Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow "ለውጡን መቀበል አቅቷቸው...
"ለውጡን መቀበል አቅቷቸው... Print E-mail
Wednesday, 16 April 2008
"ለውጡን መቀበል አቅቷቸው ራሳቸው ለቅቀው የሄዱ አሉ"
አቶ ዳባ ደበሌ፣
የቡራዩ ከተማ ከንቲባ

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ሸዋ ዞን የምትገኘው የቡራዩ ከተማ የመሬት አሰጣጥና የአገልግሎት ችግር ነበረባት፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ኃላፊዎች ይታሰሩባት፣ ይቀያየሩባትና የሙስና ወንጀል ይፈፀምባት ነበር፡፡ በቡራዩ ጉዳይ ለማስፈፀም በደላላ በኩል መሄድ የተለመደ ነበር፡፡ አዲሱ የቡራዩ ካቢኔ ይህንን ለማስተካከል ምን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አሰግድ ተፈራ የከተማዋን ከንቲባ አቶ ዳባ ደበሌን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በምልጃ፣ በደላሎችና በጉቦ ካልሆነ በቡራዩ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ማግኘት አይቻልም ነበር፡፡ ቡራዩን መንግሥት ያውቃታል? እስከመባል ተደርሶ እንደነበር በተለያዩ መገናኛብዙሃን በተለያዩ ጊዜያት ተገል..ል፤

አቶ ዳባ፡
- ከዚህ በፊት በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የነበረው ችግር እጅግ በጣም ሰፊ ነበር፡፡ በዘመድ፣ በትውውቅና በገንዘብ ነበር የሚሠራው፡፡ በደላሎች ካልሆነ በስተቀር ጉዳይ ማስፈፀም አይቻልም ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ጉዳይ እናስፈፅማለን የሚሉ ተገልጋዩን ዘርፈዋል፣ አዘርፈዋል፡፡ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ያሉ የማዘጋጃ ቤቱን ሠራተኞች በጥቅማ ጥቅም በመያዝ ይሠሩ እንደነበር ይነገራል፤

አቶ ዳባ፡-
ደላሎችን የድላላ ሥራ አትሥሩ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ መሆን አለባቸው፡፡ ደላሎችን ሕገወጦች ናቸው እያሉ ከመኮነን ይልቅ የኢንተርፕሩነር ሺፕ ስልጠና ተሰጥቷቸው ሥራ እንዲፈጥሩ በማድረጋችን በለውጡ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርገናቸዋል፡፡ ችግሩ የግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የሲስተምም በመሆኑ ሰዎችን በማስተማርና ሲስተሙን በመቀየር ማስተካከል ይቻላል ብለን ሠርተን ተሳክቶልናል፡፡ በዚህ መሠረት ለባለጉዳዮች ችግራቸውን የሚፈታ የአሰራር ስርዓት ዘርግተን ተግባራዊ አድርገናል፡፡ በቡራዩ ጉዳይ አስፈፃሚ ነን የሚሉ ዛሬ የሉም፡፡

ሪፖርተር፡- የማዘጋጃ ቤቱ ሠራተኞችም ከሕገወጦች ጋር ይተባበሩ ነበር የሚሉም አሉ፤

አቶ ዳባ፡- የጥቅም ጉዳይ ስለሆነ የሚደግፏቸው ሠራተኞች ነበሩ፡፡ አብረው ለመጠቀም የመደጋገፍና አብሮ የመስራት ነገር ነበር፡፡ እሱን ሙሉ በሙሉ በአዲስ ሲሰተም ቆርጠነዋል፡፡ በአሰራር እንዳይገናኝ አድርገነዋል፡፡ አሰራራችንን ለማደናቀፍ የተደረገው ሙከራ ከፍተኛ ሥራ በመሥራት ዋጋ ቢስ አድርገነዋል፡፡ የሠራነው አሰራሩን ለማደናቀፍ የሞከሩትን ያለማቋረጥ ማስተማር ነው፡፡ በዚህም አብዛኞቹ ተባባሪ ሲሆኑ የቀሩት ተሸንፈዋል፡፡ አሰራሩን ኅብረተሰቡ ስለደገፈውና የተሸነፉትም በጣም ጥቂት በመሆናቸው ከአሁን በኋላ ወደ ቀድሞው አሰራር እንመለሳለን የሚል ጥርጣሬ የለኝም፡፡ አዲሱን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ በወሰኑ አስፈፃሚዎች እየተተገበረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመሬት አሰጣጡን በጣም የሚተቹ ነበሩ፤

አቶ ዳባ፡-
ቀደም ሲል መሬት የሚሰጠው በዘፈቀደ ነበር፡፡ ከየትኛውም ቦታ የሚመጡ በዘረጉት የራሳቸው መስመር ቦታ ያገኙ ነበር፡፡ ተመዝግበው ቦታ ሳያገኙ እስከ ስምንት ዓመት የቆዩ ነበሩ፡፡ መሬት ሳይዘጋጅ መሬት ለመመራት ገንዘብ ማስከፈል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ካቢኔዎ ችግሩን እንዴት እየፈታው ነው?

አቶ ዳባ፡-
የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለማዘጋጃ ቤቱ እንዳይቀርብ አድርገናል፡፡ ቦታ ጠያቂዎችና መሀንዲሶች በምንም ተአምር አይገናኙም፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ ቦታ ያዘጋጃል፡፡ ቀበሌዎች በሕዝብ ውሳኔ ቤት የሌላቸውን መርጠው ቦታ እንዲሰጥ ያቀርባሉ፡፡ በግል በእጣ የማከፋፈል ሥራ ተሠርቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀበሌ ደረጃስ በገንዘብ የመስራት ነገር አይፈጠርም?

አቶ ዳባ፡-
አይፈጠርም፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ መሬት ያዘጋጃል፡፡ ቀበሌዎች ሕዝብን ሰብስበው የመኖሪያ ቤት የሌላቸው ተመርጠው ቦታ እንዲሰጣቸው ያስወስናሉ፡፡ በአደባባይ እጣ ይወጣል፡፡ ካርታና ፕላን ሲሰጥም እጣ ለደረሳቸው ወዲያውኑ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የስም ዝውውር ለማድረግ የሞከሩ ሰልችቷቸው ትተውታል፡፡ በቡራዩ ማዘጋጃ ቤት ንብረት ሸጦና ገዝቶ ስም ማዘዋወር አይቻልም ይባል ነበር፡፡ ስም ለማዞር እስከ ስድስት ዓመት ፈጅቶባቸው አቤቱታ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ዛሬስ ይኸ ተቀረፈ?

አቶ ዳባ፡-
ውልና ማስረጃ ቀርበው ንብረታቸውን የሸጡና ንብረት የገዙ ስም ለማዞር ጠይቀው እስከ ስምንት ዓመት የፈጀባቸው እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የሲስተም ችግር ነው፡፡ መዝገብ ቤት መረጃ የማቀበል ችግር አለ፡፡ መዝገብ ከተገኘም በኋላ መዝገቡ የሚዘዋወርባቸው አሰልቺ የሥራ ሂደቶች ነበሩ፡፡ በአሰራሩ ኋላ ቀርነትና በነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት ኅብረተሰቡ ተማሮ ለደላላና ጉዳይ እናስፈፅማለን ለሚሉ ሲሳይ የሆነበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አሁን በተደረገው የአሰራር ማሻሻያ ስም ለማዘዋወር የሚመጡ አስፈላጊውን ሁሉ ካሟሉ በ40 ደቂቃ ውስጥ ሁሉንም ነገር ጨርሰው ስማቸውን አዘዋውረው ይሄዳሉ፡፡ ለአሰራሩ ያመች ዘንድ መሟላት ያለበት ሁሉ በግልፅ ተለጥፏል፡፡

ሪፖርተር፡- የቡራዩን ማዘጋጃ ቤት ተለውጧል ነው የሚሉኝ?    

አቶ ዳባ፡
- የስም ዝውውር የሚሰራው በአንድ ሰው፣ በአንድ መስኮት ነው፡፡ አዲሱ አሰራር እንደተጀመረ ወረፋ ነበር፡፡ አሁን ግን በቀን አንድና ሁለት ሰው የሚስተናገድበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ኧረ የሥራ ያለህ እያሉ ነው፡፡ ባለጉዳይ በቡራዩ ማዘጋጃ ቤት ከደቂቃዎች በላይ ሊቆይ አይገባም፡፡ በዚህም የተነሳ ከዚህ ቀደም በማዘጋጃ ቤቱ በር ላይ የነበረው ልግባ አትገባም ትንቅንቅ ዛሬ የለም፡፡ በሩ ክፍት ነው፡፡ ማንም ይገባል ይወጣል፡፡ አሰራሩ ከተቀየረ በኋላ ማዘጋጃ ቤቱ ጭር ብሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የግንባታ ፈቃድ በሚሰጥበት ክፍል የሚቀርበው ጥያቄ ሌላው የቡራዩ ማዘጋጃ ቤት መጥፎ ገጽታ እንደነበር የሚገልፁ ነበሩ፤

አቶ ዳባ፡-
ለመኖሪያ ቤት ቀደም ብዬ በዘረዘርኩት አሰራር መሠረት ካርታ፣ ፕላንና የግንባታ ፈቃድ የሚሰጠው በአንድ መስኮት ወዲያውኑ ነው፡፡ አገልግሎቶችን ከፋፍሎ መስጠት ተገልጋዮችን ከማጉላላቱ ሌላ ለተባለው ዓይነት ችግር ስለሚዳርግ አሰራሩ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል፡፡ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ከሆነ ዲዛይን ለማፅደቅና የግንባታ ፈቃድ ለመስጠት ስላለ ደቂቃ አይፈጅም፡፡ ቀደም ሲል የግንባታ ፈቃድ ለመውሰድ እስከ ስድስት ወር ይፈጅ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- "የችግሮች ሁሉ መጋዘን" የሚባለው መዝገብ ቤታችሁ በአዲሱ አሰራር ለውጥ ተደርጐበታል?

አቶ ዳባ፡-
ከፍተኛ ችግር የነበረው መዝገብ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት መዝገብ ቤቱ ኮምፒተራይዝድ መሆን እንዳለበት ታምኖ ጨረታ ወጥቷል፡፡ ሥራው በቅርቡ ይጀመራል፡፡ ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- መዝገብ ቤት ለሚሰጠው አገልግሎት ሰዓት ተመድቦታል?

አቶ ዳባ፡- አሁን ባለው ሁኔታ ለመዝገብ ቤት ለራሱ የጊዜ ሰሌዳ የለውም፡፡ ነገር ግን የተጠቀሱት አገልግሎቶች ሲሰጡ ከመዝገብ ቤት መረጃ እየወጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ለስም ዝውውር 40 ደቂቃ መድበናል፡፡ መዝገብ ቤት የሚፈጀው ጊዜም ግምት ውስጥ ተካትቶ ነው፡፡ ሌሎች አገልግሎቶች ላይም ተመሳሳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎቶች በተጀመሩበት መንገድ እንዲቀጥሉ ቁጥጥር የሚደረገው እንዴት ነው?

አቶ ዳባ፡
- መሬት በየቀበሌው እንዲሰጥ ስናደርግ መሬት የሚያዘጋጀው ክፍልና መሬት የሚዘጋጅለት አካል አይተዋወቁም፡፡ አራት የፊት ለፊት መስመር (Front line) ሠራተኞች አሉ፡፡ የኢንቨስትመንት፣ የውልና ማስረጃ፣ የግንባታና ኮንስትራክሽን ዲዛይን ማረጋገጫ ናቸው፡፡ የፊት መስመር ሠራተኞች የኋላ መስመር ሠራተኞችም አሏቸው፡፡ የራሳቸው ቻርተር አላቸው፡፡ እያንዳንዱ መስመር ሲሰራ የራሱ አፈፃፀም መመዘኛ አለው፡፡ መመዘኛው ደግሞ ጊዜ ነው፡፡ አገልግሎት ፈላጊው ለጠየቀው አገልግሎት ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በላይ ከቆየ የአገልግሎት ሰጪው አፈፃፀም በዚያ ይለካል፡፡

ሪፖርተር፡- ቻርተሩ ምንድነው?

አቶ ዳባ፡-
ቀደም ሲል የዘረዘርኳቸው የአገልግሎት ዓይነቶች የመሬት አስተዳደርና የግንባታ ሥራዎች አፈፃፀም ሂደት በሚል ዘርፍ ውስጥ የሚስተናገዱ ናቸው፡፡ በአፈፃፀም ሂደቱ ውስጥ ባለ አንድ አገልግሎት ውስጥ የሚሰራ ሠራተኛ ለሂደቱ በተዘጋጀው ቻርተር ላይ ይፈርማል፡፡ የሚፈርመውና ውል የሚገባው የአገልግሎቱን ዓይነት ጠቅሶ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ እጨርሳለሁ በማለት ነው፡፡ በየዕለቱ ከ11 እስከ 11፡30 የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ይካሄዳል፡፡ በግምገማው ሥራቸውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ያልጨረሱ ካሉ ይጠየቃሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በአግባቡ የሚሰሩትስ?

አቶ ዳባ፡-
በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት የማይሰሩ የሚጠየቁትን ያህል በተቀመጠው አግባብ፣ በገቡት ውል መሠረት የሚሰሩ ሠራተኞች ይሸለማሉ፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ሲስተሙ ሲሆን ቡራዩ በዚህ ረገድ ለሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች ምሳሌ ሆና ልምድ በማካፈል ላይ ናት፡፡

ሪፖርተር፡- ግብር አሰባሰቡም ያማርር ነበር፤

አቶ ዳባ፡- ግብር ከፋዮች ማዘጋጃ ቤት መጥተው መቆም የለባቸውም፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ግብር ለመክፈል ተመላልሰው ሲሰለቻቸው ይተውታል፡፡ በዚህ አሰራር ተገልጋዮች ለቅጣት ይዳረጋሉ፡፡ መንግሥትም ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በወቅቱ ሳያገኝ ይቀራል፡፡ አሁን ባለው አሠራር ግብር ከፋዮች በየቀበሌው መክፈል ይችላሉ፡፡ በሚቀርባቸው ባንክ፣ በቁጥራችን ከፍለው ቢል ማምጣት ይችላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማዘጋጃ ቤቱ ውስጥም በደቂቃ ውስጥ የሚያልቅ አሰራር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በቡራዩ ቀደም ሲል የአመለካከት ችግር እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት ተገል..ል፡፡ ለውጡ በአመለካከት ችግር ተቀባይነት አያገኝም የሚሉም አሉ፤

አቶ ዳባ፡-
አንድ ለውጥ ሲመጣ ለውጡን የሚደግፉና የሚቃወሙ ይኖራሉ፡፡ በአሰራራችን ቅድሚያ አመራሩ መቀየር አለበት፡፡ አመራሩ ከተቀየረ ከስር ያለው በየደረጃው ይቀየራል፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር ለውጡ ኅብረተሰቡን የሚጠቅም መሆኑን ማሳየቱ ላይ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ለውጡ እንደሚጠቅም ካመነ ለውጡን ማንም ሊያቆመው አይችልም፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች አገልጋዮች ናቸው፡፡ ደመወዝ የሚከፍላቸው ሕዝብ ነው፡፡ የቀጠረ አካል የመቆጣጠር ስልጣን አለው፡፡ በቡራዩ የነበረው የአመለካከት ችግር ይህንን ያለመረዳት  ይመስለኛል፡፡ ቀጣሪ አካል አገልግሎት የማግኘት መብት አለው፡፡ ይገመግማል፡፡ ይህንን አሰራር ማስፈን ደግሞ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት ሲሆን በተዋረድ እስከ ቀበሌ ድረስ ተግባር ላይ ለማዋል በየደረጃው ያሉት በቁርጠኛነት ሊሰሩ ይገባል፡፡ የሕዝብ አለቃ መሆን አይቻልም፡፡ በየደረጃው ያለን የሕዝብ አገልጋዮች መሆናችንን ስንረሳ ነው ችግሩ የሚፈጠረው፡፡

ሪፖርተር፡- ለውጡን አንቀበልም ያሉ አሉ?

አቶ ዳባ፡-
ለውጡን መቀበል አቅቷቸው ራሳቸው ለቅቀው የሄዱ አሉ፡፡ ማንም ውጡ አላላቸውም፡፡ ሲስተሙ ራሱ ነው ያስወጣቸው፡፡ ሲስተሙ ቀልጣፋ አሰራርን በንፁህ አእምሮና በንፁህ እጅ እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡ ሲስተሙ የሕዝብ አገልጋይነትን አምኖ መቀበልን ይጠይቃል፡፡ ይህንን ለማድረግ ገና ስልጠና ስንጀምር በውይይቱ ተደናግጠው ለቀው የሄዱ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለቀው የሚሄዱ ካሉ የሰው ኃይል እጥረት ችግር አላጋጠማችሁም?

አቶ ዳባ፡- በሂደት ልንማረው ያልቻልነው ትልቁ ችግር ቀና አለመሆንን ነው፡፡ ሲስተሙ በየትኛውም ደረጃ ላይ የምንገኝ አመራሮችም ሆኑ ሠራተኞች ቀና መሆንን ይጠይቃል፡፡ የተደረገውም በሲስተሙ አምነው በቀናነት የሚተገብሩት ላይ በመድከም አቅማቸውን ማጐልበት፣ ማስተማር፣ ስልጠና መስጠት ነው፡፡ ከማስትሬት ጀምሮ በተለያዩ ደረጃዎች እያስተማርናቸው ያሉ አሉ፡፡ በየጊዜው ስልጠናም ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥራ የሚቀሩ ሠራተኞች የሚተኩበት ሥርዓት አለ?

አቶ ዳባ፡-
በአዲሱ አሠራር ሠራተኛ ከሥራ አይቀርም፡፡ አንድ ሠራተኛ ከሥራ ቀረ የሚባለው ሥራው ሳይሠራ ሲቀር ነው፡፡ በሥራ አፈፃፀም ሂደት ቻርተሩ ላይ አንድ ሠራተኛ ቢቀር ማን ይተካዋል የሚለው አስቀድሞ ተቀምጧል፡፡ ማን ማንን ይተካል የሚለው ስለሚታወቅ ሥራ ክፍት የሚሆንበት አጋጣሚ በፍፁም የለም፡፡ በማዘጋጃ ቤታችን ሠራተኛ ቀርቷል በሚል የሚቋረጥ አገልግሎት የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ለባለሀብቶች በተለይ የተፈጠረ አዲስ አሰራር አለ?

አቶ ዳባ፡
- አንድ አልሚ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ መሬት እንዲሰጠው ሲጠይቅ በ3 ሰዓት ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ሕጋዊ መረጃዎች ከማዘጋጃ ቤቱ ያገኛል፡፡ ከባለሀብቱ የሚጠበቀው በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ወይም ከስድስት ወር ባነሰ ጊዜ ወደ ተግባር መግባትን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መሬት ወስደው የማያለሙ አሉ?

አቶ ዳባ፡
- ቁጭ ብለው ኪራይ የሚሰበስቡ ባለሀብት ነን የሚሉ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት ነው ኪራይ የሚሰበስቡት?

አቶ ዳባ፡-
ስኬታማ ባለሀብት እንደሆኑ ገልፀው መሬት ከወሰዱ በኋላ የወሰዱትን መሬት በማስቀመጥ ለመሸጥ ሌላ ባለሀብት ያፈላልጋሉ፡፡ ለመሸጥ ይሯሯጣሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት በዝምድናና በትውውቅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ከማጭበርበር ተለይቶ አይታይም፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን የመለየት ሥራ እየሰራን ነው፡፡ የነጠቅናቸውም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የውጪ ባለሀብቶች በምን ዓይነት መንገድ እየተስተናገዱ ነው?

አቶ ዳባ፡-
የውጪ ባለሀብቶች ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ በተለይ ከቱርክ ባለሀብቶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ቢዩቼክሜሽ ከምትባል የቱርክ ከተማ ጋር የእህትማማችነት ስምምነት አድርገናል፡፡ በቅርቡ ያካሄድነውን ጉብኝት ተከትሎ 100 የሚደርሱ ባለሀብቶች በቡራዩ ለማልማት ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ካፒታላቸው ይታወቃል?

አቶ ዳባ፡
- ለጊዜው አይታወቅም፡፡ የሚታወቀው ከአንድ ወር በኋላ አገር ውስጥ ሲገቡ ነው፡፡ አስቀድሞ የመጣ አንድ የቱርክ ኩባንያ 30 ሚሊዮን በሚደርስ ካፒታል ወደ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለሀብቶቹ ቢመጡ ለማስተናገድ አቅሙ አላችሁ?

አቶ ዳባ፡-
የኢንዱስትሪ መንደር አዘጋጅተናል፡፡ እዚያ ባገኘነው ልምድ ማስተካከል የሚገባንን እናስተካክላለን፡፡ በዚህ ረገድ ሊረዱን ስለተስማሙ እናሻሽለዋለን፡፡ እነሱን ለማስተናገድ ብቻ ሳይሆን ሌላም የኢንቨስትመንት ጥያቄ ካለ ለማስተናገድ ዝግጁ ነን፡፡
 
< Prev   Next >