| ከግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ ከአራት... |
|
|
| Wednesday, 09 January 2008 | |
|
ከግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ ከአራት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኘ በተያዘው የበጀት ዓመት የግብርና ምርቶችን ወደ ውጪ በመላክ ከ434 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል፡፡ በተጠናቀቀው የ1999 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከተገኘው 1 ቢሊዮን ዶላር የግብርና ምርቶች ድርሻ 86.3 በመቶ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ እያደገ ሲሆን በ1999 የበጀት ዓመት ከግብርና ኤክፖርት 787.9 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ይህ ገቢ ከ1998 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ78.5 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለውም ተመልክቷል፡፡ የጠቅላላ የወጪ ንግዱ ከ1998 ጋር ሲነፃፀር በ16 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡት የግብርና ምርቶች 17 ዓይነት ሲሆኑ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚያስገኙት ቡና፣ የቅባት ሰብሎች፣ ቆዳና ሌጦ፣ ጫትና ጥራጥሬ ሲሆኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከተገኘው ገቢ 41.5 በመቶ ከቡና፣ 18.3 በመቶ ከቅባት እህሎች፣ 11.7 በመቶ ከቆዳና ሌጦ፣ 9.1 በመቶ ከጫት ፣ 6.9 በመቶ ጥራጥሬ ድርሻ አላቸው፡፡ ከሰብል ምርቶች ኤክስፖርት በ1999 ዓ.ም ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ ከሥጋና ከሥጋ ውጤቶች በ1998 ዓ.ም ከነበረው 18 ሚሊዮን ዶላር ወደ 15 ሚሊዮን ዶላር ቀንሷል፡፡ ለዚህም የእንስሳት በሽታ በምክንያትነት ተጠቅሟል፡፡ የቁም እንስሳት ኤክስፖርት በ1998 ከነበረው 25 ሚሊዮን ወደ 35 ሚሊዮን አድጓል፡፡ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ያለውን ሰፊ የእንስሳት አቅም ለመጠቀም ስትራቴጂ መንደፍ፣ የሰው ኃይል ልማትና የባለሙያ ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ በመረጃው ተገልጿል፡፡ ከግብርና ምርቶች የተገኘው ገቢ ከ1995 ጀምሮ በነበሩት ተከታታይ ዓመታት 274.3፣ 374.5፣ 545.3፣ 709.4 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን በ1999 የበጀት ዓመት 787.9 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ በዚህ አመት በመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ከተገኘው ገቢ ቡና በ127.8 ሚሊዮን ዶላር ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን ከቅባት እህሎች 47.8 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጫት 46.6፣ ከጥራጥሬ 43.9 ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች 40.1፣ ከወርቅ 37.5 ዶላር መገኘቱ መረጃው ይፋ አድርጓል፡፡ በቤዛዊት ስዩም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |