Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow አህያ ባረገው
አህያ ባረገው Print E-mail
Wednesday, 16 April 2008
አምነው የጫኑበት
ፈቅደው ያሸከሙት
"አደራ" ነው ያሉት
የስልጣን ሽልጦ የሹመት ዘመራ
ለተጫነው እንጂ ለጫኞች ካልሰራ
ካረገው ተጫኙ - ውሃ፣ ልብስ፣ እንጀራ
ርቦት ከጎረሰው
ጎርሶት ከጠገበው
በርዶት ከደረበው
ደርቦት ከሞቀው
ጠምቶት ከመጠጠው
መጦት ካሰከረው
ምናለበት እግዜር
አዙሮ ቢጥለው!!
ወይም በጥበቡ ምናል ቢለውጠው
"እፍ" ያለውን ትንፋሽ መልሶ ቢነጥቀው
ምናል ቢአሳድገው! ምናል ቢመርቀው!
ሰውነቱን ገፍፎ አህያ ቢያደርገው!!

(ጌትነት እንየው፣ እውቀትን ፍለጋ፣ 1994)

ቁጣ
 
የፕሌቶ ደቀመዝሙር የነበረው አሪሰቶትል ቁጣን ሲገልፀው ..ማንም ሰው መቆጣት ይችላል፤ መቆጣት ቀላል ነውና፡፡ ነገር ግን ተገቢውን ሰው፣ በተገቢው ደረጃ፣ በትክክለኛው ሰዓት ለትክክለኛው ዓላማ፣ በትክክለኛው መንገድ መቆጣት ግን በማንም ሰው ውስጥ የሌለ ችሎታ ብቻ ሳይሆን የማይመች ነው.. ብሎታል፡፡

ታላቋ አሜሪካ እንኳ በራሷ ቀርቶ እሷን በተወዳጁትም ይደርሳል ብላ የማትጠብቀው በትር በሴፕቴምበር 11/2001 ባረፈባት ማግስት አንድ አሜሪካዊ ወጣት "አንድ ወይም ሁለት አገር ድምጥማጡን ልናጠፋ ይገባል" በማለት በንዴት የተንገበገበ አስተያየት በቴሌቪዥን ሲሰጥ ታይቷል፡፡ ነገር ግን ወጣቱ ድምጥማጥ የሚጠፉትን አገሮች ስም አልጠቀሰም፡፡ የሮማው ጳጳስ ደግሞ "ፍርድ እንጂ በቀል አያስፈልግም" በማለት የአሜሪካን ቁጣ ለማብረድ ሞከሩ፡፡ ጳጳሱ ይህን ቢሉም በፍርድና በበቀል መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያብራሩ የጠየቃቸው ሰው አልነበረም፤ እሳቸውም ሊያብራሩ አልሞከሩም፡፡

(ኃይለጊዮርጊስ ማሞ፣ ጥበብ ከጲላጦስ፣ 1997)

ነጥብ ለማግኘት


ሴት ልጅ በተፈጥሮዋ እንክብካቤን ትወዳለች፡፡ አንተም ከእርሷ ጋር እስካለህ ድረስ ልትሰጣት የሚገቡ ክብርና እንክብካቤዎች አሉ፡፡ ከፊት በመቅደም በርና መስኮት መክፈት የአንተ ድርሻ ይሁን፡፡ ይህ በጣም ያስደስታታል፡፡

መቀመጥ ስትፈልጉ ከፊቷ ቅደምና ወንበር ስበህ አስቀምጣት፡፡ በመንገድ ዳር ስትሄዱ ሁልጊዜም በመኪኖቹ በኩል ያለውን ጎን ተጠቀም፡፡ ለምን እንደዚያ እንደምታደርግ ይገባታል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ምናልባት መኪና መንገዱን ስቶ ቢመጣ እርሷን ከልለህ ራስህን መስዋዕት ለማድረግ ማቀድህን አስረዳት፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ሴቶች ለምትሰጣቸው ሽፋንና እንቅስቃሴ ሁሉ ነጥብ ይይዙልሃል፡፡

(ዳዊት እና ጥቁማስት፣ ጦበሳ፣ 1999)

ሽልማት

አልፍሬዱ ኖቤል ምንም እንኳ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት የሰበሰበ ባለፀጋ ሰው ሆኖ ቢኖር መንፈሱ እረፍትን እንዳላገኘ ይታይበት ነበር፡፡ ስለዚህ ወደ ሠላሳ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ኩሮን ትቶ ሲሞት ዓለም ሰላምን እንድታገኝ የሚረዳ ማናቸውንም ሥራ ለሠሩ ሰዎች ሁሉ ባመት ባመቱ 5 ዓይነት የገንዘብ ሽልማት እንዲሰጣቸው ተናዘዘ፡፡ ከእነዚሁም 3ቱ ሽልማቾች በፊዚክስ፣ በሕክምና ዕውቀት ለሰው ዘር ጠቃሚ  ሥራ ለሰሩ ሰዎች የሚሰጥ ሲሆን 4ኛው በደራሲነት ጠቃሚ አሳብ ፈጥሮ ላቀረበ የሚሰጥ ነው፡፡ 5ኛው ደግሞ በሕዝቦች መካከል የወንድማማችነት መንፈስ ለመመሥረት ተግቶ ሊሰራ ወይም ደግሞ የጦር ኃይል እንዲቀነስ ወይም ጨርሶ እንዲቀር ላደረገ ወይም የሰላም ጉባኤ እንዲፀና ለማድረግ ለደከመ የሚሰጥ ነው፡፡ የመጨረሻው 5ኛው "የሰላም ሽልማት" ተብሎ ይጠራል፡፡

 (ከበደ ሚካኤል፣ የሥልጣኔ አየር፣ 1952)

ግሎባላይዜሽን ማለት ምን ማለት ነው?

ስለ ግሎባላይዜሽን በየጊዜው በጣም ብዙና ሰፊ ትንተናዎች ይሰጣሉ፡፡ ስለሆነም የሚሰጠው ትርጉም ብዙና የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡

ብዙዎች በአለምአቀፍ ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የካፒታል ፍሰት እድገት ምክንያት የተፈጠረ የብሔራዊ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት መስተጋብር ወይም ውህደት ያለው ዋና የኢኮኖሚ ሂደት ነው ይላሉ፡፡

ይሁንና ፈጣን የሆነው ድንበር ዘለል ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ቴክኖሎጂያዊ ልውውጥ የግሎባላይዜሽን ውጤት ነው የሚሉም አሉ፡፡

የሶሲዎሎጂ ባለሙያ የሆኑት አንቶኒ ጊዲነስ "ግሎባላይዜሽን ማለት ጊዜና ቦታ ሳይለይ በዓለም ደረጃ ፈጣን በሆነ በተመሳሳይ የግንኙነት የእውቀትና የባህል ልውውጥ በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄድበት ነው" ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ግራ አክራሪ የሆኑት ፀረ ግሎባላይዜሽን አቋም ያላቸው ፍፁም በተለየ መንገድ ይተረጉሙታል፡፡ በማይወክሉ ከፍተኛ ብሔራዊ የንግድ ሸሪኮችና የባንክ ተቋማት ተጽዕኖ ዓለምን ወደ አንድ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት የመቀየር ሂደት ነው" ይላሉ፡፡

(አትርሳው ጣሰው፣ የብልጽግና ቁልፍ፣ 1999)

እጆች

እጆች የማይሰሩት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ብዙውን ሥራቸውን የሚሰሩት ከአይን ጋር በመተባበር ነው፡፡ ለምሳሌ ብንናገር አይንና እጅ የአእምሯችን ወይም የነብሳችን ሁለት ስጋዊ ቅርንጫፎች ናቸው ወይም የአንጎላችን ችሎታዎች ወይም ሰልጣኞች ናቸው፡፡ ወይም ወኪሎቹ ናቸው፡፡ እሱ እዚያ እውስጣችን እንደ ተደበቀ ነው አይወጣም፡፡ ከደሳሳ ጎጆ አንስቶ እስከ አክሱም ሐውልት እስከ ላሊበላ ቤተክርስቲያናት በማን ተሰሩ? በእጅ፡፡ የሰው ልጅ ከጋሪ ሰረገላ አንስቶ በባቡር አድርጎ በአውሮፕላን አልፎ በሮኬት መጥቆ ጨረቃን ጎብኝቶ ለመመለስ ያስቻለውን ቴክኖሎጂ ማን ሰራው? እጆች፡፡

(ስብሐት ገ/እግዚአብሔር፣ 2- እግረ መንገድ፣ 1987)

የትምህርት ዓላማ

ሰው ለኑሮው የሚያገለግሉት ሁለት መሣሪያዎች አሉት፡፡ አንደኛው ሕሊናው ነው፡፡ ሁለተኛው ክንዱ ነው፡፡ እኒህ ሁለት መሣሪያዎች በተፈጥሮ ሁኔታቸው እምብዛም ሊረዱት አይችሉም፡፡ ሰው በንጹሕ ሰብዓዊ ተምኔት መሠረት ተመችቶት ተደላድሎ በሰላም ለመኖር ይችል ዘንድ ሕሊናውና ክንዱ፣ በትምህርት ረድኤት ማደግ መዳበር መሰልጠን አለባቸው፡፡ በዚህ ዘዴ ብቻ ከምኞቱ ቦታ ሊደርስና ፍላጎቱን ሁሉ ለማርካት ይችላል፡፡ ምን ጊዜም በየትም አገር በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ የሚደረገው መሻሻል የሚገኘው ከትምህርት ነው፡፡ የትምህርት መነሻ ምክንያቱ በአጭሩ ይህ ነው፡፡ ትምህርት መጀመሪያ ሰብዓዊ ነው፡፡ ሰው ከሙሉ የሰውነት ማዕረግ የሚደርሰው በትምህርት ነው፡፡ ሁለተኛ ትምህርት መክሊታዊ ነው፡፡ በዚህ መክሊት መሪነት በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ተከፋፍለው ከሚገኙት ሥራዎች ለአንዱ መሰልጠን መዘጋጀት አለበት፡፡ ሦስተኛው ትምህርት አዲስ ነገር ከማወቅ ከመመራመር የእስካሁኑን የዕውቀት ድንበር አልፎ ለመሄድ ከመጣጣር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እኒህን ሶስት የትምህርት ዓላማ ጠባዮች ፈረንጆች Humanistic Professional Scientific ይሏቸዋል፡፡

(እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ 1956)

ማንም መንገዳቸው ላይ አይቁም

አፄ ምኒልክ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ አቡነ ማቴዎስ፣ ኦኔሲሞስ ነሲብ የመጣበትን ጉዳይ ለንጉሡ ያቀርብ ዘንድ ሁኔታውን አመቻቹ፡፡ ኦኔሲሞስም ወደ ወለጋ ዘልቆ ለማስተማር የሚያስችለውን ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ንጉሡን ጠየቀ፡፡ ከመጀመሪያው እትም አንዱ የሆነው የኦሮምኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለአፄ ምኒልክ ገፀ በረከት አቀረበላቸው፡፡ ንጉሡም በደስታ ተቀበሉ፡፡ ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስንም ባልደረባ በመስጠት የሚገጥመውን ችግር በእርሳቸው አማካይነት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ተከታዩን የይለፍ ደብዳቤ ሰጧቸው፡፡

ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ይህን ደብዳቤ ይዞ ደጃዝማች ገብረ እግዚአብሔር አገር ለሚያቀናው ኦኔሲሞስ፣ ከርሱ ጋር ላሉ አስር ሰዎችና ሦስት ጠባቂዎቻቸው ፈቃድ ሰጥተናቸዋልና ማንም መንገዳቸው ላይ አይቁም፡፡

(ሰሎሞን ጥላሁን፣ ደማቆቹ፣ 2000)

ገራገር

በመኪና ማጠቢያ ውስጥ አአልማዝ ተገኘ

በሩሲያ መኪና በሚያፀዳ ድርጅት ውስጥ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ 475..400 ዶላር የሚያወጣ ተንጠልጣይ አልማዝ ሲገኝ አድናቆት እንደፈጠረ ሮይተርስ ከፒተርስበርግ ዘግቧል፡፡

የመኪና ማጽጅያ ድርጅቱ ባለቤት ቭላድሚር ሻፒሮ በሩሲያ ሰሜናዊ ክፍል ከምትገኘው ፒተርስበርግ ከተማ ለሮይተርስ ሲገልጽ "ጌጣጌጡን መጀመሪያ አገኘሁት፡፡ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ስለማላውቅ የጌጣጌጥ ባለሙያ አምጥቼ ሳሳየው 475,400 ዶላር ዋጋ እንዳለው ነገረኝ" ብሏል፡፡

ቭላድሚር አክሎም "የማጽጂያ ማሽኑ ጫፍ ላይ ተንጠልጥሎ የተገኘውን አልማዝ ዋጋ ሳስበው ሰዎች ባለማስተዋል ትልቅ ዋጋ ያለውን ነገር እንደምናጣ ተገንዝቤአለሁ" ብሏል፡፡

በመጨረሻም ለትክክለኛ ባለቤቱ ንብረቱን ለመመለስ ይረዳ ዘንድ ስለ አልማዝ ከዚህ በላይ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡

ቢራ ወዳድ ግብር ከፋዮች

ሙዚቃው ይጮሃል፡፡ የቢራ ጠርሙሶች ድምጽ ያንቃጭላል፡፡ የዳርት ተጨዋቾች ግርግር ያስተጋባል፡፡ ከእነዚህ 10 ጫማ ርቀት ላይ ሥራ ይሰራል፡፡

፣ሰርቲፋይድ፣ የሕዝብ የሂሳብ ባለሙያ ለሆነው ካርሚን ሶደራ ምሽቱ መደበኛ የሥራ ሰዓቱ ነው፡፡ ሶደራ ፣ታቨርን ግብር፣ ን እ.ኤ.አ በ2005 ነበር ያቋቋመው፡፡ የአሜሪካ የገቢ ግብር መክፈያ የመጨረሻው ቀን ከመጠናቀቁ ከ10 ሳምንት በፊት ጀምሮ በሳምንቱ የሥራ ሰዓት ምሽት እንዲሁም ቅዳሜና እሑድ ከሰዓት በቡና ቤት ውስጥ በመሆን አገልግሎቱን ይሰጥ ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልክ አገልግሎት የሚሰጥ ሌላ ሰው አያውቅም፡፡

ሶደራ "ሁሌም ለሰዎቹ ቢራችሁ የታለ? እኔ አንድም አልነካም እናንተ ግን እንደ ልባችሁ እላቸዋለሁ" ብሏል፡፡

ሶደራ በቡና ቤቱ አንድ ጥግ ላይ ተንቀሳቃሽ ኮምፒውተሩን፣ የግብር ደረሰኙንና መብራቱን በመያዝ ተቀምጦ የተደረደሩትን ደንበኞች አንድ በአንድ ዶሴአቸውንና መዛግብታቸውን እየተቀበለ ያስተናግዳል፡፡ እነሱም ቢራቸውን እየተጎነጩ የጉዳያቸውን እልባት ይጠብቃሉ፡፡

የስንፈተ ወሲብ መድሃኒት ያጭበረበረው ተያዘ

ሻንጋይ ኬሚካል የተባለው ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ባለፈው ሐሙስ ሁለት ዓመት ተፈርዶበት ወደ ዘብጥያ የተወረወረው የስንፈተ ወሲብ መድኃኒት የሆነውን ቪያግራን በማስመሰል የውሸት መድኃኒቶችን በኢንተርኔት አማካኝነት እየሸጠ ስለነበር መሆኑን የቻይና ዜና አገልግሎት ከሻንጋይ ከተማ ዘግቧል፡፡

ዩርሀ እ.ኤ.አ በ2006 እና በ2007 14,030 የተጭበረበሩ መድሃኒቶችን በውጭና በሻንጋይ ለሚገኙ ደንበኞች በመሸጥ 8,585 ዶላር አትርፏል፡፡ የታሰረው ባለፈው ነሐሴ ወር ነበር፡፡

ቪያግራ ለገበያ የሚቀርበው ፊዘር በተባለው የአለማችን ቁጥር 1 የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ነው፡፡ የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ቪያግራን ለስንፈተ ወሲብ ፍቱን መድሃኒት እንደሆነ ማረጋገጫ የሰጠው እ.ኤ.አ በ1998 ነው፡፡

ተማሪው ፣ታጅ መሐል፣ ላይ ራቁቱን ታየ    

አንድ የሆላንድ ተማሪ በሕንድ ታሪካዊ ቦታ ታጅ መሐል ላይ ብልቱን በግልጽ እያሳየ የሙዚቃ ክሊፕ በመስራቱ ውዝግብ ቀሰቀሰ፡፡
 
የተማሪው ት/ቤት ዳይሬክተር በሆላንድ የሕንድ አምባሳደርን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ሮተርዳም የሚገኘው ዩሮ ኮሌጅ ተማሪውን የት/ቤቱን መልካም ሥምና ዝና በማጥፋቱ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እያሰበ መሆኑም ተዘግቧል፡፡

ወጣቱ ተማሪ በክሊፑ ላይ ከሱሪው ብልቱን ሲያወጣ በግልጽ የሚታይ ሲሆን የእሱን ፈገግታና ሳቅ ተከትሎ የታጅ መሐልን ወራጅ ውሃ ይከተላል፡፡

የኮሌጁ የሕንድ ጉብኝትን ተከትሎ የተሰራውን ክሊፕ እንዳወቁ የት/ቤቱ አስተዳዳሪዎች ተማሪውን አግደዋል፡፡
 
< Prev   Next >