Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
Jul 05th
Home arrow Sections arrow የኤጀንሲው የማስታወቂያ፣...
የኤጀንሲው የማስታወቂያ፣... Print E-mail
Sunday, 20 April 2008
የኤጀንሲው የማስታወቂያ፣ የአየር ሰዓት አጠቃቀምና ሽያጭ ለሙስና ተጋልጧል

የአዲስ አበባ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ የሚያከናውነው የማስታወቂያ (የፕሮሞሽን)፣ የፕሮግራም ዝግጅት አመራረጥ፣ የአየር ሰዓት አጠቃቀምና ሽያጭ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን  የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ ያካሄደው ጥናት አረጋገጠ፡፡

በዚሁ ጥናት መሠረት የኤጀንሲው የድምፅና ምስል ዶክመንት ላይብረሪ አሠራር ለብልሽትና ለስርቆት የተጋለጠ ሲሆን የኤጀንሲው የድምፅና ምስል መቅረጫ መሣሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ መመሪያ ባለመኖሩ የኤጀንሲው ንብረት ለግል ጥቅም የሚውልበት ክፍተት መኖሩን ጥናቱ አመልክቷል፡፡

ጥናቱ በኤጀንሲው ያለው የኦዲዮቪዥዋል ላይብረሪ በሚገባ መልኩ የተደራጀ ባለመሆኑ የኤጀንሲው ኦዲዩ ካሴቶች ተጠያቂነትና ኃላፊነት በሌለው ሁኔታ በጋዜጠኞች እጅና 19 ሠራተኞች በሚቀመጡበት በአንድ ቢሮ ውስጥ ለቁጥጥርና ለክትትል በማይመች ሁኔታ የተቀመጡ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

 ለኤጀንሲው ከተለያዩ አካላት የሚሰጡ የዘፈን ክሊፖች ወደ ላይብረሪ ገቢ የሚደረጉበት ሰነድ በታይፕ የተዘጋጀና የኤጀንሲው አርማ የሌለው በመሆኑ እንዲሁም የህትመት ደረሰኝ ያልተዘጋጀ በመሆኑ የርክክብ ስርዓቱ ጠንካራ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከላይብረሪው በትውስት የሚወጡ ካሴቶች፣ ክሊፖች፣ ሲዲዎችና ቪሲዲዎች ሳይመለሱ የሚቀሩበትና ለግል ጥቅም የሚውሉበት አሠራር መኖሩ ተጠቁሟል፡፡

የኤጀንሲው ላይብረሪ በውስጡ ምን ያህል የድምፅና የምስል ዶክመንቶች ወይም ንብረቶች እንዳሉ ለማወቅ እንዲሁም ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል የባህር መዝገብ ወይም የንብረት ዓይነት በመለየት የሚመዘገብበት የመመዝገቢያ ስርዓት የሌለው መሆኑ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በላይብረሪ ንብረትነት የተቀመጡ የፕሮሞሽንና የልዩ ልዩ ዝግጅቶች ዶክመንት ያለ ክፍያ ለአንዳንድ ጠያቂዎች የሚሰጥበት አሠራር መኖሩ ተገልጿል፡፡

ጥናቱ፤ ኤጀንሲው ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚያደርገው “የማግባባት ጥረት”፤ በግልፅ የተቀመጠ የሥራ ፍሰት መመሪያ ያልተከተለና በድርድር ወቅት ለሙስና ተጋላጭ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የኮሚሽኑ ጥናት፣ ኤጀንሲው ከፕሮሞሽን ሥራ የሚያገኘውን የገንዘብ ድጋፍን በተመለከተ በፕሮሞሽን ሥራ ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች ብቻ ክፍያ መፈፀም ሲገባው፣ ክፍያው ለማይመለከታቸው የኤጀንሲው ሠራተኞች ክፍያ መፈፀሙን አስታውቋል፡፡ ለዚህም ኤጀንሲው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትን አስመልክቶ በሰራው የፕሮሞሽን ሥራ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያገኘውን የገንዘብ ድጋፍ፤ በፕሮሞሽን ሥራው የተሳተፉትንና ያልተሳተፉትን ሠራተኞች ሳይለይ በደመወዝ ስኬል መሠረት ማከፋፈሉ ተጠቅሷል፡፡

ኤጀንሲው የማስታወቂያነት ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞች እንዳይተላለፉ የማድረጊያ የቁጥርና የክትትል ስርዓት ስለሌለው የቁጥጥር ስርዓቱ ደካማ መሆኑ ታውቋል፡፡ በመዝናኛ ፕርግራሞች ላይ የሚተላለፉ ነጠላ ዜማዎችና ዘፈኖች በተደጋጋሚ የተወሰኑ ዘፈኖች ብቻ እንዲቀርቡ የሚደረግበት ሁኔታ እንዳለ ጥናቱ አስታውቋል፡፡ ይህንንም የአሠራር ብልሹነት ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር በኤጀንሲው እንደሌለ ታውቋል፡፡

ጥናቱ የኤጀንሲው አጋር ድርጅቶች ከመመሪያ ውጪ ያለውድድር ውል ፈርመው ፕሮግራም የሚያዘጋጁበት አሠራር መኖሩን አትቷል፡፡ ..ስለ ስፖርት እንነጋገር.. የሚለው ፕሮግራም አዘጋጆች ከሌሎች መሰል ፕሮግራም ማቅረብ ከሚችሉ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ጋር ሳይወዳደሩ በቀጥታ ውል ፕሮግራሙን እንዲያዘጋጁ መደረጉ በምሳሌነት ቀርቧል፡፡

በኤጀንሲው የሚተላለፉ ዜናዎች በተመለከተ የዜና መረጣ መስፈርቱ ለሶሰተኛ ወገን ግልፅ አለመሆኑና በዚህም ምክንያት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የማይገቡ የግል ድርጅቶች (ባለሀብቶች) ዘገባ የዜና ሽፋን እንዲያገኙ የሚደረግበት አሠራር መኖሩ ተገልጿል፡፡

የኮሚሽኑ ጥናት ጥናት ውስጥ የሥነ ምግባር መከታተያና የቅሬታ ሰሚ ክፍል ባለመኖሩ፣ በኤጀንሲው የሚከናወኑ የሙስና ተግባራትንና ብልሹ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማጋለጥ ለሚፈልጉ ተገልጋዮችና ሠራተኞች አቤቱታና ጥቆማ ማቅረብ አለመቻላቸው ገልጿል፡፡

ጥናቱ በኤጀንሲው ያለውን ለሙስናና ብልሹ አሠራር ክፍተት የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን በተመለከተ አማራጭ የማስተካከያ ስርዓቶችን አቅርቧል፡፡

በተሾመ ንቁ
 
< Prev   Next >