| ሕይወት በአንዋር መስጊድ ደጃፍ |
|
|
| Wednesday, 16 April 2008 | |
|
አንዋር መስኪድ አካባቢ ስንደርስ ስድስት ሠዓት ሊሞላ ጥቂት ደቂቃዎች ቀርተዋል፡፡ የመስጊዱን የግንብ አጥር ተከትለን ወደ በሩ አቅጣጫ ስንሄድ ወደ መስኪድ ለመግባት ዑዱ የሚያደርጉ (እግር፣ እጅ፣ ፊትና ጆሮአቸውን) የሚታጠቡ በርካታ ሰዎች ተመለከትን፡፡ በመስጊዱ አጥር መደዳውን ብዛት ያላቸው የሃይላንድ ኘላስቲኮችን በውኃ ሞልተው ሳጥን ውስጥ የሚደረድሩ ሰዎችም አየን፡፡
ወደ በሩ እየተጠጋን ስንሄድ ውኃ የተሞሉ ሀይላንድ ኘላስቲኮች የተደረደሩባቸው እንጨት ሳጥኖች በተርታ መደርደራቸውን አስተዋልን፡፡ በፍጥነት እያጠበች የምትደረድር ሴት በማየታችን ጠጋ ብለን አነጋገርናት፡፡ በአፉ ተደፍቶ የተቀመጠ ሳጥን ላይ ተቀምጠው ዑዱ የሚያደርጉ አዛውንት ደግሞ አጠገቧ ቁጭ ብለዋል፡፡ ሀናን አሕመድ አንዋር መስጊድ በር ላይ የዑዱ ውኃ መሸጥ ከጀመረች ከሁለት ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡ ሁለት መቶ የሚሆኑ የሀይላንድ ኘላስቲኮች አሏት፡፡ ከፍ በሚሉ የሀይላንድ ኘላስቲኮች የተዘጋጀውን የዑዱ ውሀ በሀያ አነስተኛውን ደግሞ በአሥራ አምስት ሳንቲም ትሸጣለች፡፡ ወደ ሥራ ቦታዋ (አንዋር መስጊድ ደጃፍ) ጠዋት ሦስት ሠዓት ላይ እንደምትሔድ የምትናገረው ሀናን ከመጣችበት ሠዓት ጀምሮ ቀን ስድስት፣ አስርና ምሽት አሥራ ሁለት ሠዓት ላይ ወደ መስጊድ መጥተው ለሚሠግዱ ሰዎች የዑዱ ውሀ ስትሸጥ እንደምትውል ገልፃለች፡፡ የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆኗ መስኪድ ለመስገድ የሚሄዱ ሰዎች የዑዱ ውሀ ችግር እንዳለባቸው መስማቷ ወደ ሥራው ለመግባት ምክንያት ሆኗታል፡፡ አብዛኛወን ጊዜ በስድስት ሠዓቱ የስግደት ጊዜ ወደ መስጊድ የሚመጡ ሠዎች ቁጥር እንደሚጨምርና፣ በተለይም አርብ አርብ በዚህ የስግደት ጊዜ እስከ መቶ ሀምሳ ሀይላንድ የዑዱ ውኃ ልትሸጥ እንደምትችል ትናገራለች፡፡ አርብ አርብ ለስግደት የሚመጣው ሰው ብዙ በመሆኑ መስኪዱ ደጃፍ ላይ የሚሰግዱ ሰዎች አሉ፡፡ ከሀናን አኗር መስኪድ በር ላይ እንደሷ የዑዱ ውሀ ከሚሸጡ ሰዎች ላይ የዑዱ ውሀ በመግዛት አማኞች ዑዱ በሚያደርጉበት ወቅት የሚፈጠረው ፍሳሽ አካባቢውን ስለሚያጨቀይ አርብ አርብ መስኪዱ በር ላይ የዑዱ ውሀ እንዳይሸጡ ተከልክለዋል፡፡ በቀን ሀያና ሰላሳ ብር ይዛ ወደ ቤቷ ትገባለች፡፡ አርብ ደግሞ የዑዱ ውሀ በብዛት የሚሸጥበት ቀን በመሆኑ፣ አርብ አርብ እንዳይሸጥ መከልከሉ አይጐዳሽም? ስንል ጠየቅናት፡፡ "የከለከሉን ደንብ አስከባሪዎች ቢሆኑም ትእዛዙ ከበላይ የመጣ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ምክንያቱ አሳማኝ ነው" በማለት ከመስጊድ በር ራቅ በማለት ቦታ ይዘው የዑዱ ውሀ የሚሸጡ የተወሰኑ ሰዎች መኖራቸውን ገልፃለች፡፡ እሷም እንደሌሎቹ የማትሸጠው ቦታ ስለሌላት መሆኑን አልደበቀችም፡፡ ሀናን ባለትዳርና የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሕፃን ልጅ እናት ናት፡፡ የምትኖረው ኮልፌ ፈጥኖ የሚባል አካባቢ ነው፡፡ የምትኖረው በግለሰብ ቤት በወር መቶ ሃምሳ ብር እየከፈለች ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቤቷ የምትገባው ከምሽቱ ሁለት ሠዓት እስከ ሦስት ሠዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ የምትናገረው ሀናን ታክሲ በማይገኝበት ጊዜ ወደ ቤቷ በእግሯ የምትሄድባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን አልደበቀችም፡፡ እሷ የዑዱ ውኃ ሸጣ የምታገኘው ገንዘብ ላይ የባለቤቷ ተጨምሮ የሚያስፈልጋቸውን አሟልተው እየኖሩ እንደሆነ ገልፃልናለች፡፡ እሷም ሆነች ሌሎቹ የዑዱ ውኃ ሻጮች ውኃ የሚቀዱት አስፋልት አካባቢ ከሚገኙ ሱቆች ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ራሷ፣ አንዳንዴ ሲደክማት ወይም ልጇ ሲያስቸግራት ለጉልበት ሠራተኞች ከፍላ ታስቀዳለች፡፡ ምሽት ላይ ወደ ቤቷ ከመሄዷ በፊት የሀይላንድ ኘላስቲኮቹን አጣጥባ በማዳበሪያ በመክተት መስጊዱ አካባቢ ከሚገኙ ሱቆች ታስቀምጣለች፡፡ አርብ አርብ የዑዱ ውሀ እንዳይሸጡ ከመከልከላቸው በፊት የምታርፈው እሁድን ብቻ ነበር፡፡ አሁን እሁድና አርብን ጨምሮ በተለያዩ የሙስሊም በዓላት ቀን የዑዱ ውሀ ለመሸጥ ወደ አኗር መስጊድ ደጃፍ አትመጣም፡፡ ምክንያቱም የእምነቱ ተከታዮች በበዓላት ቀን የሚሠግዱት በስታዲየም በመሆኑ ነው፡፡ ክረምት ላይ ሥራ እንዴት ነው? "በክረምት ማንም ዝናብ ላይ ተቀምጦ ዑዱ የሚያደርግ የለም፡፡ ሁሉም ከያለበት አድርጐ ነው የሚመጣው፡፡ ስለዚህ እኔም ክረምት ክረምት ላይ እዚሁ አካባቢ ሻይ እሸጣለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን የዑዱ ውሃ መሸጤን ሙሉ በሙሉ አቆማለው ማለት አይደለም" በማለት እዚያው መስጊድ አካባቢ ሱቅ ውስጥ ለሚሠሩ እንዲሁም ለጉልበት ሠራተኞች ሻይ መሸጡን ትኩረት ሰጥታ እንደምትሠራ ገልፃልናለች፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |