Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow "የአፍሪካ መሪዎች ፣እኔ ብቻ...
"የአፍሪካ መሪዎች ፣እኔ ብቻ... Print E-mail
Wednesday, 16 April 2008

"የአፍሪካ መሪዎች ፣እኔ ብቻ አውቃለሁ፣ የሚል አባዜ አላቸው"
አቶ ገብሩ ገብረማርያም

አቶ ገብሩ ገብረማርያም፣ በኢፌዴሪ የሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት ዋና ተጠሪ ናቸው፡፡ የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል እንዲሁም የንግድ፣ የጉምሩክና የሕዝብ ፍሰት ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ በቅርቡ በዚምባብዌ በተካሄደው ምርጫ በፓን አፍሪካ ፓርላማ ተወክለው ለመታዘብ ችለዋል፡፡

አቶ ገብሩ ፓርቲያቸው ከምርጫ ሂደቱ ራሱን በማግለሉና በዚምባብዌ ምርጫ ዙሪያ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአካባቢና ከማሟያ ምርጫው ኢዴኅህ ራሱን ማግለሉ የዴሞክራሲያዊ ሂደቱን አይጎዳም?

አቶ ገብሩ፡- ይጎዳል፡፡ ነገር ግን አማራጭ ስታጣ የምታደርገው ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜግነቴም ሆነ እንደ ኢዴኀህ አባልነቴ አዝናለሁ፡፡ ብዙ ነገሮች አይናችን ስር እየተደረጉ እስከዛሬ ምርጫው ውስጥ እየገባን ነበር፡፡ አንድም ጊዜ ምርጫው አልጋ ባልጋ ሆኖልን አያውቅም፡፡ ከዛሬ ነገ ይሻሻላል እያልን እየታገልን ነበር፡፡ የአሁኑ ግን ያፈጠጠ ያገጠጠ የሕግ ጥሰት ሲሆን ነው ኢዴኅህ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡ ለምሳሌ አምስት አምስት የምርጫ ታዛቢዎች ተቃዋሚዎቹ በደብዳቤ ተጠርተው በተገኙበት መመረጥ እንዳለባቸው በአዋጅ የተደነገገ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ያለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ የምርጫ ታዛቢዎችን መረጠ፡፡ ይሄ ሲደረግ የምርጫ ቦርድስ ለምን ይቀበላል? ባለፈው ምርጫ በአስፈፃሚነት ያጠፉና የተቀጡ ሰዎች በድጋሚ እንዴት አስፈፃሚ ይሆናሉ? እነዚህና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ከአቅም በላይ በመሆናቸው ከምርጫው ራሳችንን ለማግለል ተገደናል፡፡ ይህን ከማድረጋችን በፊት ጉዳዩ እንዲስተካከል ብዙ ማሳሰቢያ ለምርጫ ቦርድም ለመንግሥትም ሰጥተናል፡፡ በፓርላማ ከኢሕአዴግ በመቀጠል ብዙ መቀመጫዎች ቢኖሩንም በመገናኛ ብዙሃን የተሰጠን የአየር ሰዓት በጣም ትንሽ ነበር፡፡ ለዚህ ቅሬታችን የተሰጠ ምላሽ አልነበረም፡፡ 51 የፓርላማ ወንበር ያለን ቢሆንም በ12 ወንበር ነው የአየር ሰዓት የተሰጠን፡፡ ለምን እንዲህ እንደተደረገ አልገባንም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቀሪዎቹ አባላት የኦብኮ አባላት ናቸው፡፡ ኦብኮ ደግሞ ከኢዴኀህ ራሱን አግልሏል የሚል ክርክር አለ፤

አቶ ገብሩ፡- የእኛን አባላት ስምና ፊርማ እኮ ለምርጫ ቦርድ ሰጥተናል፡፡ ሰዎቹም ያሉት አሁንም ፓርላማ ውስጥ ነው፡፡ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የፓርላማው አፈ ጉባኤ ጉዳዩን በሚገባ ያውቃል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ከተመዘገቡበት ፓርቲ መቀየር ተከልክሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀየሩ ሰዎች ግን አሉ?

አቶ ገብሩ፡- ከአቶ ቶሎሳ ተስፋዬ (ኦብኮ) ጋር አንድ የፓርላማ ተመራጭ ብቻ እንዳለ ነው የምናውቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዴኀህ ራሱን ከምርጫ ያገለለው እንደማያሸንፍ ሲረዳ ነው የሚሉ አሉ፤

አቶ ገብሩ፡- ይህን የሚሉ ሰዎች መነሻ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ 20"000 እጩዎች እኮ አቅርበናል፡፡ በዚህ ወከባ ውስጥ ይህን ያህል እጩዎች ያቀረበ ፓርቲ ያሸንፋል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ በምርጫ 97 ሕዝባችንን እንዴት ከጫፍ ጫፍ እንደምናንቀሳቅሰው አሳይተናል፡፡ ያውቁናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሂደቱን ተቋቁማችሁ ብትጨርሱት አይሻልም ነበር?

አቶ ገብሩ፡- አንችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ገብሩ፡- ከዚህ በኋላ ነው ፋይዳውን የምናየው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ወገኖች ኢሕአዴግን በምርጫ ከስልጣን ማስወገድ ስለማይቻል ሌላ አማራጭ ይፈለግ ይላሉ፡፡ የሕብረት ከምርጫ ራሱን ማግለል ከዚህ ጋር ይገናኛል?

አቶ ገብሩ፡- አይገናኝም፡፡ በሰላማዊ ትግሉ እንቀጥላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫ ራሳችሁን ስታገሉ ከሰላማዊ ትግሉ ራሳችሁን እያገለላችሁ አይደለም?

አቶ ገብሩ፡- አይደለም፡፡ ከዚህ ምርጫ ራሳችንን ብናገልም በሀገራዊ ምርጫ ያሸነፍናቸውን የፓርላማ መቀመጫዎች አሁንም እየተጠቀምንባቸው ነው፡፡ ከ2002 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ ራሳችንን አገለልን ማለት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በ2002 ዓ.ም የተሻለ ምርጫ ይኖራል?

አቶ ገብሩ፡- የፖለቲካ ሂደቱን መሻሻል፣ የእኛን ጥንካሬ፣ የአባላት ሁኔታ የመሳሰለውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የምናየው ይሆናል፡፡ የበለጠ አቅም እንገነባለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን አቅም የላችሁም?

አቶ ገብሩ፡- የበለጠ አቅም ነው ያልኩት፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የተካሄደው የዚምባብዌ ምርጫ ለመመልከት በታዛቢነት እንደሄዱ ሰምቻለሁ፡፡ ማንን ወክለው ነው የሄዱት? የታዛቢ ቡድኑስ አባላት እነማን ነበሩ?

አቶ ገብሩ፡- የፓን አፍሪካን ፓርላማ የምርጫ ታዛቢ ቡድን አባል ነኝ፡፡ በመጀመሪያ የታዛቢ ቡድኑ አባላት በጅዋንስ በርግ ለሶስት ሣምንት ስልጠና ወስደናል፡፡ ቀጥሎም ወደ ዚምባብዌ ሄደን ለሁለት ቀናት ያህል ምርጫው ከሚመለከታቸው ወገኖች ከዚምባብዌ ምርጫ ኮሚሽን፣ ከአገሪቱ ፀጥታና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ውይይት አካሂደናል፡፡ ውይይቱ ስለ ዚምባብዌ አጠቃላይ ስእል ለማግኘት ረድቶናል፡፡ ከዚያ በኋላ ከዋና ከተማው ሐራሬ ራቅ ወደሚለውና ትልቁ የዚምባብዌ ጠቅላይ ግዛት ወደ ሆነው ማካቢሲላንድ ነው የሄድኩት፡፡ ማካቢሲላንድ ትልቅ ክፍለ ሃገር ከመሆኑ የተነሳ ሰሜንና ደቡብ ተብሎ ለሁለት የተከፈለ ነው፡፡ እኔ የሄድኩት ዋንጌ የሚባል የሰሜኑ ከተማ ስለሆነ ይህንን ማዕከል አድርገን ነው የተንቀሳቀስነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዚምባብዌን ምርጫ እንዴት አገኙት?

አቶ ገብሩ፡- ቅድመ ምርጫ ሂደቱን አላየንም፡፡ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ቢታይ ሙሉ የሆነ ስእል ይኖርሃል፡፡ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቱ እንዴት እንደነበር ለማወቅ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችን ተዘዋውረን ለማየት ሞክረናል፡፡ የምርጫ ቁሳቁሶች መድረሳቸውን፣ ምዝገባ የተካሄደባቸውን ዶክመንቶችና ሌሎች ለምርጫ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች መካሄዳቸውን ለሁለት ቀናት ለማየት ሞክረናል፡፡ ለምርጫ የነበረው ዝግጅት ጥሩ ነው፡፡

ከእኛ የሚሻሉበት አንዱ በየአካባቢው በየቀበሌው መኪና ሊገባበት የሚችል መንገድ መኖሩ ነው፡፡ ሁለት ያህሉ ናቸው መኪናዎች የማይገባባቸው፡፡

የውጭ ተመልካቾችና ታዛቢዎች በሁሉም ጠቅላይ ግዛቶች ገብተው ለማየት ችለዋል፡፡ ለምሳሌ ሰዴቅ የተባለው የደቡብ አፍሪካ አገሮች የልማት ድርጅት ምርጫው ከመካሄዱ ከሶስት ወር በፊት ጀምሮ ታዛቢዎችን ልኮ የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ለማየት ችለዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም እንደዚሁ አድርጓል፡፡ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫ ታዛቢ ቡድን የላከው ወደ ኬንያ ነው፡፡ ወደ ዚምባብዌ የተላከው ሁለተኛው ቡድን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፓን አፍሪካን ታዛቢ ቡድን በዚምባብዌ ምርጫ ምን ዓይነት አቋም ይዟል?

አቶ ገብሩ፡- ታዛቢ ቡድኑ ከ10 የአገሪቱ ጠቅላይ ግዛቶች ይዞ በተመለሰው ሪፖርት መሠረት ምርጫውን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ምርጫው በአጠቃለይ ሲታይ ፍትሃዊና ግልፅ (Fair and transparent) ነበር፡፡ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ይህንን አቋም ይያዝ እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሱ መጠነኛ ግድፈቶች እንደነበሩም ተገንዝበዋል፡፡ በአጠቃላይ ምርጫው ግን የጎላ ግድፈት አልታየበትም፡፡

ሪፖርተር፡- በግልዎ በምርጫው የታዘቡት ነገር የለም?

አቶ ገብሩ፡- የሕዝቡ ተሳትፎ እጅግ ጥሩ ነበር፡፡ ዚምባብዌ አሁን ከደረሰችበት አኳያ ሳይሆን ካለው ችግር ከምዕራቡ ዓለም ጋር ካላት ውዝግብና ከሚደረግባት ጫና አንፃር እንዲህ ዓይነት ፍትሃዊና ግልፅ ምርጫ ማካሄድዋ የሚያስመሰግናት ነው፡፡ የምርጫው ውጤት ምን ይሆናል? ማን አሸነፈ፣ ማን ተሸነፈ? ሌላ ነገር ሆኖ በዚህ ችግር ውስጥ ሆና እንዲህ ዓይነት ፣ሃርሞናይዝድ፣ ምርጫ ማካሄድ መቻሏ በጣም ጥሩ ነው፡፡ (ሃርሞናይዝድ ማለት ሁለን ዓቀፍ ምርጫ የፕሬዚዳንቱ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ "ሳኒቶሪያል"ና የአካባቢ ምርጫ ማለት ነው"፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝቡ ስሜትና እንቅስቃሴስ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ገብሩ፡- በየቦታው የድጋፍ ሰልፎች ሲካሄዱ ነበር፡፡ ሐራሬ የተቃዋሚው ኤም ዲሲና የገዢው ፓርቲ የዛኑ ፒ ኤፍም ድጋፍ ሰልፈኞች ወጥተዋል፡፡ (ኤም.ዲ.ሲ ትልቁ ተፎካካሪ ተቃዋሚ ነው"፡፡ በተለይ ምርጫ ከመካሄዱ ሳምንት በፊት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እያለን በሳተላይት መከታተል እንደቻልነው ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ በእርግጥ በአፍሪካ ሁሉ አገራት እንደሚታየው ተቃዋሚው የገዢው ፓርቲ ያህል አቅምና ሀብት ኖሮት መንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ ተቃዋሚዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ አንድ እንግሊዛዊ ለሞርገን ሻንግራይ (MDC) ለቅስቀሳ እንዲጠቀሙበት ከደቡብ አፍሪካ የመጣ ፕሌን የያዘ ፓይለት ስለያዙባቸው ከዚህ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ነበር፡፡ በእርግጥ የዚምባብዌ ፖለቲካም ፓላራይዝድ ነው፡፡ የዓለምን ትኩረት የሳበችና በተለይ ምዕራቡ ዓለም ዓይኑን አፍጥጦት የሚመለከታት አገር ናት፡፡ በነጮች የመሬት ይዞታ ላይ በተወሰደው እርምጃ ምክንያት በተለይ እንግሊዞች በአገሪቱ ላይ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ነጮችም ኤም.ዲ.ሲ ቢመጣ ፍትሃዊ የመሬት ክፍፍል ያደርጋል በሚል ይደግፉታል፡፡ የሮበርት ሙጋቤ ዛኑፒኤፍ ደግሞ ተቃዋሚው ኤም.ዲ.ሲን የሚከሰው ከነጮች ጋር ተሻርኮ የመሬት ይዞታ ወደነበረበት ይመልሳል በሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዚምባብዌ ምርጫ ከእኛ አገር የምርጫ ሂደት ጋር ማነፃፀር ይቻላል?

አቶ ገብሩ፡- በአፍሪካ የምርጫ ቦርዶች ላይ ያለውን ጥርጣሬ ያገናኘዋል፡፡ እዚህ አገርም ያለው የምርጫ ቦርድ ነፃ አይደለም ነው ያልነው፡፡ እዚያም አገር ይህንን ነው የሚያሳየው፡፡ የምርጫ ውጤት በወቅቱ አለመውጣቱ የመንግሥት ተፅዕኖን የሚያሳይ ነው፡፡ ነፃ ቢሆን ኖሮ ያወጣ ነበር፡፡ ሌላው አብዛኛው የተማረ አለመሆን የምርጫ ሂደቱን አጓትቶታል፡፡ ትልቁ ነገር ግን ሕዝቡ ለለውጥ መነሳሳቱ ከእኛ ከ97 ምርጫ ጋር ይመሳሰላል፡፡ አሁን የዚምባብዌ ሕዝብ ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ችግር የሚያወጣው አካል መምጣት አለበት የሚል አስተሳሰብ ስላለ ለምርጫ የሚሰጡት ቦታ እጅግ ትልቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሙጋቤ መሬት ከነጮች ቀምተው ለጥቁሮች የሰጡ መሪ ናቸው ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት ከምዕራባውያን ጋር ውዝግብ ውስጥ ናቸው፤

አቶ ገብሩ፡- እሱን እኛ ራቅ ብለን እንደምናየው አይደለም፡፡ የተወሰነ ጥቁር የሕዝብ ክፍል ያ መሬት ያገኘው ተጠቃሚ ይሁን እንጂ ሁሉ የዚምባብዌ ተወላጅ አይደለም፡፡ የዚህ ተጠቃሚዎች እጅግ ውስን የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ያነጋገርኳቸው ሰዎች እንደነገሩኝ ከሆነ መሬት ከነጮች ተወስዶ ለጥቁሮች እንዲከፋፈል ያደረጉት ፕሬዚዳንቱ አስበውት ሆን ብለው አይመስለኝም፡፡ ከውጭ የመጡ ሰዎች ናቸው የገፋፏዋቸው እንጂ በሙጋቤ መንግሥት ተነሳሽነት አይደለም፡፡ አሁን ወጣም ወረደም የዚምባብዌ ሕዝብ ለውጥ እንደሚፈልግ ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ በተለይ የኑሮ ውድነቱ (የዋጋ ግሽበት) በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ገዥው ፓርቲ ይተቻል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ሲያነፃፅሩት ምን ታዘቡ?

አቶ ገብሩ፡- የምርጫ ቀን የደረሰ ነገር አልነበረም፡፡ ፖሊሶች በአካባቢው ነበሩ፡፡ የሚሰሩትን ያውቃሉ፡፡ በየቦታው እየተሯሯጥኩ እንዳየሁት በምርጫ አስፈፃሚዎች ሥራ ላይ ጣልቃ ሲገቡ አላየሁም፡፡ በምርጫው እለት አስጨናቂ ከባቢ አየር አልነበረም፡፡ ከሚቀጥለው ቀን ጀምሮ ግን ነገሮች ወደ አስጨናቂነት አምርተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ባይኖሩም መረጃ ለማግኘት ጥረት አላደረጉም?

አቶ ገብሩ፡- የጎሳ ፖለቲካ አፍሪካ ውስጥ የትም አለ፡፡ የዚምባብዌ ሕዝብ ለለውጥ መነሳሳቱን የሚያሳይህ ሮበርት ሙጋቤ ተወልደው ባደጉበት ማሽናላንድ ሁሉ ተሸንፈዋል፡፡ ሙጋቤ በማሽናላንድ ለማሸነፍ በጣም ነበር የጠበቁት፡፡

ሪፖርተር፡- ማሽናላንድ ላይ መሸነፋቸው ምን የተለዬ ነገር አለው?

አቶ ገብሩ፡- ማሽናላንድ ላይ ከተሸነፉ ሌላው ላይ አይቀርላቸውም የሚለውን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሙጋቤ ምርጫው በድጋሜ እንዲካሄድ ይፈልጋሉ፣

አቶ ገብሩ፡- የምርጫው ውጤት ሳይገለፅ ድጋሚ ምርጫ ይካሄድ መባሉ በጣም ነው ግራ ያጋባኝ፡፡ አይደለም ድጋሚ ምርጫ ለማካሄድ ቀርቶ ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ ለማካሄድ ሁሉ የምርጫው ውጤት ቀደም ብሎ መታወቅ አለበት፡፡ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ኤምዲሲ የሚለው ምርጫ ኮሚሽኑ አስቀድሞ የምርጫውን ውጤት ይግለፅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምዕራባውያን ሚድያዎች ለገዢው ፓርቲ አሉታዊ ምስል ሰጥተው ይዘግባሉ፤

አቶ ገብሩ፡- ትንሽ እውነታውን የማጋነን ነገር አለ፡፡ ሙጋቤ ቢሸነፉም የምዕራቡ አለም ሚድያ ይህን ያህል ፕሮፖጋንዳ መሥራቱ ትዝብት ላይ ይጥለዋል፡፡ ለነገሩ በጉዳዩ ላይ ጥቅም ስላላቸው ነው፡፡ እነ ቢቢሲ ከደቡብ አፍሪካ ሰው እየጠየቁ የስሚ ስሚ ነበር የሚዘግቡት፡፡ ከዚምባብዌ የመዘገብ ፈቃድ የላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓይነት እንዴት ነው የምዕራባዊያንን ዘገባ የምናምነው? ከዘገባው ጀርባ የራሳቸውን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ዘገባውንና እውነቱን የሚያጣ ከሆነ፤

አቶ ገብሩ፡- አፍሪካዊያን ማየት ያቃተን ይህንን ነው፡፡ አለመግባባትን በውይይትና በመነጋገር መፍታት እንዳለብን ማመን ይኖርብናል፡፡ ዚምባብውያንም ማድረግ ያለባቸው ይህንኑ ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ፣እኔ ብቻ አውቃለሁ፣ የሚል አባዜ አላቸው፡፡ ፣የአንተ ብቻ ጉዳይ አይደለም እኛም ዜጎቹ ያገባናል፣ የሚሉትን ሁሉ ይጠላሉ፡፡ መደረግ ያለበት ግን ፣ኑና ጉዳያችንን እንነጋገርበት፣ ነው፡፡ እዚህ አገር ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዴኀህ) አነሳሽነት ተጀምሮ የነበረውን የፓርቲዎች ውይይት በ1998 ዓ.ም አቋርጦ ፓርቲዎቹን ይቅርታ ጠይቁ አለ፡፡ ስንት መስዋዕት ከፍለን ያስጀመርነውን መድረክ ይቅርታ ካልጠየቃችሁ ተብሎ ተቋረጠ፡፡ ማን ማንን ነው ይቅርታ የሚጠይቀው? አገራችን ውስጥ ሆነን ድብደባውን ችለን ለዚህ አገር አንድ ነገር እናደርጋለን የምንለው ሰዎች መሳለቂያ አደረገን፡፡ መነጋገርን ባህል ካላደረግን የአፍሪካ መፃኢ እድል ደብዛዛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምዕራባውያን ተፅዕኖ የሌለበት ነፃና ገለልተኛ ምርጫ በአፍሪካ ውስጥ ሊካሄድ ይችላል?

አቶ ገብሩ፡- አይችልም፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምዕራባውያን ወደ አፍሪካ እጃቸውን ሰደዋል፡፡ የሚፈልጉትንም እየሰሩ ነው፡፡ የዚምባብዌን ቀውስ ተከትለው ለምሳሌ ለሙጋቤ ፣ያለ እኛ ምን እንደምትሆን እየው፣ የሚሉ ነው የሚመስለኝ፡፡ ለሌላውም የአፍሪካ መሪ እኛ ከምንለው ብታፈነግጥ ምን እንደምትሆን ከሙጋቤ ተማር ሊሉ የፈለጉ ይመስለኛል፡፡ የምዕራባውያኑን ጥያቄ በአግባቡ ማየት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ተፅዕኖአቸውን በምን መቀነስ ይቻላል?

አቶ ገብሩ፡- በተረጋጋ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነው መቀነስ ያለብን፡፡ በቀጥታ በመጋፈጥ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ገብሩ፡- የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምን ይመስላል? የሚለውን በደንብ ማየት ያስፈልጋል፡፡ እኔ የምዕራባውን ወዳጅ ነን ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከቻይና ጋር ከመቀራረባችን ውጭ ምዕራባውያንን ያበሳጨ ድርጊት አልፈፀምንም፡፡ ጉዳዩን በሚገባ ይዘነዋል፡፡ አሜሪካም "ኢሕአዴግን አትንኩት" ስትል ነበር፡፡ አሁን ምን ላይ እንዳሉ አላውቅም፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ለኢትዮጵያና ለኡጋንዳ እንዲሁም ለመሪዎቻቸው ልዩ ክብር አላቸው፡፡ እንደምሳሌም ይቆጥሯቸዋል፡፡ ከ1997 ዓ.ም የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኋላ ግን የአሜሪካ መንግሥት (ዲፕሎማቲክ ይሁን እንጂ) በዚያው ደረጃ ያለ አይመስለኝም፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን አስመልክቶ ብዙ መረጃዎችን አውጥቷል፡፡ ማስጠንቀቂያም ሰጥቷል፡፡ እንደ ግለሰብ በፊት የነበረው ነገር ይቀጥላል የሚል ግምት የለኝም፡፡

 
< Prev   Next >