሆነብኝም፡፡ ልምድ አስፈላጊ ቢሆንም የግድ ሀያና ሠላሳ ዓመት መውሰድ አለበት ብዬ አላምንም"

በማስተማር ሂደት የትምህርት አቀራረብ፣ ጥያቄ አወጣጥና ውጤት አሰጣጥ ሁለም በአጠቃላይ ልምድ የሚጠይቁ ቢሆንም ተማሪዎች የሚፈለገውን ነገር እንዲረዱ የሚያስችል አቀራረብ ማምጣት ከፍተኛ ልምድ እንደሚጠይቅ ያስረዳል፡፡ ቢሆንም ብዙ ዓመት ማስተማር ጥሩ የትምህርት አሰጣጥ መንገድን ለማዳበር ዋስትና አይደለም ብሏል፡፡ ያሬድ እንደገለፀው የትምህርት አሰጣጥ ዘዴን ለማዳበር በአንድ የትምህርት ዘርፍ ከመቆየት ልምድ የሚገኝ ቢሆንም ልምድን ከተማሪ ፍላጐትና የመረዳት ችሎታ ጋር አጣምሮ መሄዱ የጀማሪውንም ሆነ የአንጋፋውን መምህር ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡

በምሕረት አስቻለው
 
< Prev   Next >