| አማራጭ የሌለበት ምርጫ |
|
|
| Sunday, 20 April 2008 | |
|
ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የአካባቢና የማሟያ፤ ምርጫ ያለው የምርጫ ድባብ በ1997 ዓ.ም. ከተካሄደው ምርጫ አንፃር ወደ ኋላ መጓዛችንን ያመላክታል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አላማቸውን ለህዝብ ለማስተዋወቅ በተዘረጉ ኘሮግራሞች እንዳይጠቀሙ፣ ዓላማቸው በተለያዩ ሰበቦች እንዳይተላለፍ መደረጉ ብሎም ዛቻና ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው መቆየቱን ሲናገሩ ነበር፡፡
የገዢው ፓርቲ ማስታወቂያዎች ጎልተው በወጡበት ሁኔታ አንዳንድ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫም አገለሉ፡፡ ምርጫ ማለት በልዩነት ውስጥ የሚደረግ ውሳኔ ሆኖ ሳለ አሸናፊው ቀድሞ በታወቀበት ሁኔታ ምርጫ ማለት አያስደፍርም፡፡ ለዚህም ይመስላል ምርጫው በተካሄደ በሁለተኛው ቀን የምርጫው ውጤት በምርጫ ቦርድ ሳይነገር “እንኳን ደስ ያለን” በሚል የተጨፈረው፡፡ አማራጭ ተወዳዳሪ በሌለበት ሁኔታ አሸናፊዎቹን እያወቅን ምርጫ መካሄዱ ምርጫውን የይስሙላ ያደርገዋል፡፡ (ሊያ፣ ከሳሪስ) ለከተማው መጻሕፍት ቤት ምቹ ቦታ መጋቢት 28 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ..በ27 ሚሊዮን ብር ለሚገነባው ቤተ መጻህፍት ማሰሪያ የሚውል ቦታ እስካሁን አልተገኘም.. የሚለውን አነበብኩ፡፡ ስለከተማችንና ስለህዝብ በሃቅ ለሚያስብ፣ ታሪካዊነቱም ሆነ ከማዕከላዊ አቀማመጡ፣ ለመዲናችን ታላቅ መጻህፍት ቤት ትክክለኛ መነሃሪያ ይሆናል የምለው፣ በፒያሳ እምብርት ላይ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ጎን የሚገኘው ቦታ ነው፡፡ ቦታውን ይዘውታል የተባሉት ባለሃብት አገሪቱን እወዳለሁ እንደማለታቸው ቦታውን አልሰጥም አይሉም፡፡ ቦታው ላይ የብዙሃኑ መገልገያ የሆነ ቋሚ ቅርስ ቢሰራበት የሚደሰቱ ይመስለኛል፡፡ አስተዋፅኦ ከማድረግም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ይህም ካልሆነ ሌላ አማራጭ ተፈልጎ ቤተ መጻሕፍቱ መገንባት ይኖርበታል፡፡ ( ከቦሌ) የኢቴቪ ሽወዳ ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሕዝቡ በነቂስ ለምርጫ መውጣቱን ለማሳየት ብዙ ሲደክም አስተዋልኩኝ፡፡ የሚገርመው የጣቢያው ኃላፊዎች የምርጫ ረዣዥም ሰልፎችን ከፋይላቸው እያወጡ፣ ያለፈው ሳምንት ምርጫ እያስመሰሉ ለማቅረብ ሲደክሙ፣ ሕዝቡ ይታዘበናል አለማለታቸው ያስገርማል፡፡ ሌላው ቀርቶ የጣቢያው ኃላፊዎች ያስተላለፋቸው የፋይል ምስሎች ላይ ያሉ ሰዎች ቢጫ የመራጮች ካርድ መያዛቸውን እንኳን ጨርሶ ልብ አላሉም፡፡ እንደሚታወቀው የአሁኑ የመራጮች ካርድ ውሀ ሰማያዊ ቀለም የያዘ መሆኑን እያወቅን ግብር በምንከፍልበት ቲቪ ስንሸወድ ያሳፍራልም፣ ያሳዝናልም፡፡ (መሀሪና ጓደኞቹ፣ ከአራት ኪሎ) አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ እውነት ተናግሮ የመሸበት ይደር አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ “በበልግ ዝናብ እጥረት ምክንያት የውሀ እጥረት አይከሰትም”፡፡ ብሎ መናገሩን ያነበብኩት ከእናንተው ሪፖርተር ነበር፡፡ በዚሁ ጋዜጣ ሚያዚያ 8 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በወጣው ዜና ደግሞ “በውሃ ጥም የተደፈቁ ቀበሌዎች” በሚል ህብረተሰቡ ምን ያህል እየተሰቃየ እንደሆነ አስነብባችሁናል፡፡ የውሃና ፍሳሽ የአደባባይ ሚስጥር የሆነውን የውሃ እጥረት ችግር ከበልግ ዝናብ ጋር አይያያዝም ብሎ ማወጁ ችግሩ ሰው ሰራሽ ወይም የባለሥልጣኑ ድክመት መሆኑን በተዘዋዋሪ የሚያሳይ ነው፡፡ ዛሬ በከተማዋ በተለይም በከተማዋ ዳርቻ የቧንቧ ቆጣሪያቸውን ለይስሙላ ገትረው በውሃ እጦት የሚሰቃዩ ወገኖች ቁጥር ቀላይ አይደለም፡፡ ባለሥልጣኑም “ይሄ ነው ምክንያቴ” እንኳን ሳይል አገለግልሃለሁ ብሎ የቆመለትን ህብረተሰብ ዘንግቶታል፡፡ ሁል ጊዜም የአቅም ማነስና የከተማ ህዝብ መጨመር ለውሃ እጥረት እንደምክንያት የሚደረድራቸው ዲስኩሮች ናቸው፡፡ ለባለሥልጣኑ አቅሙን የሚያጠነክርለት ሕዝቡ ይሆን? እንደ መንግሥት መሠረታዊ የሆነውን የውሃ ማግኘት መብት ማሟላት ሲጠበቅበት በአቅም የለኝም ሰበብ ህብረተሰቡን ሲያንገላታ ይታያል፡፡ ባለሥልጣኑ ለምን መዋቅሩን አያስተካክልም፣ አስተዳደሩን ለምን አይፈትሽም? የተጀመሩ ኘሮጀክቶችን ለምን በአግባቡ አይፈፅምም? ለችግሩ አማራጭ መንገዶችን ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ለምን አይቀይስም? ብዙ ሊነሱና ባለሥልጣኑን ሊያስወቅሱ የሚችሉ የተዝረከረኩ አሰራሮች ህብረተሰቡን ለውሃ እጦት ዳርጐታልና ባለሥልጣኑ አሠራሩን ይፈትሽ፡፡ የህብረተሰቡን ሰብአዊና ሕገ መንግሥታዊ መብት ይጠብቅ፡፡ (ሩሃማ በላይ፣ ከመገናኛ) ቀዝቃዛው ምርጫ ሰሞኑን በተካሄደው ምርጫ ህዝቡ የሚፈልገውን ፓርቲ ወይንም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ በማጣቱ የምርጫው ሂደት እጅግ ቀዝቃዛ እንደነበር እሙን ነው፡፡ በርካታ የውጭ መገናኛ ብዙሀን ምርጫው የምርጫ መስፈርትን ያሟላ እንዳልነበረ ገልፀዋል፡፡ በምርጫው ለመሳተፍ ጥረት ሲያደርጉ ከቆዩ ፓርቲዎች መካከል ሦስት ፓርቲዎች ከምርጫው እራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም የገዢው ፓርቲ በምርጫው ሂደት ላይ ኢዴሞክራሲያዊና ኢፍትሐዊ አሠራር በማንገሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መራጩ ህዝብ ደግሞ የሚመርጠውን ፓርቲ ያጣበት ምርጫ በመሆኑ የእሁዱ ምርጫ ቀዝቀዝ ባለ መልኩ ተካሂዷል፡፡ የአሁኑ ምርጫ አገራችንን ወደ ኋላ የጐተተ መሆኑን ያየንበት ነውና ዴሞክራሲን እናሰፍናለን የሚሉ ፓርቲዎች ህዝቡን ማዕከል ያደረገ አላማ ይዘው ይንቀሳቀሱ እላለሁ፡፡ (በረከት፣ ከሳር ቤት) ኸረ ኢኮኖሚስቶቹ ይስሙ! በእለተ እሁድ ሚያዚያ 5 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ገፅ ላይ በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጃኪም ቮን ብራውን የዋጋ ተመን ማውጣትና መቆጣጠር በኢኮኖሚ እድገት ላይ ጫና ስለሚፈጥር የዋጋ ንረት መንስኤና ችግሮቹን ለማወቅ ተጨማሪ የተወሰኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት በሂልተን ሆቴል ተገኝተው ማብራራታቸውን አይቻለሁ፡፡ የእኛ ፖሊሲ አውጭዎች ሐገር በቀል ኢኮኖሚስቶችን መቀለጃ ከማድረግ ዘለው ሲሰሟቸው አይታይም፡፡ እስኪ ባይሆን እኒህኞቹን ስሟቸው፡፡ ማረሚያ በረቡዕ ሚያዚያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ገጽ ዜና ..ለድርቅ ተጠቂዎች 7 ቢሊዮን ብር ዕርዳታ ያስፈልጋል.. በሚል ርዕስ በወጣው ዜና ላይ የስሌት ስህተት ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም “ከ670 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል” በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ እየጠየቅን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ዝግጅት ክፍሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |