| የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ... |
|
|
| Sunday, 20 April 2008 | |
|
የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የቴሌፎን አገልግሎትን እያወከ ነው
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በቅርቡ ከጀመረው የፈረቃ የኃይል እደላ ጋር በተያያዘ የቴሌፎን አገልግሎት በከፊል የመቋረጥ ችግር እየተከሰተ መሆኑን፣ ችግሩም የኃይል እጥረቱ እስኪወገድ እንደሚቀጥል ቴሌ አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከኤሌክትሪክ ኃይል እጥረቱ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባና አንዳንድ አካባቢዎች የቴሌ መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ መሥራት ባለመቻላቸው የቴሌፎን አገልግሎት በከፊል የመቋረጥ ችግር እየተከሰተ መሆኑን አምኗል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ያጋጠማቸው የኮርፖሬሽኑ መሳሪያዎች በማዞሪያዎችና በደንበኞች መካከል የሚገኙ የኦኘቲካል ፋይበር ኔትወርክ የኬብል ማከፋፈያ ሳጥኖች ሲሆኑ፣ እነዚህ መሳሪያዎች የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጐት በዓይነትም ሆነ በጥራት ለደንበኞች ለማድረስ ከፍተኛ አቅም የሚሰጡና ከማዞሪያዎች የሚወጣውን ኔትወርክ ተቀብለው ወደ ደንበኞች የሚያከፋፍሉ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የከተማ ውስጥ የኦኘቲካል ፋይበር ኔትወርክ ማከፋፈያ ሳጥኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ በተጠባባቂነት የሚያገለግል ባትሪ ቢኖራቸውም እንዲህ ዓይነት ባትሪዎች በባህሪያቸው አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ በመሆኑና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሚገኘው ኃይል በአሁኑ ጊዜ በተፈጠረው የፈረቃ ኘሮግራም ምክንያት ለ12 ሰዓታት የሚቋረጥ በመሆኑ በተጠቀሱት መሳሪያዎች ላይ ከፍተኛ የኃይል እጥረት (ክፍተት) እያጋጠመ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በእነዚህ የኦኘቲካል ፋይበር ኔትወርክ ማከፋፈያ ሳጥኖች ላይ እያጋጠመ ያለውን የኃይል እጥረት ለመቅረፍ ፈፅሞ የስልክ አገልግሎት ሊቋረጥባቸው በማይችሉና በተመረጡ ውሱን ቦታዎች ላይ ተንቀሳቃሽ ጀኔሬተር በማዘጋጀት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ የሚገኙት እነዚህ የኬብል ማከፋፈያ ሳጥኖች እጅግ በጣም በርካታ በመሆናቸው የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥባቸው ሁሉም አካባቢዎች በሙሉ ተንቀሳቃሽ ጀኔሬተር ለማዘጋጀት ስለሚያዳግት በፈረቃ እየተሰጠ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እስኪቀረፍ ድረስ ሊቀጥል ስለሚችል ደንበኞች በሃገር አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን የኃይል እጥረት ግምት ውስጥ በማስገባት ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ በቴሌኮም አገልግሎት ላይ እየተከሰተ ያለውን ችግር ይወቁልኝ ብሏል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |