| በአዋሽ ሰባት ኪሎ ተጀምሮ... |
|
|
| Sunday, 20 April 2008 | |
|
በአዋሽ ሰባት ኪሎ ተጀምሮ የነበረው የምግብ ዋጋ ቁጥጥር ተቋረጠ
በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ተጀምሮ የነበረው የምግብ ዋጋ ቁጥጥር ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ ተቋረጠ፡፡ አልጋቸውን በውድ ዋጋ የሚያከራዩ ነጋዴዎች ሆቴሎቻቸው እየታሸጉባቸው ነው፡፡ የአዋሽ ሰባት ኪሎ ነዋሪዎችን አነጋግረን ካገኘነው መረጃ ለማወቅ እንደቻልነው የአካባቢው አስተዳደር ለሁለት ሳምንታት ያህል በተለያዩ የምግብ ምርቶች ላይ የዋጋ ተመን ጥሎ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሠረት ሆቴሎች የሚያዘጋጁትን ቀይ ወጥና ቅቅል በአምስት ብር እንዲሸጡ ተወስኖባቸው ነበር፡፡ አርባ ብር ይሸጥ የነበረው የአፋሮች ባህላዊ ምግብም ወደ 20 ብር በመቀነሱ ተጠቃሚዎች በዝተው ነበር፡፡ እንደምንጮቻችን ገለፃ በከተማዋ ተጀምሮ የነበረው የዋጋ ቁጥጥር የተቋረጠው በአካባቢው የሚኖሩትን ነጋዴዎች ለኪሳራ መዳረጉ ስለታወቀ ነው፡፡ የከተማዋ መስተዳድር በምግብ ምርቶች ላይ ሲያደርገው የነበረውን ቁጥጥር ቢያቋርጥም አልጋዎቻቸውን በውድ ዋጋ የሚያከራዩ ነጋዴዎች ግን እየታሸጉባቸው ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ሲካሄድ በነበረው የዋጋ ቁጥጥር 150 ብር ይከራይ የነበረ አንድ አልጋ ወደ 50 ብር ዝቅ እንዲል ተደርጐ ነበር፡፡ በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በኑሮ ውድነት ላይ ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ግብረ ሀይል መቋቋሙንና የሚቋቋመው ግብረ ሀይልም ነጋዴዎች ምርታቸውን የሚሸጡበትን ዋጋ መለጠፋቸውንና አለመለጠፋቸውን እንደሚከታተል መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡ ግብረ ሀይሉ የሚያከናውነው ሥራም የዋጋ ቁጥጥር አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ የመሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ያቀረቡት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ ግርማ ብሩ በበኩላቸው በአሁኑ ሰዓት መንግሥት የዋጋ ቁጥጥር እንደማያደርግ ጠቁመው የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ ካስፈለገ ግን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ ያለበት መሆኑን መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡ በኃይሌ ሙሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |