| ቻይናውያን የራሳቸውን... |
|
|
| Sunday, 20 April 2008 | |
|
ቻይናውያን የራሳቸውን የኢንዱስትሪ መንደር ሊገነቡ ነው
የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አለሙ ስሜ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስታወቁት የቻይና ባለሀብቶች በዱከምና በቢሾፍቱ ከተሞች መካከል የሚመሰርቱት መንደር ኢስት ኢንዱስትሪያል ዞን (East industrial Zone) በሚል ስያሜ የሚጠራ ነው፡፡ ባለሀብቶቹ ላቀረቡት የመሬት ጥያቄ በመጀመሪያ ዙር 2ዐዐ ሄክታር (2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር) ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ እንደ አቶ ስሜ ገለፃ በተዘጋጀው መሬት ላይ የኘሮጀክቱ ምዕራፍ አንድ የሆነው የ8ዐ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ ይከናወናል፡፡ በቅድሚያ ከሚገነቡት 8ዐ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የብረት ማምረቻዎች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ታውቋል፡፡ በቀጣይ ቀሪው 3ዐዐ ሄክታር (3 ሚሊዮን ካሬ ሜትር) ቦታ እንደሚዘጋጅ ቃል መገባቱን ያስታወሱት አቶ አለሙ “ቻይናውያኑ ለክልሉ መንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ኢንቨስትመንትን ከማበረታታት አንፃር የሊዝ ኪራይ ዋጋ አስተያየት እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል፡፡ የኢንዱስትሪ መንደሩ ምዕራፍ ሁለት ግንባታ የሚጀመረው ከሦስት ዓመት በኋላ መሆኑን ከአቶ አለሙ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአድአ ወረዳ በዱከምና ቢሾፍቱ ከተማ መካከል የኢንዱስትሪ መንደሩ ግንባታ የተፈቀደው ከ2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ቦታ ከአራት መቶ በላይ አርሶ አደር አባወራዎች የነበሩበት ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን ለኢንዱስትሪ መንደር ሲያስረክቡ በክልሉ መንግሥት መመሪያ መሰረት 2ዐ ሚሊዮን ብር ያህል ካሳ እንደሚከፈላቸው ታውቋል፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ ለሚቀጥለው የኢንዱስትሪ መንደሩ ግንባታ ሦስት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ የሚለቁት አርሶ አደሮች ግንባታው እስኪጀመር መሬቱን እያረሱ እንደሚጠቀሙ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡ በቅድሚያ የሚጀምሩት 8ዐ ኢንዱስትሪዎች አጠቃላይ ካፒታላቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ቢሆንም ትክክለኛውን አሀዝ ለመስጠት ያልተጠናቀቁ ሥራዎች መኖራቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡ ክልሉ ከሊዝ መሬት 4ዐዐ ሚሊዮን ብር ያህል ገቢ እንደሚያገኝም ከኃላፊው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ሥራ ሲጀምሩ 1ዐ ሺ ቋሚ እና ሁለት ሺ ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተገልጿል፡፡ በኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በባለሀብቶቹ መካከል አርብ እለት ከሰዓት በኋላ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡ የቻይና ኩባንያዎች በቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽንና በመንገድ ሥራ ከያዙት ከፍተኛ ሥራ በተጨማሪ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ተሳታፊ እየሆኑ ነው፡፡ በሰሜን ሸዋ ደጋም ላይ ኢስት ስሚንት በሚል መጠሪያ እየገነቡ ያሉት ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚጠቀስ ነው፡፡ በአሰግድ ተፈራና በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |