|
Sunday, 20 April 2008 |
|
የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከምርጫው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በክብረ በዓል ለተገኘው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር ተቃዋሚዎችንና ብሪታንያን ወረፉ፡፡
ዚምባብዌ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችበትን 28ኛ ዓመት በተከበረበት ባለፈው ሳምንት፣ "አገራችን ለመስረቅ የሚፈልጉ ሌቦች ይውደሙ" በሚል መፈክር ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡
የዚምባብዌ የምርጫ ውጤት እስካሁን ያልተገለፀ ሲሆን ተቃዋሚዎች ድምጽ እንደገና እንዲቆጠር ያቀረቡትን ማመልከቻ ፍርድ ቤት ውድቅ ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ84 ዓመቱ ሙጋቤ፣ በስታዲየም የነፃነት በዓል ላይ "ሕዝባችን በእንግሊዞች ዘረኛ ሰፋሪዎች ከላይ እስከ ታች መያያዝ ተገርሟል. . ". ሲሉ እንግሊዝን ወቅሰዋል፡፡
"የእንግሊዝ ማሽኖች" የሚሏቸው፣ ተቃዋሚዎችም ሕዝቡ እንዲተፋቸው ሲያሳስቡ እነርሱንም "የእንግሊዝ ሸሪካ የሆኑት ሌሎች አምባገነኖች" ሲሉ ተችተዋቸዋል፡፡
አንጎላ፣ የተመድ ቢሮ እንዲዘጋ ወሰነች
በአንጎላ የሚገኘውን የሰብዓዊ መብት ጠባቂ ቢሮውን ተመድ ሊዘጋ ነው፡፡ ድርጅቱ ቢሮውን የሚዘጋው የአንጎላ መንግሥት ከሚቀጥለው ግንቦት አጋማሽ ጀምሮ ቢሮው መዘጋት እንዳለበት በማሳሰባቸው መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የተመድ ከፍተኛ ኮሚሽነር ግን፣ አንጎላ አሁንም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጋረጠባት አገር መሆኗን ጠቅሰው በውሳኔው ቅር መሰኘታቸውን አልደበቁም፡፡
ውሳኔው የተገለፀው በተመድ እንደበፊቱ በአንጎላ ተግባሩን እንዲቀጥል ለማድረግ ተጀምሮ የነበረው ንግግር መቋረጡን ተከትሎ ነው፡፡
አንጎላ በርስ በርስ ውጊያ ለ30 ዓመታት ያህል ስትታመስ የቆየች አገር መሆኗ ይታወሳል፡፡ ---------- ካርተር የሐማስ መሪን አነጋገሩ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በሶሪያ የሚገኙትን የሐማስ መሪ ካሀሊድ መሻልን አነጋገሩ ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በቢቢሲ ዘገባ መሠረት ጂሚ ካርተር ከካሀሊድ መሻል ጋር ያደረጉት ውይይት በእስራኤልና በፍልስጥኤማውያን መካከል ያለውን ውዝግብ ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡ ካርተር ሰሞኑን በመካከለኛው ምስራቅ ባደረጉት ጉብኝት የእስራኤልንና የሶሪያን ባለስልጣናት ማነጋገራቸው ታውቋል፡፡
ካርተር ከእስራኤል መሪዎችን ባነጋገሩበት ወቅት አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን ከሀማስ መሪዎች ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀውላቸዋል፡፡ በዚህም እስራኤል ከፍልስጤም መሪዎች ጋር ለመነጋገር የያዘችው አቋም ሊፈርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ጂሚ ካርተር እ.ኤ.አ በ2002 የአለም አቀፍ የሰላም ኖቬል ሽልማት ተሸላሚ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
ኮፊ አናን አዲሱ የኬንያ ጥምር መንግሥት ትብብሩን እንዲያጠናክር አሳሰቡ
የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን፤ አዲሱ የኬንያ ጥምር መንግሥት ትብብሩን እንዲያጠናክር የኬንያን ድህነት ለማስወገድ በጋራ መስራት እንዳለበት ማሳሰባቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ኮፊ አናን ኬንያ የተመሰረተው ጥምር መንግሥት ልዩነቱን ወደ ጎን በማድረግ በኬንያ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ድህነትና አካባቢያዊ ልዩነት የሚያስወግድበትን መንገድ መቀየስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
"የኬንያ የፖለቲካ ኃይል በቀድሞ ተቀናቃኝ ወገኖች በፍትሃዊ ሁኔታ ክፍፍል ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኬንያ ኃይሎች ተቀናቃኝ ሳይሆኑ አጋር ድርጅቶች ሆነዋል" በማለት ገልፀዋል፡፡
ኮፊ አናን በኬንያ የተፈጠረውን የምርጫ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በምርጫው ውዝግብ ከአንድ ሺ አምስት መቶ በላይ ኬንያውያን ሲሞቱ ከስድስት መቶ ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ |