Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow የብሔራዊ ባንክና የባንኮች የሥራ ኃላፊዎች...
የብሔራዊ ባንክና የባንኮች የሥራ ኃላፊዎች... Print E-mail
Wednesday, 09 January 2008

የብሔራዊ ባንክና የባንኮች የሥራ ኃላፊዎች በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያዩ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው የባንኮች መተዳደሪያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተቃውሟቸውን በጽሁፍ ያቀረቡት ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያያታቸው ተገለፀ፡፡

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የባንኮችን ሕልውና እንደሚነካና ብሔራዊ ባንክ ገደብ የሌለው ስልጣን እንዲኖረው እንደሚያደርግ በመግለጽ ሁሉም ባንኮች በረቂቁ አዋጅ ላይ በየግል ቅሬታቸውን ያስገቡ ሲሆን በባንኮች ማኅበር በኩልም አቋማቸውን በጽሁፍ አሳውቀዋል፡፡

በጽሁፍ ከቀረበው ቅሬታ ባሻገር የየባንኮቹ የሥራ ኃላፊዎች ከብሔራዊ ባንክ ገዥና ከሌሎች የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባሳለፍነው አርብ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

የውይይቱን መንፈስ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የባንኮች የሥራ ኃላፊዎች እንደጠቆሙት ከቀረቡት ተቃውሞዎች መካከል በረቂቅ አዋጁ ፣አንድ ባለ አክስዮን በሁለት ባንኮች ውስጥ አክስዮን ሊገባ አይችልም፣ በሚለው አንቀጽ ባንኮቹ የወሰዱት አቋም የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ በማሳደጉ ረገድ ጠቃሚ ይሆናል እንጂ ጉዳት አይኖረውም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ የብሔራዊ ባንክ ወደ ፊት በሚያወጣው መመሪያ የተለያዩ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችል በሚያመለክቱ አንቀፆች ዙሪያም መመሪያዎቹ እስካልታወቁ ድረስ እንዲህ አይነት አዋጅ ሊወጣ እንደማይችልም አስገንዝበዋል፡፡

በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ብሔራዊ ባንክ በባንኮች የዳይሬክተሮች ቦርድ አሿሿም የክፍያ መጠንና በመሳሰሉት ጉዳይ ላይ የተካተቱ አንቀፆች ባንኮቹ በነፃነት እንዳይሰሩና ሥራቸው ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት ይቆጠራል በማለትም አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የባንኮቹን ዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ክፍያን እኔ እወስናለሁ ማለቱ ትክክል አለመሆኑንና እንዲህ አይነት ክፍያዎች በአክስዮኑ እንጂ ብሔራዊ ባንክ ሊወሰን አይችልም የሚል አቋም ይዘዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ቅጣትን በተመለከተ የተቀመጡት አንቀፆችም የባንክ የሥራ ኃላፊዎች እንደ ልብ እንዳይሰሩ የሚገድብና የቅጣቱ መጠንም የተጋነነ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በአብዛኛው ባንኮች የረቂቅ አዋጁ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው የሚያመለክት ውይይት የተደረገ ሲሆን የብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎችም ይህ ረቂቅ አዋጅ ለምን እንደተዘጋጀ አስረድተዋል፡፡

ውይይት ውሳኔ የሚሰጥበት እንዳልነበር ያመለከቱት የባንኮቹ የሥራ ኃላፊዎች ብሔራዊ ባንክ በጽሁፍና በግንባር የቀረበለትን አስተያየት ተቀብሎ ረቂቅ አዋጁን ማስተካከል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በዳዊት ታዬ

 
< Prev   Next >