| ከምርጫው ወጥቻለሁ ጨዋታ፡-... |
|
|
| Sunday, 20 April 2008 | |
ከምርጫው ወጥቻለሁ ጨዋታ፡- መነሻውም መድረሻውም ሽንፈት ነው!!ዕድሜ ትምህርት ነው ይባላል፡፡ ጊዜ በጨመረ ቁጥር ተጨማሪ ልምድ ተጨማሪ እውቀት ይገኝበታል፡፡ ከሕፃን ይልቅ ወጣት፣ ከወጣት ይልቅ አዛውነት ይበልጥ በሳሎች ናቸው የሚባለው ጊዜ ተጨማሪ እውቀትና ብስለት ስለሚፈጥርባቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አካሄድ ስናይ ግን ጊዜ የሚሰጠው እውቀትና ብስለት ለመቅሰም የታደሉ አይመስሉም፡፡ ካለፈው ስህተታቸው የሚማሩ ሆነውም አልተገኙም፡፡ አሁንም የማኩረፍና የማግለል ፖለቲካ እየተጠቀሙ ናቸው፡፡ አንድ በአንድ በየተራ እኔ ከምርጫ ወጥቻለሁ፣ ትቸዋለሁ፣ ራሴን አግልያለሁ የሚል መግለጫ እንደ ተረኛ መድሃኒት ቤት ተራቸውን ጠብቀው እየወጡ ናቸው፡፡ ይህ ..ከምርጫ ወጥቻለሁ.. የሚል መግለጫና የሚሰጠው ማብራሪያና ምክንያት ፓርቲዎቹን ለትዝብት እየዳረገ ነው፡፡ ምክንያቱም አወጣጣቸው ሁለት ይዘትና ገፅታ ያለው ነውና፡፡ አንደኛው ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ነው፡፡ ሕዝብ ተመዝግቦ፣ ማንን እንደሚፈልግና እንደሚመርጥ ከገለፀ በኋላና በማይፈልጋቸው ተወዳዳሪዎች ላይ ተቃውሞውን በተለያዩ መንገዶች ከገለፀ በኋላ ወጥቻለሁ ማለት ትርጉሙ ተሸንፌያለሁ ነው፡፡ እንደማያሸንፉና እንዳላሸነፉ እያወቁ ወጥቻለሁ፣ ትቸዋለሁ ማለት ደግሞ ትርጉም የለሽ የተቃውሞ ዘዴ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተጨባጭ በሕዝቡ ዘንድ እየፈጠረው ያለው ስሜትም ይኸው ነው፡፡ “ይቀልዳል?” ነው የሚለው፡፡ ሁለተኛው ትርጉምና ገፅታ ደግሞ የፈለገው ችግር ቢያጋጥምስ ከምርጫስ መውጣት ተገቢ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡ በማንኛውም አገር በሚደረግ ምርጫ በተለያየ መንገድ የሚገለፁ ችግሮች አሉ፡፡ የዴሞክራሲ ተምሳሌት የምትባለዋ አገር ራስዋም “በፍሎሪዳ ምርጫው ተጭበርብሯል” የሚል ክስና ወንጀል አጋጥሟታል፡፡ ሆኖም ግን ከምርጫው ወጥቻለሁ፤ የሚል ፌዝ አልተከሰተም፡፡ በፓኪስታን ምርጫ ከመደረጉ በፊት ቤናዚር ቡቶ በሕይወት እያሉ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ኮሚሽኑ የሙሸረፍ ደጋፊ ስለሆነና ፍትሐዊ ምርጫ ስለማይሆን በምርጫው አንሳተፍም ብለው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ቤናዚር ቡቶ እኔ በምርጫ አልተሳፍም፤ የሚል ቋንቋ አይገባኝም፡፡ የፈለገው ችግር ይኑር፣ ተቃዋሚዎች በምርጫ መሳተፉ ይኖርባቸዋል ነበር፤ ያሉት፡፡ ሁሉም ፓርቲ የተሳተፈውም ..ቦይስቲስት.. አመለካከትን አውግዞ ነው፡፡ በቅርቡ በዚምባቡዌ በተደረገው ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ተደብደበው ቆሳስለውና አባብጠው ነበር ቤት የገቡት፡፡ ነገር ግን በምርጫ አንሳተፍም፤ የሚል ቃል አልወጣቸውም፡፡ ተወዳድረውም ትልቅ ውጤት አግኝተዋል፡፡ በጋና በምርጫው ተሳትፈው ደህና ውጤት ያገኙት ተቃዋሚዎች አሸናፊዎች ናችሁ፤ ካልተባልን በፓርላማ አንሳተፍም አሉ፡፡ ሕዝቡ አንሳተፍም ማለታቸውን አልተቀበለውም፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ቀጣቸው፡፡ ከዛም በኋላ በወጣው ምርጫም ቀጣቸው፡፡ መሳሳታቸውን አምነው ይቅርታ ሲጠይቁና ሲስተካከሉ ከአስራ ሁለት ዓመት በኋላ እንደገና መርጦ በጀሪ ሮሊንግስ ምትክ ወደ ስልጣን አወጣቸው፡፡ ባለፈው ምርጫ የእኛ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባን አለመረከባቸውና ፓርላማ በፀጋ አለመግባታቸው በአንዳንዶች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ አልነበረም፡፡ አሁን መለስ ብሎ ሲያየው መግባት ነበረባቸው ይላል፡፡ እንኳን ሕዝቡ በርካታ የቅንጅት አባላትም መግባትና መረከብ ነበረን በማለት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን በምርጫ አንሳተፍም ወጥተናል የሚል ጨዋታ ከአሁን በፊት በአገራችንም በሌሎች አገሮችም ተሞክሮ ያልሰራና ..የተበላ እቁብ.. መሆኑን ነው፡፡ የእኛ ተቃዋሚዎችም ከዚህ የአገርና ዓለም አቀፍ አካሄድ መማር አለባቸው፡፡ መታገል አለባቸው፡፡ ትክክለኛ መንገድ ይዘው የሚጓዙ ተቃዋሚዎች ጥቂት ቢሆኑም አሉና እነሱን በርቱ ተባረቱ፤ አንሳተፍም የሚሉት ደግሞ ታረሙ ሊባሉ ይገባል፡፡ ገዢው ፓርቲ ላለው ድክመት ተጠያቂዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው ማለት እንደሌለበት ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላላቸው የውስጥ ድክመት ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነው ማለት የለባቸውም፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሮግራም፣ ስልትና ስትራቴጂ የላቸውም፡፡ ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነውን? አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉባኤ አያካሄዱም፡፡ ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነውን? አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕገ ደንብና መተዳሪያ ደንብ የላቸውም፡፡ ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነውን? አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአመራር ምርጫ አያካሄዱም፡፡ ተጠያቂው ገዚው ፓርቲ ነውን? አብዛኛዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ንብረታቸውንና ገንዘባቸውን ኦዲት አያስደርጉም፡፡ ሪፖርትም ለአባላት አያቀርቡም፡፡ ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነውን? አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲከፋፈሉ፣ ሲሰነጣጠቁ ሲወነጃጀሉ ይሰማሉ፤ ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነውን? አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት እየመለመሉ ከመጨመር ይልቅ አባሎቻቸውን እየቀነሱ፣ እያሸሹ ባዶ እየቀሩ ናቸው፡፡ ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነውን? አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገዢው ፓርቲ በሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ላይ ሂስ ሲያቀርቡና አማራጭ ሲያስቀምጡ አይሰሙም፡፡ ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነውን? ወዘተ. ወዘተ. ገዢው ፓርቲ እንቅፋት አይፈጥርም፣ ተቃዋሚዎች እንዲያሸንፉ በፀጋ ይቀበላል ማለታችን አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ተቃዋሚዎች እዚያ ከመድረሳቸው በፊት በውስጥ ድክመት ምክንያት አቅማቸውን እያዳከሙ ነው፡፡ የአሁኑ ወጥቻለሁ፤ አልሳተፍም ማለት ደግሞ ገዢውን ፓርቲ ያጠናክራል እንጂ አያዳክምም፡፡ አድካሚ ጨዋታን በፎርፌ ማሸነፉ ማን ይጠላል? ይህን ሁሉ የምንለው ኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሚያስፈልጋት ነው፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ስለናፈቀን ነው፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ለኢትዮጵያ መንግሥት መጎልበት ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወት ነው፡፡ ወጥቻለሁ፣ ትቸዋለሁ፤ እያሉ ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር አይቻልምና እባካችሁ፣ እባካችሁ ጨርቄን ትታችሁ በርቱ ተበራቱ፡፡ ጠንካራ ፓርቲም ሁኑ፡፡ አትሽሹ፡፡ በትግል ማዕበል ውስጥ ቅዘፉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |