Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ድንበር የጠፋበት ፖለቲካ
ድንበር የጠፋበት ፖለቲካ Print E-mail
Sunday, 20 April 2008
መስፍን ካሳ

ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ሳምንት በተሟገት ገጽ "እያዩ ነው መውደድ እያስተነተኑ. . ". በሚል ርዕስ የኃይሌ ገብረሥላሴ አቋምን የሚፈትንና የሚያንጓጥጥ አድርጌ የቆጠርሁት ጽሁፍ በማንበቤ ነው፡፡ ጽሁፉ (ስም የለውም) አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በቤጅንግ የኦሊምፒክ ውድድር ለመካፈል አለመቻሉን፣ ለመካፈል ያልቻለበትን ምክንያት የገለፀውን ይተቻል፡፡

 

ትችቱ ግን ኃይሌ ባላሰበው መንገድ ዱካውን የሚፈልግ ወይም "ኃይሌ እንዲህ ማለቱ ነው" ከሚል ግምት ተነስቶ ጥያቄውን ፈጥሮ፣ መልሱን ራሱ ሰጥቶ፣ በዚያ ላይ መደምደሚያውን ያንተርሳል፡፡ የኃይሌን የፖለቲካ እውቀት የጠበበ መሆኑን እየጠቀሰ የሚሰራውን የሚያወቅ እንዳልሆነ እየደጋገመ ሲገልጽ፣ ማስረጃ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ረስቶታል፡፡ ያ ጽሁፍ በእነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ የመነመኑ ሃሳቦች ላይ ለመመርኮዝ በመፈለጉ ይደክማል፡፡

ፀሐፊው ለሁሉም ነገር በቂ መረጃ ለማቅረብ አልቻለም፡፡ እንደ መረጃ አድርጎ ሊጠቅሳቸው የሞከራቸው የሆኑና የተደረጉ ሳይሆኑ ልብ ወለድ ሆነው ይታያሉ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ አስተያየቱ የፀሐፊው በመሆኑ በዚያ ረገድ የምናይለት ቢሆንም ነገር ግን ለአንድ ጽሑፍ መስተካከል ዋና ጉዳይ የሆነውን የትክክለኛ መረጃ ስንቅ ባለመያዙ "የተከበረ" ጽሁፍ ለመሆን የሚበቃ አይመስለኝም፡፡ በዝርዝር እንያቸው፡፡
 
አትሌት ኃይሌ፣ በቤጅንግ የማራቶን ውድድር ላለመሳተፍ የወሰነበትን መግለጫ ቅድሚያ የሰጠው ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በመሆኑ፣ ማንም አማርኛ ማንበብ የሚችል ሰው በቀላሉ ሊገባው ይችላል፡፡ በቤጅንግ ለመወዳደር የማይችለውም በዚያች ከተማ ያለው የአየር ብክለት፣ ከራሱ ጤንነትና ልምድ አኳያ ለመሮጥ የሚያስችለው መሆኑን በማያሻማ አቀራረብ ገልጿል፡፡ ራሱ በራሱ እጁን አውጥቶ የሰጠበት ምክንያት፣ ይህና ይኸው ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሌሎች የውጭም ጋዜጠኞች ይሁኑ፣ እንደ ፀሐፊው ያሉ ግለሰቦች፣ የራሳቸውን ፍላጎትና ስሜት እያሸተቱ ተርጉመውትና ጽፈውት ከሆነ፣ የኃይሌ ጥፋትም ሆነ ፍላጎት ነው ሊባል አይችልም፡፡

የዓለም አቀፍ ጋዜጦች እንደራሳቸውና አንዳንድ ጊዜም እንደየ አገሮቻቸው መንግሥታት ፍላጎት፣ የኃይሌን እውቅና ግርማ ሞገስ ተጠቅመው የቻይናን የፖለቲካ አቅጣጫ ጋር ሊያገናኙት መሞከራቸው ታይቷል፡፡ እንደዚህ ያለው ትርጓሜ ግን የራሳቸው ነው፡፡ ፀሐፊው ከኋላ የሚገፉት ኃይሎችና አሜሪካን ለማስደሰት የተወሰደ አቋም ሊያደርጉት ሞክረዋል፡፡ ይህም የራሳቸው ነው፡፡ ኃይሌ ግን በማንኛውም ጊዜ ቻይና እንዲህ ያለውን ስምምነት ስላልፈረመች ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስላለባት አላለም፤ ብቻ ሳይሆን፣ መግለጫው በገደምዳሜም ቢሆን እንዲህ አይነት መንፈስ ያዘለ አይደለም፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው እዚያው ቻይና ሌላው ቦታ ቢሆን እንደሚወዳደር ማስታወቁ ነው፡፡

ቻይና ውስጥ የአየር ብክለት ደረጃ እንደ ቤጅንግ ባልሆነበት ቦታ፣ ለመወዳደር ዝግጁ መሆኑን የገለፀው ሌሎች በራሳቸው ፍላጎት እየለጠጡ፣ ፖለቲካዊ ይዘት ለመስጠት ለሚፈልጉትም ሆነ ብዥታው ላለባቸው ሁሉ ግልጽ ለማድረግ አስቦ ይመስለኛል፡፡ ቻይናን የሚጠላ፣ የኃይሌን አቋም አሜሪካን የሚያስደስት፤ በሚል ግምት ቁጣ ቢያድርበት፣ ወይም የቻይና ፍቅረኛ ቻይናን "ለጠላቶቹ" አሳልፎ እንደሰጣት አድርጎ ቢቆጥረው የራሱ አመለካከት ነው፡፡ ግን የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ከተጨባጩ እውነት ላይ ያልተንተራሰ የስሜት አመለካከት ነው፡፡ ሌላው የተናገረውን ያልሆነ ትርጉም ሰጥቶ መከራከር ደግሞ ዕውቀት ነው ሊባል አይችልም፡፡

ፀሐፊው የማያውቀውን ነገር ሳይመረምር ዘው ብሎ ገብቶበታል፣ እያሉ የኃይሌ አቋም፣ የፖለቲካ አንድምታ ያለው መሆኑን በመግለጽ የሚብከነከኑት የራሳቸው ፍላጎትና ውሳኔ እንጂ ኃይሌ አንዳችም የፖለቲካ ሽታ የሚሸተትበት መግለጫ መስጠቱን አያሳይም፡፡ የተናገረው ስለ ራሱና ስለ ራሱ ሩጫ ብቻ ነው፡፡  ስለ ራሱና ሰለ ሩጫ ለመናገር ከባለቤቱ በላይ ባለቤት መሆኑ ስህተት ይመስለኛል፡፡

 ፀሐፊው፣ ኃይሌ "በየጊዜው የተለዋወጠ መግለጫ መያዙንና እያደር አቋሙ እየተለዋወጠ መምጣቱን እየተለሳለሰና ቀስ እያለም ዝምታ ውስጥ እየገባ መሄዱን" ይገልፃል፡፡

እንዲህ አይነቱ ገለፃና የ"ባወጣ ያውጣው" ግምት ከእውነታው ተስፈንጥሮ ስለሚርቅ፣ በዚያ ላይ የሚሰጠውም አስተያያት የተስፈነጠረ፣ የተዛባ ወይም ዓላማውና ግቡ ሌላውን መጎንተል ማናናቅና ብቻ የሆነ ያስመስለዋል፡፡

ኃይሌ፣ በቤጅንግ ማራቶን ውድድር እንደማይካፈልና የማይካፈልበትንም ምክንያት ከገለፀ ወዲህ አቋም የለዋወጠበት ሁኔታ አልተሰማም፡፡ ፀሐፊው እኛ ያልሰማነውን ሰምተው ከሆነ ከየት እንደሰሙት ቢገልፁልን ሃሳባቸውን በተማማንበት ነበር፡፡ ያልተባለ እንደተባለ አድርጎ፣ የሌላውን ሰው ስም ለማጥፋት የሚያስችል ነው ብሎ መገመት የሚቻል ቢሆንም ግን አንባቢ የሚቀበለውና በጋዜጣ የሚቀርብ ጽሁፍ ሊሆን አይችልም፡፡

አትሌት ኃይሌ አከታትሎ የሰጣቸው መግለጫዎች ሁሉም የሚከተሉት የመጀመሪያውን መግለጫ መንፈስ ሆኖ ከዚያም በላይ ብዥታውን የሚያጠሩ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ስሜት እንደሌለበት፣ ቻይና ውስጥ በሌላ አካባቢ ሊወዳደር እንደሚችል መግለጹ፣ አቋም መለወጥን አያሳይም፡፡ በ10"000 ሜትር ለመወዳደር እንደሚያስብበት መገለጹ፣ ረጅም ርቀትና ጉዞ የሚፈልገውንና የአስም ሕመም ሰሜት ላለው አትሌት፣ አስቸጋሪ እንደሚሆን የሚታመንበትን የማራቶን ሩጫ አልወዳደርም፤ ማለት አቋም መለወጥን አያሳይም፡፡ ኃይሌ ከተናገረው አለመወላወሉ፣ እንዳለ ሆኖ፣ አቋሙን ቢለውጥ እንኳን ድምፁን የሚያጠፋና የሚያለሳልስ ሆኖ ሊታይ አይችልም፡፡ ለእያንዳንዱ ውሳኔ መነሻ የሚሆነው ምክንያት ከተለወጠ አቋም መለዋወጥ የሚደገፍ እንጂ የሚነቀፍ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ ጽሁፉ የኃይሌን ስብዕና ለማንኳሰስ ታስቦ የተደረገ የሚያስመስለው "ዝምታው፣ ማቀርቀሩና መለሳለሱ የመጣው፣ ጥበብና ብልሃት የሌለው ዘዴ መከተሉ፣ የማያዋጣውን "ጣጣ" እንደገባበት አድርጎ በፃፈባቸው ቃላት ሊገመት ይችላል፡፡ መቼም ማንም እንደሚያውቀው እንደ ኃይሌ ያሉ የተከበሩ የውጭ መገናኛ ብዙሃን፣ አነፍንፈው ደጅ ጠንተው ሲያገኙት ለሚያቀርቡለት ጥያቄዎች የሚሰጣቸው መልሶች፣ በማያውቀው ነገር ጠልቆ የሚገባ መሆኑን አያመለክቱም፡፡ ይህንን እንተወው ቢባል እንኳ መግለጫ ለሚዲያ የሚሰጠው አንድ ጊዜ ብቻ እንጂ በየቀኑ ሲተነትን አይዋልም፡፡ ስለዚህ ድምፁ የጠፋው በማያውቀው ነገር ስለገባ ነው ሊባል አይችልም፡፡
 
መግለጫውን ከሰጡ በኋላ የመድገም የመደጋገም ጉዳይ የሚዲያው ነው፡፡ ለነገሩ ኃይሌ አቋሙን የሚወስደው መሮጥ ስላልቻለ እንጂ ሚዲያው ደጋግሞ ያወራልኛል ብሎ አይመስለኝም፡፡

ፀሐፊው የኃይሌን ፖለቲካ ውስጥ መግባት መብት መሆኑን ይጠቅስና "ይህን ሊያደርግ በእውቀት ላይ ተመስርቶ ግራ ቀኙን አይቶ. . ". መሆን እንዳለበት ያትታል፡፡ ክብርና ዝና ያላቸው ሰዎች ካጠፉ አይተቹም አይባልም፡፡ ነገር ግን "ያለ ሥራቸውና ኃጢአታቸው" መተቸት የዚያኑ ያህል የሚያስነቅፍ ይመስለኛል፡፡ ፀሐፊው የኃይሌን የፖለቲካ እውቀትም ሆነ ተሳትፎ አውቃለሁ ባይ ከሆኑ ከፍ ብዬ እንደገለፅኩት ማስረጃውን ቢያስደግፉልን ባመሰገናቸው ነበር፡፡ ካላወቁ ግን ሌላውን አያውቅም፤ ብሎ የጋዜጣ ጽሑፍ ማሳተም የሰው ክብር መንካት ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
 
እኛ እስከሚገባን ድረስ ኃይሌ በውጭ ቋንቋ ጭምር የሚሰጣቸው ቃለ ምልልሶች፣ በአገሩ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ (እስረኞችን በማስፈታት ምልጃ ብቻ አይደለም) አይተናል፡፡ የዚህ ተሳትፎ በቂ ነው ካልተባለም በዕውቀት ላይ ያልተመሰረተ ነው ሊያስብለው አይገባም፡፡

ፀሐፊው ኃይሌን ሊያናንቀው የሚሞክረው፣ ያንን ያህል በዓለም የተከበረ ታዋቂ አትሌት በጤና ምክንያት በማራቶን ውድድር አልሳተፍም፤ ለማለት የበቃው፣ ከኋላ የሚገፋው ኃይል እንዳለ አድርጎ በማቅረብ ነው፡፡ ኃይሌ ጉልበቱንና አቅሙን እንደማያውቅ አድርጎ በመገመት የሌላ ኃይል ፍላጎት አስፈፃሚ አድርጎ ማቅረብና ለማጣጣል መሞከር፣ ሆን ተብሎ ፣የማጥቃት፣ ሥራ ሆኖ ይታያል፡፡ ለመሆኑ "ኃይሌን ተጨማሪ ኃይልና ጉልበት እንሰጥሃለን" የሚሉት የአገር ቤት ሰዎች እነማን ይሆኑ? ይህንንም ፀሐፊው ምናልባት ስለማያውቁት ሊገልፁልን አልቻሉም፡፡ ጉዳዩም አሉባልታ ስለሚሆን እየቀለለና እየወረደ ይሄዳል፡፡

ፀሐፊው የአሜሪካ ጥላቻቸውን ለመግለጽና ለመውቀስ፣ ኃይሌንም እነ አሜሪካን ደስ የሚያሰኝ ርምጃ ወሰደ፤ በሚል ስሌት እንደተናደዱበት ጽሁፋቸው ይጠቁማል፡፡ ይህም ቢሆን የተሳሳተ ስሌት ይመስለኛል፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት የአየር ብክለትን ማንሳት አዲስ ነገር ሳይሆን አሜሪካ በሚመራው "ጉዳይ ላይ በመመስረት ነው"፡፡ ይህን እንዴት እንደገጣጠሙት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ጤንነቱና አቅሙን የሚያውቀው ኃይሌ ሆኖ ሳለ፤ ገና ለገና አሜሪካ ልትደሰትበት የምትችለው አቋም በመሆኑ፣ የአሜሪካ "ጠላቶች ይጠሉኛል" ብሎ አቋሙን ከመግለጽ ማፈግፈግ አለበት፤ ብሎ መናገር አግባብ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ድፍረትም ነው፡፡

ኃይሌ በአየር ብክለት ምክንያት አልወዳደርም፤ ቢል "ጥቅም ያወራቸውን አድናቂዎች" እንደተከተለ አድርጎ መተርጎም ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡ በቻይና በሚደረግ ውድድር አለመወዳደር የሚፈልግ አትሌት፣ ገና ለገና አሜሪካን የሚያስደስት ውሳኔ ስለሚሆን፣ ሙጋቤ ወይም ቢንላደን፣ ቻይና ወይም ሐማስ፣ ካስትሮ ወይም ቻቬዝ ይቃወሙኛል፤ ብሎ ማሰብ የለበትም፡፡ ባለማሰቡም Wisdom የለውም ሊያስብለው የሚገባ አይመስለኝም፡፡

የኃይሌን አቋም የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ወይም የአትሌቲክ ፌዴሬሽን ቢቃወመው፣ እንደ ግለሰብነቱ፣ እንደ እጅግ ከፍ ያለ እውቅና ያለው አትሌትነቱ፣ የያዘው አቋም እንደሚከበር የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ይፋ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ታዋቂ አትሌቶች የሚናገሩትን እንደ ፀሐፊው ወይም እንደ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች ወደ አንድ ጥግ ሊያስይዙት መሞከር፣ ነገሩን ያለመገንዘብ ችግር ሳይሆን የቡድነኝነት ስሜታቸው ስላየለባቸው ይመስለኛል፡፡

ኃይሌ አሜሪካን ለማስደሰት፣ ቻይናን ለማስቀየም የያዘው አቋም የለም፡፡ በፖለተካም ምክንያት መሆኑን የሚያሳይ ፍንጭ አልሰጠም፡፡ ግን ሁሉም በየራሱ ስሜት ከተረጎመ ችግሩ የራሱ ነው፡፡

የኃይሌን አቋም ምናልባትም የኢትዮጵያ መንግሥትም አይወድለት ይሆናል፡፡ ከቻይና ጋር ባለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ትብብር ምክንያት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የቻይና ሸሪካ እንደመሆኑ የኃይሌን አቋም በተጽዕኖም ለማስለወጥ ይሞክር ይሆናል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች የሌሎችን አቋም ማክበር እንደ መንግሥትነታቸውም ከማስከበር ይልቅ በእነሱ ፍላጎት ብቻ እንዲፈጸም ይፈልጋሉ፡፡

የቻይና መንግሥት በአዲስ አበባ ያለውን አምባሳደሩን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን እንዲያነጋግር እንደሚልከው መገመት ይቻላል፡፡ አቶ መለስ ያሉትን መገመት አልችልም፡፡ ቅር ብሏቸው ከሆነና ተጽዕኖ አደርጋለሁ፤ ካሉ ግን ስህተተኛ ይሆናሉ፡፡ ይሄ መቼም የእኔ ግምት ሲሆን ግምቴም የሚነሳው የዲፕሎማሲን ሥራ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የኃይሌ የግለሰብ አቋም መከበር አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከፈለገውና ካሰበው ውጭ ከሆንክ፣ ውጉዝ ሁን ለማለት፣ ማንም መብት የለውም፡፡

ፀሐፊውም በኃይሌ ላይ ከመስመር ወጥተው ያላለውን ፈጥረው፣ ያላሰበውን ፖለቲካ ቀርፀው፣ መኮነናቸው፣ ለዚያ ሁሉ ትንኮሳቸውም መረጃ አለማቅረባቸው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አስተያየት መሆኑን እንዴት ሊያሳይ ይችላል?

 
< Prev   Next >