Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱና ፈተናዎቹ
የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱና ፈተናዎቹ Print E-mail
Sunday, 20 April 2008
“ዴሞክራሲን ደረጃ በደረጃ እያጠናከርነው ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ፓርላማ የገቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የነበራቸውን ስጋት ለማስወገድ ተወያይተናል፡፡ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አደረጃጀትን ለውጠናል፡፡ በፓርላማ ውስጥ አነስተኛ መቀመጫ ያላቸው አካላት አጀንዳ በማንሳት በተወሰኑ ቀናት ለክርክር እንዲቀርብ የሚያደርግ የፓርላማ አሰራር ቀርፀናል፡፡
. . . ስለዚህ በተቋሞቻችን የነበሩት ችግሮች ላይ በተከታታይ መሻሻል እያደረግን ነው . . “ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከኒውስዊክ ፣የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ጥረት አሁን ያለበትን ደረጃ እንዴት ይገልፁታል?፣ በማለት ለተጠየቁት ጥያቄ ከመለሱት መልስ የተቀነጨበ ነው፡፡

ከዴሞክራሲያዊ ተቋማት መካከል ዋነኛዎቹ የሆኑት ፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ ቦርድ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱ ተቋማት ተሻሽለዋል ብለው ያምናሉ፡፡ ከሳምንት በፊት በፓርላማው የፀደቀውን የተሻሻለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ተከትሎ ከተቃዋሚ  አመራሮች መካከል አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ አቶ መስፍን መንግሥቱና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የዴሞክራሲው ዋና ተቋም የፖለቲካ ፓርቲው አደረጃጀት በአዲስ ሕግ የተነሳ አደጋ ላይ እንደወደቀ ገልፀዋል፡፡ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተወካይ አቶ ሺፈራው ጃርሶ ግን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉ በአዋጁ ላይ የተጠቀሱት ቁጥጥሮች ህግን ከማስከበርና ዴሞክራሲን ከመገንባት አንፃር ታይተው የተዘጋጁ መሆኑን አመልክተው አንዳንድ ፓርቲዎች ከውጭ አገር ባመጡት ገንዘብ ምክንያት እርስ በርሳቸው የተጋጩበትና ፓርቲያቸውም ህልውና እንዳይኖረው ያደረጉበት ሁኔታ መኖሩን እንደ ምሳሌ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ፋይናንሳቸውን ለምርጫ ቦርድ ማስመዝገብ እንዲያብቡ የሚረዳቸው መሆኑን ገልፀው ነበር፡፡

የተሻሻለው  ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ምርጫ ቦርድ በፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ ዘልቆ ጣልቃ እንዲገባ መፍቀዱ ትችት ገጥሞታል፡፡

አዋጁ በመግቢያው ላይ  የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰርቱ እና በአባልነት ሲንቀሳቀሱ ስለሚኖራቸው መብትና ግዴታ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊከተሏቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሆዎችን በመደንገግ ህጋዊ ሰውነት አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ህጉ እንደታወጀ ይገልፃል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 9(4) መሠረት የምዝገባ ጥያቄ ማመልከቻ ያቀረበ የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባ የአገልግሎት ክፍያ እና በየጊዜው  የመሰረታዊ ሰነዶች ማሻሻያ ክፍያ ይከፍላል፡፡ በአንቀጽ 8(6) መሠረት የክፍያውን መጠን የሚወስነው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 9(4) መሠረት ምርጫ ቦርድ ለምዝገባ አስፈላጊ የሆኑ ተያያዥ መረጃዎች እንዲቀርብለት እንዲሁም በአዋጁ መሠረት በሚደረግ እንቅስቃሴ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መረጃ ወይም ማብራሪያ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ በአንቀጽ 9(5) መሠረት ቦርዱ የሚቀርብለትን ማመልከቻና አባሪ ሰነዶች ተቀብሎ በመመርመር ሰነዶቹ የተሟሉ እና ትክክለኛ መሆናቸውን፣ ፓርቲው ህገ መንግሥቱንና አዋጁን የሚያከብርና የሚያስከብር መሆኑን በማረጋገጥ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲውን ዋና ጽህፈት ቤት በመጎብኘት የምዝገባ ማመልከቻውን በተቀበለ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ የምዝገባውን ፎርማሊቲ አጠናቅቆ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለአመልካቹ ይሰጠዋል፡፡

በተጨማሪም በአዋጁ ከአንቀጽ 9(14) እስከ 9(17) በተዘረዘረው መሠረት ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴን ይከታተላል፤ ተገቢውን መረጃ ይይዛል፤ የፖለቲካ ፓርቲን የገቢ ምንጭ የወጭ ዝርዝር እና ንብረት ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤ ህገ ወጥ ድርጊት ተፈፅሞ ሲያገኘውም አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት የተደረገ  የድጋፍ አጠቃቀም ዝርዝር እና ስለፖለቲካ ፓርቲ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወቅታዊ እና ዓመታዊ ሪፖርት ያቀርባል፤ የኦዲት ሪፖርት እንደደረሰው ለህዝብ ይፋ ያደርጋል አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውም እንዲመረመር ሊያዝ ይችላል፡፡

ምርጫ ቦርድ  ክፍያን በዘፈቀደ እንዳይወስን ማን ይቆጣጠረዋል? ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠይቃቸው መረጃዎች ይዘት ገደብ እስከየት ነው? ፣ህገ መንግሥቱንና አዋጁን የሚያከብርና የሚያስከብር፣ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ፓርቲ በህጉ ንፍቀ ክበብ ውስጥ ሆኖ ሕገ መንግሥቱንና አዋጁን የተሻለ በሚለው መልኩ ለመቀየር መንቀሳቀስ አይችልም ማለት ነው? ምርጫ ቦርዱ የሚወስነው እርምጃ ፣ህገ ወጥ ድርጊት ተፈጽሞ፣ መሆኑን የሚያረጋግጠው ማን ነው? በአዋጁ ከተደነገገውና በዝርዝር ከተቀመጠው ህገ ወጥ ድርጊት ውጭ ምርጫ ቦርድ በራሱ ጊዜ አንድን ድርጊት ፣ህገ-ወጥ፣ ለማለት ስልጣን አለውን?

ማንኛውም በአዋጁ መሠረት የተመዘገበ የፖለቲካ  በየዓመቱ ወይም ቦርዱ በሚወስነው ጊዜ ፓርቲው በኦዲተር የተረጋገጠ የሃብትና እዳ ሰነድ በፓርቲው መሪ ፊርማ ለቦርዱ የፅሁፍ ሪፖርት የማቅረብ፤ ሪፖርቱም የፖለቲካ ፓርቲውን የገቢ ወይም የሃብቱን ምንጭ የማካተት ግዴታ እንዳለበት የአዋጁ አንቀፅ 19(1) ይገልፃል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 42 መሠረት መንግሥት በፌዴራልና በክልል ምክር ቤቶች ውክልና ላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ፤ ለፌዴራል ወይም ለክልል ምክር ቤቶች የምርጫ ተግባር ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚውል ድጋፍ እንደሚሰጥ ቢገለፅም የፖለቲካ ፓርቲዎች የገቢ ወይም የሃብት ምንጭ የመግለፅ ግዴታ መጣሉ እንደተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች አገላለፅ ፣ህልውናቸውን ይፈታተናል፣፡፡ ባለፉት ዓመታት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከተወዳዳሪነት ይልቅ የጠላትነት ግንኙነት መስርቶ እንደመቆየቱና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣አባሎቻችንን እና ደጋፊዎቻችንን ያሰቃያል፣ ክስ በተደጋጋሚ ስሙ እንደመነሳቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚረዳ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ስሙ መመዝገብ አለበት መባሉ እንደ መሪዎቹ አባባል ፓርቲዎቹን ከማጥፋት መድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ደግሞ አደጋ ላይ ከመጣል አይተናነስም ባይ ናቸው፡፡

በአንቀጽ 45 መሠረት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጥ ድጋፍ የሚከፋፈለው በፌዴራል ወይም በክልል ምክር ቤቶች ባላቸው መቀመጫ ብዛት መሠረት ሲሆን፤ ለፌዴራል ወይም ለክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ተግባር የሚሰጥ ድጋፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ዕጩ ብዛት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን የሴት ዕጩዎችን ብዛት፣ መሠረት በማድረግ የሚከፋፈል ይሆናል፡፡ እነዚህ መስፈርቶች በአንቀጽ 44 መሠረት ፣ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጥ የመንግሥት ድጋፍ በፍትሃዊነት እና ያለ አድልኦ መፈፀም አለበት፣ ከሚለው ድንጋጌ ጋር ስለመጣጣሙ አጠራጣሪና አከራካሪ ነው የሚሆነው፡፡

በአንቀጽ 51(1)  መሠረት የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የገንዘብ ምንጭ ከአባላቱ የሚሰባሰብ የአባልነት መዋጮ፣ ቦርዱ አጥንቶ በሚያስቀምጠው ጣሪያ መሠረት በኢትዮጵያውያን ግለሰቦች እና ኩባንያዎች የሚደረግ ስጦታ ወይም እርዳታ፣ ከመንግሥት ከሚሰጠው ድጋፍና ዕርዳታ ሊሆን ይችላል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያውያን ግለሰቦች እና ኩባንያዎች የሚደረግ ስጦታን ወይም እርዳታን አጥንቶ ጣሪያ እንዲያስቀምጥ ውክልና ሰጥቶታል፡፡ በአሜሪካ ይህ ጣሪያ በኮንግረስ ነው የወጣው፡፡

ሁሉንም ፖለቲካ ፓርቲዎች ባስማማ መልኩ  የአሜሪካ ምርጫ ኮሚሽን እንኳን የሌለውን ውክልና ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውጭ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣ገለልተኛ አይደለም..፣ ለሚሉት ምርጫ ቦርድ ውክልና መስጠቱ ምን አስፈለገ? የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ተዋናይ የሆኑት የፓርላማ አባላት በሕግ ቢወስኑትስ አይሻልም?

ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሚያዘጋጀው የሂሳብ መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲውን የገንዘብ ምንጭ፣ መዋጮ ያደረገውን ወይም ስጦታ የሰጠውን ወይም ቃል የገባውን ሰው ስም፣ ቃል የተገባ መዋጮ ወይም ስጦታ ካለም የሚከፈልበትን ጊዜ እና አጠቃላይ ሰው ስም፣ ቃል የተገባ መዋጮ ወይም ስጦታ ካለም የሚከፈልበትን የፖለቲካ ፓርቲውን የሂሳብ እንቅስቃሴ ሊያካት ይገባል፡፡ ምንጭ መጥቀሱ ከላይ በተገለፀው ምክንያት የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ቢመስልም ፣ቃል የተገባ መዋጮ ወይም ስጦታ፣ የሚከፈልበት ጊዜ መጠቀስ አለበት ማለት ግን የተጋነነ ነው፡፡ ጊዜው በግልፅ ለማሳወቅ የሚቸገር የፓርቲው አባል ወይም ደጋፊ ቢኖርስ? የኦዲት ስራውን እንዳያደናቅፍ ከተሰጋም ወደ ሌላ ዓመት መሸጋገሩን ፓርቲው በታሳቢነት ማስቀመጥ ይችላል፡፡ በዚያ ላይ በአንቀጽ 55(2) መሠረት የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የገቢና ወጭ ሂሳብ አያያዝ ስርዓት በሂሳብ አያያዝ ልምድ ተቀባይነት ባለው መንገድ መሆን እንዳለበት በመገለፁና ትክክለኛ ጊዜን ማሳወቅ ደግሞ በተለመደው የሒሳብ አያያዝ ስርዓት ግዴታ ባለመሆኑ በዚህ መልኩ መተርጎም ይኖርበታል፡፡

ፓርላማው ያፀደቀው ይህ አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቶ ህግ ከመሆኑ በፊት ምናልባትም መጠነኛ መሻሻል ይደረግበት ይሆናል፡፡ የሆነ ሆኖ በመግቢያችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳሉት የተቋሞቻችን ድክመትና አሰራር መስተካከል  በ1997 ዓ.ም. የተደረገው ምርጫ አጀማመሩ ያማረ የነበረው በመንግሥት፣ በሕዝቡና በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎ ነበር፡፡ ይህ በመጭው ምርጫ 2ዐዐ2 እንዲደገም ለማድረግ መንግሥትና ተቃዋሚዎች የጥላቻና የንቀት ስሜትን አስወግደው በመከባበርና በመቻቻል ችግር ያለባቸውን ተቋሞች ማሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም ወሳኙና የሁለቱን አለመግባባት ለመፍታት በሕገ መንግሥቱ በተቋቋመው በምርጫ ቦርድ አወቃቀር፣ አደረጃጀትና አሰራር ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት ላይ እስካልደረሱ ድረስ እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ ከመተያየት  በዚህም የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ችግሮች ከአመት አመት ይንገዋለላሉ፡፡

በሰለሞን ጐሹ
 
< Prev   Next >