| “ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት... |
|
|
| Wednesday, 16 April 2008 | |
![]() አቶ ሀብታሙ ታደሰ አቶ ሀብታሙ ታደሰ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዓለም የንግድ ድርጅት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የግል ዘርፍ ባለሐብቶች የሚፈልጉትን አቅጣጫ፣ ያለባቸውን ችግሮች ለማሳየትና የተጠና አቋም ይዘው ለመወያየት ያላቸው ተነሳሽነት አናሳ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ በንግድና አንዱስትሪ ሚኒስቴር የዓለም የንግድ ድርጅት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ታደሰ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ በዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሁኔታ የተጠና አቋምና ጥያቄ ይዘው የቀረቡ የግል ባለሐብቶች የሉም፡፡ እስከአሁን በሁሉም ዘርፎች ያለው ድርድር በመንግሥት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በድርጅቱ በታዛቢነት መሳተፍ የተጀመረው በቅርቡ በመሆኑ በመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ በምርምር በፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በግል ባለሐብቶች ያለው ተሳትፎ አናሳ መሆኑን የገለፁት አቶ ሀብታሙ እያንዳንዱ ዘርፉ ባለቤት መሆኑን አውቆ ተሳታፊ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ የድርድር ሂደቱ በመንግሥት ብቻ መሠራቱ አንድ ወገን አይሆንም ወይ ብለን ለጠየቅናቸው አቶ ሀብታሙ ሲመልሱ፤ የግል ዘርፍ ባለሐብቶች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አናሳ በመሆኑ የሁሉንም ፍላጎት በማካተት የግሉ ዘርፍ ችግር በመንግሥት በኩል እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የግል ባለሐብቶቹ አብረዋቸው እየሠሩ ቢሆንም ጠንካራ የሆነ አቋም የሚያቀርብ የግል ዘርፍ ባለሐብት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ጠንካራ የሆነ የግል ዘርፍ ባለመኖሩ በመምሪያው የቴክኒክ ኮሚቴዎችን በማዋቀር የእያንዳንዱን ስምምነት ዝርዝር ጉዳይ አሠራራችንንና ክፍተቱን እንዲያውቁ እያንዳንዱ ዘርፍ ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ባሉት ቴክኒካል ሥራ ደረጃዎች አራት አስፈላጊ ሂደቶች መኖራቸውን፣ የአባልነት ጥያቄ ማቅረብና የሥራ ቡድን መመስረት፣ አመልካች አገር አባል ለመሆን ሲፈልግ በማራካሽ ስምምነት አንቀፅ 12 መሠረት ጥያቄውን ለጄነራል ዳይሬክተር እንደሚያቀርብ የገለፁት አቶ ሀብታሙ ጥያቄው በሁሉም አባል አገሮች ተቀባይነት አግኝቶ በተቋቋመው የአባልነት ደረጃ ሁኔታችንን በመመርመር ጥያቄያችን ተቀባይነት ያገኘው በ2ዐዐ3 መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መረጃ በማሰባሰብ አመልካች አገር የውጪ ንግድ ስርዓቷን የሚመለከት ሠነድ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚ ጀምሮ አጠቃላይ የንግድ ህግጋት፣ የሁለትዮሽ ስምምነት፣ የታክስ ስርዓት በሚያመለክት ሁሉም አካላት እንዲሳተፉ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በተውጣጡ ኮሚቴ እንዲታይ ተደርጎ ብሔራዊ ኮሚቴ የተወሰኑ ማስተካከያዎችን ማድረጉንና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቅረብ ቢፀድቅም ለድርጅቱ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ሁኔታ ለሁለት ዓመታት ሳይላክ በመቆየቱ አዳዲስ የተፈጠሩትን ሁኔታዎች በመጨመር በ2ዐዐ6 መጨረሻ ለድርጅቱ መቅረቡን ገልፀዋል፡፡ የተላከው መረጃ ለሁሉም 151 አባል አገራት መላኩን የገለፁት አቶ ሀብታሙ በሰነዱ ላይ ጥያቄ ያላቸው በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ የካቲት 2ዐዐ7 ላይ ሁለት አገሮች አሜሪካና ካናዳ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡ የአሜሪካ በሰነዱ የተካተቱትንና የዓለም የንግድ ድርጅት ሦስት ምሰሶዎችን የእቃዎች፣ የአገልግሎት ንግድና ከአእምሯዊ ንብረት ጋር ሁሉንም ያካተተ 202 ጥያቄዎችን ከካናዳ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚያተኩር 17 ጥያቄዎች ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡ ጥያቄዎቹ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን የሚመለከት በመሆኑ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች በማስተባበር የቴክኒክ ኮሚቴ ከመንግሥት መስሪያ ቤት፣ ፋይናንስ፣ ከምርምር በግል ዘርፍ በሚገኙት በማጠናከር በ1ዐ ወር ምላሽ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡ ጥያቄዎቹ ማብራሪያና አዳዲስ የተጨመሩ ህጎችን ለማስታወቅ የሚረዱ መሆናቸውን የጥያቄዎቹ መልስ በ2ዐዐ7 መጨረሻ ለድርጅቱ ደርሶ ለአባል አገራቱ መላኩን ተናግረዋል፡፡ በመረጃ ማሰባሰብ በየዘርፉ በግብርና አገልግሎት ላይ ያሉን አሠራሮች ደንቦችና ሕጎች ዙሪያ ለድርድር አጋዥ የሆኑ ሠነዶች እንደሚዘጋጁም ጠቁመዋል፡፡ የባለብዙ ወገን ድርድር እንደሚካሄድና ሁሉንም አገር የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በሥራ ቡድን አባል አገራትን በመጥራት በፅሁፍና በቃል የሚያስረዱበት ሂደት እንደሆነና በሁለትዮሽ የንግድ ድርድር በእቃዎችና አገልግሎት ላይ የሚደረግ የታሪፍ የጉምሩክ ህግ ላይ ውይይት በተናጠል እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ታሪፍ ዝቅተኛው ዜሮና ከፍተኛው 3ዐ መሆኑ በሁለትዮሽ ድርድር መሆኑንና በድርድሩ የታሪፍ ሁኔታው እንዳያድግ የመጨረሻ ታሪፍ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ለዚህም የታሪፍ ጣሪያ 1ዐዐ መቀመጡን በመቀነስ ድርድር እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡ ከአባልነት በኋላ ከመጨረሻው ታሪፍ ማውረድ እንደሚኖር ገልፀዋል፡፡ የቀረቡት ጥያቄዎች የሁሉንም አባላት ጥያቄ የሚወክል ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄ ያላቸው ከሁለት እስከ አራት ዙር ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለዚህም በተከታታይ ምላሽ እንደሚሠጥ ገልፀዋል፡፡ የሁለትዮሽ ስምምነት የሚደረገው ከሁሉም የዓለም የንግድ ድርጅቶች አባል አገራት ጋር እንዳልሆነና ከዋና የንግድ ሸሪኮች ባለፉት ሦስት ዓመታት ባለው የንግድ ስታትስቲክ ውጤት መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት ከአውሮፓ አገሮች ጋር የሚደረገው በአውሮፓ ህብረት ስም ሲሆን ከአንዱ አገር ጋር የሚደረግ ስምምነት ለሌላው በግልፅ እንደማይቀመጥ የገለፁት አቶ ሃብታሙ ለአንድ አገር የተሰጠ የተለየ ጥቅም ለሌላ አገር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሥጠት ግድ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በታሪፍ አወሳሰን አነስተኛ የተባለው ታሪፍ በሌሎችም ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ አሜሪካና ካናዳ ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ለሁሉም አባል አገራት እንደሚደርስ ከጥያቄው ምላሽ ተነስተው ጥያቄና ተጨማሪ ማብራሪያ መጠየቅ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ የመጀመሪያ የሥራ ቡድን ስብሰባ ሚያዚያ 4 የነበረው ወደ ግንቦት መዛወሩን የገለፁት አቶ ሀብታሙ በስብሰባው በሰነዱና በምላሾቹ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ይህም ለሁለትዮሽ የንግድ ድርድር መነሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በስብሰባው ወቅት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ምላሽ መስጠት የሚችል ቢሆንም ምላሹ ተቀባይነት እንዲያገኝ በፅሁፍ ምላሽ መስጠት የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት ከሚጠይቀው የፖሊሲና ተቋማዊ ለውጥና ውስብስብ ሂደት ካለን ውሱን አቅም ሃብት አንፃር በአምስት ዓመት ማሟላት እንዴት ይቻላል ብለን ለጠየቅናቸው ሲመልሱ አባል መሆን ጥቅምና ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩትም አባል አለመሆን አማራጭ አለመሆኑን የገለፁት አቶ ሃብታሙ 151 አባል አገራትና ከዓለም የንግድ እንቅስቃሴ 97 በመቶ የሚካሄደው በእነዚህ አገራት ውስጥ በመካሄዱ በዓለም የንግድ እንቅስቀሴ ተሳታፊ ለመሆን የዓለም ንግድ ድርጅት መመሪያዎችን በመጠየቃችን አባል መሆን የተሻለ አማራጭ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት የነፃ ገበያ ሂደት ሳይሆን በሕግ ላይ የተመሠረተ የንግድ አሠራር በመሆኑ በዕቃዎች ንግድ ብቻ ከ12 በላይ የንግድ ስምምነቶች መኖራቸውን ገልፀው የዓለም የንግድ ድርጅት መርሆዎች ለአንድ አገር የተሰጠውን የተሻለ እድል ለሌላው መስጠት፣ ከአገር ወስጥ ድርጅቶች የተሰጠን መብት ለውጪ አገር መስጠት፣ ወደ ፊት ታክስ ሊያድግ አይችልም የሚል መወሰኛ ማስቀመጥ በአገር ደረጃ የወጡ ሕጎች ለፅህፈት ቤቱ ማሳወቅ አባል በመሆን ሂደት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሂደቱ አባል አገራት መረጃ እንዲያገኙ ሲረዳ ከህጎቹ የተለየና የማይነኩ (exceptions) ከአካባቢ፣ ሰው ጤና አኗኗር ሞራል ጋር ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮች ትኩረት እንደሚሰጥና በአካባቢያዊ የንግድ ስምምነት የሚደረጉ የተለያዩ ድርጅቶች ከዓለም የንግድ ድርጅት ተግባራዊ እንደማይሆን ጠቁመዋል፡፡ ታዳጊ አገሮች ከአደጉት አገሮች ጋር የተጣጣመ አሠራር እንዲከተሉ የእፎይታ ጊዜ እንደሚሰጥና ተደራዳሪ ወገኖች እንዲያምኑበት ካስፈለገ አቅም እስኪገነባ መቆየት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡ በየስምምነቱ የሽግግር ጊዜ እንዲሰጥ የተለያዩ አሳማኝ ምክንያት በማቅረብ ድርድር ማድረግና በሚቀርቡት ጊዜ የፋይናንስ ድጋፍ መጠየቅ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት ያሉንን የንግድ ሥርዓትና ሕጎች ከዓለም የንግድ ስርዓት ጋር ለማጣጣም እንደሚረዳም የገለፁት አቶ ሃብታሙ ምርቶቻችን በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ እንደሆኑና የድርጅቱ አባል ባለመሆን የተጣሉብንን ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የሚላክ ሥጋና የቁም ከብት ሳኡዲ አረቢያ ተቀባይነት እንደሌለው ሆኖም የዓለም የንግድ ድርጅት አባል በመሆን ሂደት በሳይንስ ማረጋገጥ ካለው የጂኦግራፊ ስፋት አንፃር በሽታ ያለበትን አካባቢ ብቻ ለይቶ በማጥናት የሚከላከሉበት ሂደት እንዳለ ይህ አባል በመሆናችን ልናገኛቸው የምንችለው እድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በእቃዎች በሚደረጉ ድርድር ከ12 በላይ ስምምነቶች እንዳሉና በአባልነት ሂደት የሌሉንን የማውጣት የማይጣጣሙትን ክፍተት የማስተካከል ሥራ እንደሚኖር ገልፀዋል፡፡ የማይመሳሰሉትና የሌሉንን ሕጎች የምናወጣበት የምናፀድቅበትና የምናስተካክልበት የጊዜ ሠሌዳ መቅረቡንም ተናግረዋል፡፡ በልማት ያደጉት አገሮች ያላደጉትን እንዲደግፉ፣ እንዲረዱ ልማትን በሚያመጣ ሁኔታ የተለየ ድጋፍ እንዲደረግ ትልልቅ አገሮች የሚያደርጉትን አነስተኛ አቅም ባላቸውም በእኩልነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ሁኔታ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ በቤዛዊት ሥዩም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |