Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow በአዲስ አበባ 30 ያህል ሕገወጥ የቤት ሥራ...
በአዲስ አበባ 30 ያህል ሕገወጥ የቤት ሥራ... Print E-mail
Sunday, 20 April 2008
በአዲስ አበባ 30 ያህል ሕገወጥ የቤት ሥራ ማኅበራት የተቋቋሙት በአንድ ግለሰብ ነበር

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 30 ያህል የቤት ሥራ ማኅበራት ከ1983 ዓ.ም በፊት የተቋቋሙ በማስመሰል፣ መሬት፣ ካርታና የግንባታ ፈቃድ እንዲያገኙ በመርዳት ቁልፍ ሚና የተጫወተው አንድ ግለሰብ እንደነበር የፌደራል የሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ይፋ አደረገ፡፡

ኮሚሽኑ “ሥነምግባር” በተሰኘውና በቅርቡ ባወጣው መጽሔቱ ላይ እንደዘገበው በሕገወጥ ሥራው ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ያለውና በአሁኑ ወቅት ለፍርድ ያቀረበው ግለሰብ በማዘጋጃ ቤት ይሠራ የነበረ ነው፡፡ ግለሰቡ የምህንድስና ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በ1983 ዓ.ም ሥራ የጀመረው በአዲስ አበባ  ቤት መሆኑን፣ በመ/ቤቱም በሰርቬይና በሱፐርቪዥን ሙያ እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ መሥራቱን ያትታል፡፡ ይኸው ግለሰብ ከመዋቅር ጋር በተያያዘ በ1995 ከሥራ ሲሰናበት የከተማዋን ማስተር ፕላን በሲዲ ይዞ መውጣቱን፣ ከወጣም በኋላ ሲዲውን ለሕገወጥ ሥራው ማከናወኛ ሲጠቀምበት መቆየቱን ኮምሽኑ ገልጿል፡፡

ከኮሚሽኑ ዘገባ መረዳት እንደተቻለው ግለሰቡ በደላሎች አማካይነት በሕገወጥ መንገድ በማሳበር ለመደራጀት የሚፈልጉ ሰዎችን ይቀርባል፡፡ ለዚያም ይዞት በወጣው ሲዲና በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት በሚያውቃቸው ቴክኒካዊ መረጃዎች ተጠቅሞ ሰነዶችን በማዘጋጀት ቤት ፈላጊዎች በማኅበር እንዲደራጁና መሬት እንዲወስዱ ሲረዳ ቆይቷል፡፡
ግለሰቡ ለመኖሪያ ቤት የተፈቀዱና ክፍት የሆኑ ቦታዎችን በሲዲው አማካይነት በመለየት፣ በቀድሞ ሥርዓት ለማኅበራት ይፈቀድ የነበረ የቤቶች ፕላን ቲፖሌጂ (በ175 ካሬ ሜትር እና በ160 ካሬ ሜትር በወቅቱ በከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር የሚሰራበት የቤቶች ዓይነት) በማዘጋጀት እንዲሁም ቀደም ሲል ተደራጅተው ጉዳያቸው በእንጥልጥል ላይ የሚገኙ ማኅበራትን የነበራቸውን ሰነድ ዓይነት በመሥራት 30 ያህል ሕገወጥ ማኅበራት እንዲደራጁ መርዳቱን የኮሚሽኑ ዘገባ ያስረዳል፡፡ በዚህም መሠረት 30 ያህል ማኅበራት እያንዳንዱ ግለሰብ 175 ካሬ ሜትር ቦታ ወስዶ ቤት እንዲገነቡ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ በምርመራው እንደደረሰበት ግለሰቡ በኮምፒዩተር በመታገዝ ለመኖሪያ ቤት የተከለለ ቦታን ካሳየ በኋላ በምህንድስና የተደራጀ ኃይል ይዞ ወደ ሥፍራው በመሄድ በመሬቱ ላይ ችካል ያስተክላል፣ የመኖሪያ ቤትን ሳይት ፕላኖችን ያዘጋጃል፣ መሬቱን ሸንሽኖ ያስረክባል፡፡ ግንባታውን (ሽንሸናውን) የደንብ አስከባሪዎች እንዳያስቆሙ ለማግባባትም ጉቦ እንዲሰጣቸው እንደሚደረግ፣ በአንድ ወቅትም እስከ 70ሺህ ብር ለደንብ አስከባሪዎች ጉቦ መስጠቱን አስፍሯል፡፡

ግለሰቡ ለሕገወጥ ሥራው አጋዥ የሆኑ ደብዳቤዎች፣ የሥራ ኃላፊዎች ፊርማዎች፣ ማኅተሞች አስመስሎ የሚጠቀም ሲሆን በተባባሪዎቹ አማካይነት በመዝገብ ቤት በፋይል እንዲቀመጡ ያስደርግ ነበር ብሏል፡፡

ኮሚሽኑም ግለሰቡን ከሚጠቀምበት ሲዲና ኮሚፒዩተር እንዲሁም በየክፍለ ከተሞች ከሚገኙ ተባባሪ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ የፍርድ ሂደቱ ቀጥሏል፡፡ በተጨማሪም 616 ሺህ 510 ካሬ ሜትር በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ቦታዎች በፍርድ ቤት ኮሚሽኑ ማሳገዱን ዘግቧል፡፡   

በጋዜጣው ሪፖርተር
 
< Prev   Next >