| አገልግሎት ሰጪዎች ትርፍ ብቻ... |
|
|
| Sunday, 20 April 2008 | |
|
አገልግሎት ሰጪዎች ትርፍ ብቻ ሳይሆን ሸማቹንም ይመልከቱ
ከኤክሳይስ ታክስ ቅነሳ ጋር በተያያዘ ቅነሳው የሚመለከታቸው ምርቶች በገበያ ለውጥ አምጥተዋል ወይ? የሚለውን ለመመልከት የተወሰነ የገበያ ቅኝት አድርጌ ነበር፡፡ ነገር ግን ጉዳይ ውጪ ሌላ ነገር ለመመልከት ችያለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ የመዝናኛ ሥፍራዎች ወይም መካከለኛ ገቢ ያላቸው ተጠቃሚዎች የሚገለገሉባቸው እንደ ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ ባር፣ ካፌ የመሳሰሉት ለተጠቃሚው የሚያቀርቧቸው የለስላሳ መጠጦችና የታሸጉ ዋጋ ተመሳሳይ ነው፡፡ በእነዚህ አገግሎት መስጫዎች 300 ሚሊ ሊትር የሚይዙት ኮካኮላ፣ ፔኘሲና ተመሳሳይ ምርት በሦስት ብር ይሸጣሉ፡፡ በአንዳንድ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ዋጋቸው እስከ አምስት ብር ይደርሳል፡፡ የቤት ጥራታቸውና አገልግሎታቸው አሻሻልን ዋጋ ጨምረው የሚሸጡት ይህን ያህል ባያስገርመንም ይህ ነው የሚባል መስተንግዶ ሳይገኝ ቤቱም ተራ ብለን የምንጠራው ዓይነት ሆኖ አንድ ለስላሳ በአምስት ብር ሲሸጥ ይከብዳል፡፡ በታሸጉ ውሃዎችም ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል፡፡ ግማሽ ሊትር የታሸገ ውሃ በመካከለኛ ወይም አነስተኛ መዝናኛ ቦታዎች ሦስት ብርና ሦስት ብር ከአምሳ ሣንቲም፣ አንድ ሊትር ተኩል የሚይዘው ደግሞ አምስትና ስድስት ብር ይሸጣሉ፡፡ የታሸጉ የውሃዎችና የለስላሳ መጠጦች ዋጋ በመጠኑም ቢሆን ቅናሽ የሚታየው በትናንሽ መደብሮች ውስጥ ነው፡፡ በሁሉም ሳይሆን በአንዳንዶቹ አንድ የለስላሳ መጠጥ በሁለት ከሃምሣ ሣንቲም ማግኘት ይችላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህም መደብሮች ዋጋውን ወደ ሦስት ብር እያሸጋገሩት በመሆኑ የለስላሳ መጠጦች መደበኛ የመሸጫ ዋጋ ሦስት ብር እንዲሆን አድርገውታል ማለት በለስላሳ መጠጦችና በታሸጉ ውሃዎች ዋጋ በእርግጥም ሦስት ብር መድረስ ነበረበት ወይ ብለን ስንጠይቅ ፈፅሞ መሆን እንደሌለበትና ከፋብሪካዎቹ በሚረከቡትና እነርሱ በሚሸጠበት ዋጋ መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ እንረዳለን፡፡ የትርፍ መጠናቸው በጣም የተለጠጠ በመሆኑ ሸማቹን እያነጋገረ ነው፡፡ ጉዳይ የሁለት የለስላሳና የታሸጉ ውሃ ፋብሪካዎች ኃላፊዎችንና የሽያጭ ሠራተኞችን ለማነጋገር እድል አግኝቻለሁ የነገሩኝ በጣም አስገርሞኛል፡፡ ሃያ አራት ጠርሙዞችን የሚይዘው የለስላሳ መጠጦች ሳጥን ዋጋ ከፋብሪካው ላይ የሚገዛው አርባ ብር ከስልሣ ሣንቲም ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው አንዱን ጠርሙስ በአንድ ብር ከሰባ አምስት ሣንቲም መግዛታቸውን ነው፡፡ ነጋዴዎቹ ግን አንዱን ሳጥን ለስላሳ በሰባ ብር ያጣሩታል፡፡ ስሌቱ የሚያሳየን እነዚህ ነጋዴዎች ከእያንዳንዱ 32 ብር ያተርፋሉ ማለት ነው፡፡ በጠርሙስ ደረጃ ካሰብነው ከእያንዳንዱ ጠርሙስ አንድ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም ትርፍ ይገኝበታል፡፡ በታሸጉ ውሃዎች ላይም ተመሳሳይ ሂሳብ ይታያል፡፡ ከእያንዳንዱ የታሸገ ውሃ ከአንድ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም በላይ ትርፍ ይገኝበታል፡፡ የለስላሳና የታሸጉ ውሃዎች የሚያመርቱ ኩባንያዎች ደግሞ ምርቶቻቸውን ተሽከርካሪ እያንዳንዱ ነጋዴ ወይም ምርቱን የሚረከብላቸው ደንበኛቸው የሚያደርሱ በመሆኑ አንዳንድ የፋብሪካዎቹ ደንበኞች የትራንስፖርት ወጪ የለባቸውም፡፡ በለስላሳና በታሸጉ ውሃዎች ላይ የሚታየው የትርፍ መጠን ስፋት በመጋነኑ ልንተችበት በቃን እንጂ በሌሎች ምርቶች ተመሳሳይ ድርጊት ይፈፀማል፡፡ የነጋዴዎቹ የትርፍ መጠን ስሌት ከልክ ያለፈ እንደሆነ ከማሳየቱም በላይ አንድ ነጋዴ ትርፍ ብሎ ሲያስብ አንድ ምርት ምን ያህል መጠን ወይም ምን መቶኛ ማትረፍ እንደሚገባው ጠንቅቆ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ የትርፍ መጠኑ ከ10 እስከ 20 በመቶ ካልበለጠ ጤናማ የትርፍ መጠን ተደርጎ ከሃምሳ በመቶ በላይ ትርፍ መጠበቅ ግን ጤናማ አይደለም፡፡ በለስላሳና በታሸጉ ውሃዎች ላይ የሚታየው የትርፍ መጠን ስፋት ደግሞ ከሃምሳ በመቶ በላይም ሥልሳና ሰባ በመቶ መድረሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ ጤነኛ የትርፍ መጠን ነው ተብሎ ከሚጠበቀው በላይ ትርፍ እንዲገኝባቸው የሚፈለጉ ምርቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለረዥም ጊዜ የተቀመጡና መቀመጣቸውም ወጪ የሚያስከትል ሆኖ ከተገኘ ልንቀበለው እንችላለን፡፡ ለስላሳ መጠጥ ግን ገበያ ያለውና ለሳምንታት ሊቀመጥ የማይችል ነው፡፡ ይህንን ያህል ትርፍ እንዲገኝበት ማድረጉ ተገቢ አይሆንም፡፡ ከነጋዴዎቹ ወደ አምራቾቹ ስንመለስ የለስላሳና የታሸጉ ውሃዎች አምራቾች ከሁለት ሳምንታት በፊት ይከፈሉት ከነበረው ኤክሳይስ ታክስ የአስር በመቶ የዋጋ ቅናሽ ተደርጐላቸዋል፡፡ ይህ ቅናሽ ሲደረግ ተጠቃሚው የሚጠብቀው እነዚህ ምርቶች ዋጋቸውን በተወሰነ ደረጃ እንደሚቀንሱ ቢሆንም ፋብሪካዎቹ ቅነሳውን አሜን ከመቀበል ውጭ ምንም ለውጥ አላደረጉም፡፡ ትላልቅ ማምረቻዎች የአስር በመቶ ኤክሳይስ ታክስ ቅናሽ ማግኘታቸው ትልቅ ነገር ቢሆንም ቅናሹ የእነርሱን የትርፍ መጠን ለማሳደግ ብቻ እንዲጠቀሙበት ሳይሆን በቅናሹ ሸማቹንም እንዲያገለግሉበት ጭምር መሆን ነበረበት፡፡ አምራቾቹ የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱን ሊነግሩን ይገባል፡፡ በሌላ በኩልም ምርቶቻቸው በነጋዴዎች እጅ ሲገባ ሰፊ በሆነ ትርፍ እየሸጡ ስለመሆናቸው ከእኛ በላይ ያውቃሉና ይህንን ለመቆጣጠር አስተዋፆ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |