Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የድርሰትን ሙያ በአጋጣሚ
የድርሰትን ሙያ በአጋጣሚ Print E-mail
Wednesday, 16 April 2008
Image
ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም
ትርጉም፣ ወጥ እንዲሁም በኮንትራት አርትኦት ይሠራሉ፡፡ ሥነ ጽሑፍን በአጋጣሚ እንደጀመሩ የሚናገሩት ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም በሎስ አንጀለስ ተማሪ በነበሩበት ወቅት በኢትዮጵያ ሴማዊ ቋንቋዎች ሊቅ የነበሩት መምህራቸው ለእያንዳንዱ ሴማዊ ቋንቋ መዝገበ ቃላት እያዘጋጁ ነበር፡፡ ለሥራቸው ይረዳቸው ዘንድም በወቅቱ ከነበሩት ተማሪዎች ከየቋንቋው ከየነገዱ በመውሰድ እየጠየቁ ይሰሩ ነበር፡፡

"ለምን አንድ ነገር አትጽፍልኝም፡፡ ቃላት ለመሰብሰብ ይረዳኝ ነበር" በማለት በወቅቱ ተማሪ ለነበሩት ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ የተማሪውም መልስ "ይቻላል" ሆነ፡፡ ለመምህራቸውም አንድ ጽሑፍ አቀረቡ፡፡ ጽሑፉን ሲያቀርቡት መምህራቸው ለሚሰሩት መዝገበ ቃላት ይረዳል በሚል እንጂ ከዚህ አልፎ ለህትመት ይበቃል የሚል ግምት አሳድረው አልነበረም፡፡

መምህሩ ጽሑፉን ወደዱት፡፡ ለዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ፕሬስም አሳዩት፡፡ በጉራግኛ የተፃፈው የመጀመሪያ ሥራቸውን የእንግሊዝኛ ትርጉም፣ አሳታሚ ድርጅቱ አይቶ ነፃ ትርጉሙ ቢቀርብለት ሊያሳትመው እንደሚችል ገለፀላቸው፡፡ በቋንቋ ፕሮፌሰር መምህራቸው አርታኢ ተመደበላቸውና ትርጉሙን እንዲሰሩ ተደረገ፡፡

በ1954 ዓ.ም ሥራውን እንዲሰሩ ተጠይቀው የመጀመሪያ ጽሑፋቸው የሆነው "የሺነጋ ቃያ" በእንግሊዝኛው "ሺነጋስ ቪሌጅ" በሚል በ1956 ዓ.ም የህትመት ብርሃን አየ፡፡

መጽሐፍ ይሆናል ብለው ያላሰቡት ሥራ ታትሞ ሲያዩት ጥሪዬ ወደ ድርሰቱ ይሆናል በሚል ስለ ሥነ ጽሑፍ ማሰብ ጀመሩ፡፡

በሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ ጨቦና ጉራጌ አውራጃ ሲሴ መንደር የተወለዱትና ከሰባት ቤት ጉራጌ አንዱ በሆነው ቸሃ ወገን የተወለዱት ደራሲ ሣህለ ሥላሴ የመጀመሪያ ሥራቸው ከጉራግኛ ቋንቋ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ እዚያው አሜሪካ ገበያ ላይ ውሏል፡፡ ጉራግኛውና የቃል በቃል ትርጉሙንም መምህራቸው ፕሮፌሰር ሌስላው ጀርመን አገር አሳትመውታል፡፡ በጉራግኛ ከዚያ በፊት ጽሑፍ ታትሞ ስለማያውቅ የሚያነብም ሰው ስላልነበረ፣ አሳታሚ ድርጅቶችም አንባቢ ስለማይኖረው አያሳትሙትም የሚል አመለካከት ስለነበራቸው በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲታተም አላደረጉም፡፡ ለቋንቋው ተናጋሪዎች ዛሬ ቢወጣ ግን እንደሚጠቅም ከታሪክ አንፃር የመጀመሪያው በጉራግኛ የተፃፈ እንደሆነ የሚነገርለት ይኸው "የሺነጋስ ቪሌጅ" እምነታቸው ነው፡፡

በጉራጊኛ ታትሞ ለአንባቢያን ባይሰራጭም "ሺነጋስ ቪሌጅ" የሚለው የእንግሊዝኛ ትርጉም በወቅቱም በኢትዮጵያ ተነባቢ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ለማሳተም ፍላጐቱ ቢኖራቸውም ብዙ የጉራጊኛ ጽሑፍ አንባብያን አለመኖሩ እንጂ ሊመጣ የሚችለውን ኪሳራ ወስደው ሊያሳትሙ በቻሉ ነበር፡፡

የደራሲ ሣህለ ሥላሴ "ሺነጋስ ቪሌጅ" እንዲሁም "አፈርሳታ" ጭብጣቸውን በኢትዮጵያ የገጠር ህይወት ዙሪያ አድርገው የታተሙት በእንግሊዝኛ ነበር፡፡ "ባሻ ቅጣው"ና "ዘ ዋሪየር ኪንግ" ደግሞ ታሪካዊ ልብ ወለዶች ናቸው፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ፣ በማይጨው ጦርነትና በአርበኞች ታሪክ ላይ ያጠነጥናሉ፡፡

 ደራሲው ፖለቲካ ነክ የሆኑ ድርሰቶችንም ይጽፋሉ፡፡ "ፋየር ብራንድስ" በእንግሊዝኛ የፃፉት ሲሆን የሚያጠነጥነውም ከአብዮቱ ቀደም ብሎ ያለውንና ከአብዮቱ በኋላም እስከተወሰነ ድረስ ያለውን ሁኔታ በልብ ወለድ መልክ ያቀረቡበት ነው፡፡ አብዮቱ ገና ይመጣል፣ የብሔረሰቦች ጉዳይ አልተፈታም የሚል ይዘት አለው፡፡

ስለ ንቅዘትና የአብዮቱ አመጣጥ እንዲሁም የተማሪዎች ንቅናቄ ምን ይመስል እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ለደራሲ ሣህለ ሥላሴ እስከ ዛሬ የሚቆጫቸው ይህ ሥራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ አለመሸጡ ነው፡፡ የታተመው በደርግ ጊዜ ስለነበር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይገባ በመታገዱ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ነው ተሸጦ ያለቀው፡፡ ዛሬ ሳንሱር ባለመኖሩ መታተም የሚችል ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ደራስያን ችግራቸው አሳታሚዎችም ማግኘት ጭምር በመሆኑ ሊያሳትሙት አልቻሉም፡፡

በቅርቡ ለማውጣት ያሰቡት ደግሞ በራሳቸው ግለ ሕይወት ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ነው፡፡ ባለፉት 60 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የአፄ፣ የደርግና ያለንበትን መንግሥት ከራሳቸው ሕይወት ጋር አያይዘው የሚያቀርቡበት ይሆናል፡፡

ደራሲው "እንደማንኛውም ሰው ብዙ ውጣ ውረድ ደርሶብኛል፣ ፈተና አለ፤ ግን መጽሐፌ ውስጥ ስላለ ብዙ በመዘርዘር በቅድሚያ ላጨናግፈው አልፈልግም" ብለዋል፡፡

ትርጉም አንዱ ሥራቸው ነው፤ ወደ ትርጉም የሚያዘነብሉት ግን የሃሳብ ድርቀት ሲያጋጥማቸውና ጊዜያቸውን በከንቱ ማሳለፍ እንደሌለባቸው ሲያምኑ ነው፡፡ የሚወዷቸውንና ለኢትዮጵያውያን ጠቃሚ ናቸው የሚሏቸውን ብሉይ (ክላሲካል) ድርሰቶችን ይተረጉማሉ፡፡ ካነበቡዋቸው ውስጥ ለኅብረተሰቡ ፋይዳ አላቸው ያሏቸውን ስድስት መጽሐፎች ከፈረንሳይኛና ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመተርጐም አሳትመዋል፡፡

"ለ ሚዘረብል" "መከረኞች" በሚል ወደ አማርኛ የተረጐሙትን የቪክቶር ሁጎ ሥራ የእንግሊዝኛውን ሙሉ ትርጉም ይዘው የሚጠራጠራቸውን ከፈረንሳይኛው ጋር እያገናዘቡ ሠርተዋል፡፡ ከፈረንሳይኛው እንግሊዝኛው እንደሚቀናቸው የሚናገሩት ደራሲ ሣህለ ሥላሴ "ኤ ውመንስ ላይፍ" በሚል በፈረንሳዊ የተደረሰውን መጽሐፍ "እጣ ፈንታ" በሚል ተርጉመዋል፡፡

የእንግሊዛዊውን ቻርለስ ዲከንስ፣ የአሜሪካዊቷ ፐርል ፓክ እንዲሁም የመጨረሻው ትርጉማቸው የጥቁር አሜሪካዊው ሪቻርድ ልይት "ኔቲቭ ሳን" "የአገር ልጅ" ከትርጉም ሥራዎቻቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ከወጥ ሥራ ይልቅ የትርጉም ሥራ ይበዛል፡፡ ደራሲው መጥፎ ነው ብለው አያምኑም፡፡ ምክንያቱም የትርጉም ሥራ የአንድ አገርን ሥነ ጽሑፍ አደጋ ላይ የሚጥለው የትርጉም ሥራው ወጥ ሥራውን ሲተካው ነውና፡፡

በትርጉም ዙሪያ የሚያሳስባቸው መብዛቱ ሳይሆን ጥራቱ ነው፡፡ በጥራት እስከተተረጐመና ለኅብረተሰቡ ፋይዳ ያለው ሥራ እስከተሰራ ድረስ ትርጉም እንዲሰራ ከሚደግፉ ደራስያን መሃል ናቸው፡፡ ጥራቱ ላይ ትኩረት መስጠት ተገቢ መሆኑን ግን ያሰምሩበታል፡፡

ሥነ ጽሑፍ ሊዳብር የሚችለው ተቺዎች ወይም ሐያስያን ሲኖሩ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ስለትርጉም ጥራት ሲነሳም የጥራቱን ደረጃ በማስጠበቅ ዙሪያ የሐያስያን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ሐያሲያን ካሉ ትችት ያቀርባሉ፡፡ አጥንተው ጠንካራና ደካማ ጐኑን ይናገራሉ፡፡ አስተያየት ሲሰጡም አንባቢው ስለቀረበው ጽሑፍ ያውቃል፣ ይረዳል፡፡

ሒስ ለሥነ ጽሑፍ እድገት አስፈላጊ ቢሆንም በአገራችን ሐያሲና ሒስ አለ ወይስ የለም? የሚለው አሁንም ድረስ አከራካሪ ነው፡፡ ስለ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ተንትኖ በመጽሐፍ ሒስ ያቀረበ ባለሙያ በዘመናቸው አላዩም፡፡ የመጽሐፍ ምዘና (ቡክ ሪቪው) ግን አለ፡፡ እሳቸውም ይሰራሉ፡፡ መጽሐፍ በሚመዝኑበት ጊዜ ተንትነው ግምት ይሰጣሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ሥራ የሚሰሩ ሌሎች ደራስያን አሉ፡፡ "ሐያሲ" ናቸው ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር ግን ይከብዳቸዋል፡፡

ለሥነጽሑፋችን ማደግ ሐያሲ ያስፈልጋልና ብሎ በፍላጐቱ የሚነሳ ሰው ቢኖር ጠቃሚ ነው"፡፡ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ሰዎች በተለይም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉት በሐያሲነት መሥራት እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ደራስያን ሐያስያን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ደራሲ በድርሰቱ ሲያተኩር ሐያሲ ሒስ በመስጠቱ ይሰራል፡፡ ደራሲው ጊዜ ካለው የሒስ ሥራን ሊሰራም ይችላል፡፡ ሆኖም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሥነ ጽሑፍና ቋንቋ ካጠኑ ሰዎች ውስጥ ነው ሐያስያን መውጣት ያለባቸው፡፡ የደራስያን ማኅበርም ቢሆን መድረክ ሊያዘጋጅ፣ ሊያነቃቃና በሙያው የሰለጠኑትን ጋብዞ ሊያወያይ ይችላል፡፡

"ሚዩዚክ ሜይዴይ" የሚሰራው ደራስያንንና ሥራቸውን የመገምገምና የማስተዋወቅ ተግባር ሥነ ጽሑፉ እንዲዳብር አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ደራሲ ሣህለ ሥላሴ መምከር የሚፈልጉት እሳቸው ተጋባዥ ሆነው ..ፋየር ብራንድስ.. ልብወለዳቸው በተገመገመበት ወቅት ያጋጠማቸውን በማስታወስ ነው፡፡

ተጋባዥ ሆነው ስለ ልብ ወለዱ በሚያቀርቡበት ወቅት ተጋባዥ ከነበሩት እንግዶች ምን ያህሉ መጽሐፉን አንብበው እንደመጡ ጠየቁ፡፡ ከነበሩት ሰዎች ሦስቱ ብቻ ነበሩ እጃቸውን ያወጡት፡፡ መጽሐፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ስላልተሸጠ ብዙዎቹ ማንበብ ያልቻሉ መሆኑን እንደ አንድ ምክንያት ቢገነዘቡም ካልተነበበ ውይይት ማድረግ የማይቻል መሆኑን ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ መጽሐፉ ገበያ ላይ አይዋል እንጂ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ አለ፡፡

ደራሲ ሣህለ ሥላሴ እንደገለፁልን ኢትዮጵያ ውስጥ ትርጉሞች በቅጡ ከተተረጎሙ ሽያጫቸው ከወጦቹ ይበልጣል፡፡ የአገራችን አንባቢ ወጥ ሥራ ከሚያነብ ይልቅ ትርጉም የሚመርጥ ይመስላቸዋል፡፡

ደራሲው፡- "እምዩ"፣ "የሁለት ከተሞች ወግ"፣ "ያገር ልጅ" የሚለውን ጨምሮ ስድስት የትርጉም ሥራዎች አላቸው፡፡ "ባሻ ቅጣው"፣ "ሹክታ"ና ሌሎች ያሏቸው ሲሆን ከአማርኛው ሌላ በእንግሊዝኛ ሶስት፣ በጉራግኛ አንድ በድምሩ 14 ልብ ወለድ፣ ኢልብ ወለድና የትርጉም ሥራዎችን ለአገር ውስጥና ለውጭ አንባብያን አበርክተዋል፡፡ ተጠናቀው አሳታሚ የሚጠብቁ ጽሑፎችም አሏቸው፡፡

 በምሕረት ሞገስ
 
< Prev   Next >