| የአገራችን ምርጫ ከሞዴልነት ወደ ዳዴነት |
|
|
| Wednesday, 16 April 2008 | |
|
በምርጫው አሸናፊና ተሸናፊ (መገመት ቢቻልም) ለወደፊቱ የሚገለፅ ቢሆንም በምርጫው የነበረ ሁኔታ ግን ምን እንደሚመስል መግለፅ የሚያዳግት አይደለም፡፡ ምርጫው አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ነበሩበት፡፡ ከምርጫ በፊት በአንዳንድ ወገኖ ይናፈስ የነበፈረው "ሕዝቡ አይመርጥም" የሚል አደገኛና ከአእምሮ ሊወገድ የሚገባው ጸረ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት የተሸነፈበት ሁኔታ አይተናል፡፡ እንደ 97ቱ በነቂስ ወጥቶ የለውጥ መንፈስ ባለበት ባይሆንም ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበው ሕዝብ ተስፋ ቆርጦ፣ አኩርፎ በእጁ ያለው ካርድ ዋጋ ቢስ አላስቀረውም፡፡ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውረን ያገኘነው ሪፖርታችን አጠናክረን ተመልሰናል፡፡ በቂርቆስ፣ ቦሌ፣ አዲስ ከተማ፣ የካና በአራዳ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የነበረው ሁኔታ ሁሉ ተመሳሳይነት ይታይበታል፡፡ በዚህ መሰረት በሁሉም ቦታዎች የነበረው ሁኔታ ሰላማዊና ምንም ዓይነት ችግር ያልታየበት ነበር፡፡ ድምፅ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሚጎርፈው ሕዝብ ብዙም መነሳሳት በሚታይበት መንፈስ አይደለም፡፡ መምረጥ ስለአለበት እንጂ ለለውጥ ተነሳስቶ በስሜት የሚጎርፍ አይደለም፡፡ በምርጫ ጣቢያዎች የነበሩት አስተባባሪዎች መራጩን ሲያስረዱና፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሲሰጡ ታዝበናል፡፡ መራጮችም ያለምንም ተፅዕኖና ፍርሃት በተዘጋጀላቸው ሚስጥራዊ የድምፅ መስጫ ቦታ ገብተው መምረጣቸው ነግረውናል፡፡ ወጣት ተስፋይ በርሀ ይባላል፡፡ በመሿለኪያ አካባቢ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/14 ይኖራል፡፡ ድምፅ ሰጥቶ ሲወጣ አግኝተነው ባነጋገርነው ወቅት፣ "እንደ ዜጋ መምረጥ ግዴታየና መብቴ ነው፡፡ የመረጥኩት ፓርቲ ደግሞ ፖሊሲውና አቋሙን አይቼ እንጂ በስሜት ተገፋፍቼ አይደለም፡፡ ምርጫው ደግሞ እጅግ የተረጋጋና ስነ ሥርዓት ያለው ነው" ብለዋል፡፡ ወጣት ጌታቸው በርሀ በተመሳሳይ ቦታ አግኝተነው ያለምንም ተፅዕኖ መምረጡን ነግሮናል፡፡ "እኔ የምመርጠው ፓርቲ ቢያሸንፍም ባያሸንፍም የያዙኩት ካርድ ዋጋ እንዳለው አቃለሁ" ብሏል፡፡ ሌላ በመጽሐፍት ሥራ ላይ የሚተዳደረው ሰይፈዲን ሙሳ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚኖረው መምረጡን ጠይቀነው አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቶናል፡፡ ለምን እንደመረጠ ሲናገር "መምረጥ ግዴታችን ነው፤ ፍላጎታችንም ነው፡፡ ለሃገራችም ወሳኝ ጉዳይ ነው" በማለት ባለመምረጡ የሚጎዳ አካል ራሱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ "ያልመረጥነው ወገን ሲመረጥ ጉዳቱ ለእኛ ነው፡፡ ማንኛውም አካል ስልጣን ላይ ሲወጣ ግን የሕዝቡን ችግር ማዳመጥ አለበት"፡፡ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በተለይ ለማሟያ ምርጫ በርከት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉ ቢሆንም ታዛቢ ያስቀመጠ ፓርቲ ኢሕአዴግ ብቻ ነበር፡፡ በእርግጥ በሁሉም አካባቢዎች ነፃ የሕዝብ ታዛቢዎች ተቀምጠው ነበር፡፡ ሆኖም እንደ ችግር ሊጠቀስ የሚችል የተቃዋሚዎች ታዛቢ ማየት አልቻልንም፡፡ በቦታው ያገኘናቸው ታዛቢዎችና የምርጫ አስፈፃሚዎች ጠይቀን ለመረዳት እንደቻልነው እስከ መጨረሻ ሰዓት ቢጠብቁዋቸውም በቦታው ሊገኙ ባለመቻላቸው ቃለ ጉባኤ ይዘው ስራቸውን ሳይተጓጎል ቀጥለዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ተቃዋሚዎች ለማነጋገር ሞክረናል፡፡ ፓርቲዎቹ ታዛቢ አለማቅረባቸው በምርጫው ውጤት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ የመኢብን ሊቀመንበር አቶ መስፍን ሽፈራው ታዛቢ ያላቀረቡበት ምክንያት ሲገልፁ ምርጫ ቦርድ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚሰጥ ገንዘብ ስላልተሰጣቸውና አበል የሚከፍሉት ዓቅም ስለሌላቸው መሆኑን ነው፡፡ የቅንጅት ሊቀመንበር አቶ አየለም ከዚህ በተጨማሪ እስከ 30 የሚደርሱ ታዛቢዎች ቢያቀርቡም ማንነቱ ካልታወቀ አካል ማስፈራሪያ ስለደረሳቸው መስራት አለመቻላቸው ገልፀዋል፡፡ የኢዴፓ መድህን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሞሼ ሰሙ በበኩላቸው ታዛቢዎች አበል ለመክፈል በቂ ገንዘብ እንደሌላቸው በመናገር "በመሰረቱም ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም የተወዳደርነው ለተሳትፎ እንጂ ውጤት ተኮር ስላልሆነ ታዛቢ ማስቀመጥ አላስፈለገንም" የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ተቃዋሚዎች ደጋግመው ያሉት "አሸናፊው ይታወቃል" የሚል አመለካከት ነበር፡፡ በአገራችን የተቃዋሞ ትግል ረዥም ዕድሜ ያለው ሕብረትም በ11ኛው ሰዓት ከምርጫው መውጣቱ ይህንን በማሰብ ከተሸናፊነት ለማምለጥ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ሌሎችም ተቃዋሚዎችም አማራጭ ሆነው አልተገኙም፣ አልተሰባሰቡም፣ ጠንካራ አይደሉም፣ በመሆኑም ሕዝብ እንደ አማራጭ ሊያያቸው አልቻለም፡፡ በመሆኑም ፉክክር ያለበት ምርጫ ተካሂዷል ማለት ይከብዳል፡፡ በቂ ተፎካካሪ የሌለበት ምርጫ ፍትሃዊም ነፃም ለመሆን መስፈርት የለውም፡፡ ተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸው በውል ሳይተዋወቁ አንዳንዶቹ ከጥላቻ ተነስተው ይቀናጁ ማለታችን ሳይሆን ፕሮግራማቸው አጥብበው መቀራረብና መከራከር ይኖረባቸዋል፡፡ ከ97ቱም ከአሁኑም ምርጫ ይህንን መማር ይኖርባቸዋል፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚዎች አለመኖራቸው ገዢውን ፓርቲ የሚያስተች ባይሆንም፣ ለድክመታቸው አንዱ ምክንያት ራሱ ኢሕአዴግ በመሆኑ አመቺ ድባብ በመፍጠር በኩል ከትችት ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ተቃዋሚዎች አዳክሞ ብቻውን ከሚወዳደር ጠንካራ ተቃዋሚዎች ተፈጥረው በራስ መተማመን ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ተቃዋሚ አልባ ምርጫ ግን አማራጭ የሌለው ምርጫ በመሆኑ ለዴሞክሲያዊነቱ መስፈርት ማግኘት አይቻልም፡፡ ምርጫ የዴሞክራሲ ዋነኛው መገለጫና ነፀብራቅ መሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ሀሳብ ነው፡፡ ሆኖም ምርጫ የዴሞክራሲ ምሰሶ የሚሆን ማሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎችና ባህርያት አሟልቶ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑም ስንፅፍም ስንናገርም ከቃሉ በፊት እየሰካን የምንጠቀማቸው ተቀጥላ እንደ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ግልፅ፣ ፉክክር ያለበት". ወዘተ. የሚሉ ቅፅሎች የምርጫው ሂደት፣ ሁኔታ ትክክለኛነት ሐቀኝነት ለማወቅ የሚያስችሉን ዓለም ዐቀፍ መስፈርቶች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ምርጫ በገዛ አገራቸው ሰምተውም፣ አይተውም የማያውቁ ሕዝቦች እንዳሉ ሆኖ፣ በዘመናችን በየትኛውም የአለማችን ክፍል በየአራት ወይም አምስት ዓመቱ ውስጥ ምርጫ ብቅ ማለቱ የተለመደ ሆኗል፡፡ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ጥቁሩም ነጩም፣ ደሃውም ባለፀጋውም፣ ዲሞክራቱም አምባገነኑም፣ ገዢውም ተቃዋሚውም በምርጫ አስፈላጊነት የተስማሙ ይመስላሉ፡፡ ከዚህ መርህ ውጭ ወደ ስልጣን መቆናጠጥ "ወግድ" የተባለ ይመስላል፡፡ ይህም ስልጣን ከላይ በመንፈስ ቅዱስ የወረደ በመለኮታዊ ኃይል የሚገኝ፣ በዘር ተዋረድ የሚተላለፍ፣ ወይም በአፈ ሙዝ መያዝ ቀርቶ ምንጩ ሕዝብ በመሆኑ በሕዝብ ፍላጎትና ፍቃድ የሚሰጥና የሚከለከል ከሚል የዘመናችን መሰረታዊ መርህ የመጣ ነው፡፡ በስልጣን ምንጭና መንገድ ላይ ያለው መሰረታዊው ጽንሰ ሃሳብ ማንም ቢቀበለውም በተግባር ለመርሁ ተገዢ የሚሆኑ ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆን በአገራቸው ውስጥ እንጂ በሌሎች አገሮች ለሚኖሩ ሕዝቦች ተመሳሳይ እድል እንዲያገኙ የሚፈልጉ ካላቸው ፍላጎትና ምኞት የመነጨ ሳይሆን በአገሪቱ የራሳቸው ጥቅም በተሻለ መንገድ "ሊያስፈፅምልኝ የሚችል ማን ነው?" ከሚል ራስ ወዳድነት የተነሳ እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡ በቅርቡ በዙምባቤዌ የተካሄደው ምርጫ በብዙ ታዛቢዎች ዘንድ የተመሰገነ ቢሆንም የምዕራባውያን ታዛቢዎችና መገናኛ ብዙኃን ግን አጨልመውታል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ነጮች የመሬት ይዞታቸው ስለተነካባቸው ምንም ይሁን ምንም ጥሩ ነገር ቢሰራ ለነሱ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን ለመጣል ትንንቅ የገጠመው ኤምዴሲ ድጋፍ የሚያገኘው ከምዕራባውያን እንደሆነ ድብቅ አይደለም፡፡ በአገራችንም የ97ቱ ጨምሮ ሶስት አገራዊ ምርጫዎች ተካሄደዋል፡፡ የምርጫዎቹ ዴሞክራሲያዊነትና ተፎካካሪነት እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ ነበር፡፡ በመሆኑም በ1997 የተካሄደው ምርጫ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የመረጠበትና ለለውጥ ያለው ተነሳሽነት ያሳየበት ሁኔታ መፈጠሩ ይታወቃል፡፡ የ97ቱ ምርጫ ልዩ የሚያደርገው በአገራችን ከፍተኛ ፉክክር ያለበትና ተቃዋሚዎችም ቀላል የማይባል የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፉበት በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የስልጣን ምንጭ ሕዝቡ በእጁ የያዘው ካርድ መሆኑን የተረዳበት ነው፡፡ በተለይ በቅድመ ምርጫው የታየው የሕዝብ ተሳትፎና የሂደቱ መንፈስ አገራችን በአፍሪካ እንደ "ሞዴልነት" ሊያስቆጥር የሚችል አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በድህረ ምርጫው የተፈጠረው ውዝግብ እንደተጠበቀ ሆኖ በቅድመ ምርጫው የነበረው ሂደት በጣም አበረታችና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የ97 ምርጫ እንዲህ የምናስመሰግነው ጠንካራና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመኖራቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ በወቅቱ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለጊዜውም ቢሆን ተቀናጅተው ከዚያ በፊት ተቃውሞ የማያቅ ገዢው ፓርቲ አስግተዋል፡፡ በተቃውሞ ወገን የነበረው ሕዝብና አጠቃላይ የአገሪቱ ምርጫ ሞቅ ሞቅ እንዲል አድርገውታል፡፡ የ97ቱ ምርጫ እንዲህ አስደናቂ ሆኖ እንዲነሳ ምክንያት የሚሆነው በቂ ፉክክርና ክርክር አድርጎ ገዢውን ፓርቲ በካርድ ሊጥል የሚችል ሌላ አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ የያዘ ጠንካራ ተቃዋሚ በመፈጠሩ ነው፡፡ እንዲህ በሌለበት ሁኔታ የሚካሄደው ምርጫ ምን ሊመስል እንደሚችል ለማወቅ ባለፈው እሁድ የተካሄደው የማሟያና የአካባቢ ምርጫ መመልከት ማስረጃ ነው፡፡ እንደ 97ቱ ምርጫ ለአገሪቱ የመንግሥት ለውጥ የሚደረግበት ባይሆንም በተለይ ለአዲስ አበባ ከዚህ የማይተናነስ ጥቅም ያለው ምርጫ ነበር የተደረገው፡፡ በ1997 ምርጫ አለመታደል ሆኖ የከተማው ሕዝብ የሰጣቸውን ድምጽና ስልጣን ለመቀበል ፈቃደኞች ያልሆኑ ተቃዋሚዎች ባለቤት በመሆኗ እነሆ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሕዝቡ ባልመረጠውና በማያውቀው አካል በባለ አደራ መስተዳደር እጅ ወድቃ ቆይታለች፡፡ እነዛ ሁሉ የምርጫ ካርዶች የለውጥ ምንጭ መሆናቸው ቀርቶ ነውጥ በማስከተላቸው ከተማዋ የሁከትና የብጥብጥ መንደር አንድትሆን አድርገውታል፡፡ ያልታደሉ ካርዶች፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |