|
Sunday, 20 April 2008 |
|
"መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ የሴቱን አናውቅም አንድ ሰው ሞተ"
በወርሀ ሚያዚያ 1860 ዓ.ም ታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ የተሰውበት ዕለት "ሽጉጣቸውን አጉርሰው ራሳቸው የጎረሱበት ክስተት፡፡ የዘመኑን ትንሣኤ በዓል አክብረው በማግሥቱ የማዕዶት ዕለት ያለፉበት፡፡"
ይህን ታሪካዊ ክስተትና ላገሪቱ የሰጡትን አገልግሎት የሚዳስስ አዲስ ቴአትር ባለፈው ማክሰኞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተመርቋል፡፡ "የቴዎድሮስ አርአያ" በሚል ርእስ ተውኔቱን የደረሰው ጸሐፌ ተውኔት ጌትነት እንየው ሲሆን፣ በተዋናይነት የተሳተፉት ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አርቲስቶች ናቸው፡፡ በክልሉ ባህል ቢሮ አስተባባሪነት የተዘጋጀው ተውኔት ከአዲስ አበባ ሌላ በተለያዩ ከተሞች ለተመልካች እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡
በዕለቱ የምረቃ መሰናዶ የአማራ ክልል መንግሥት ለተውኔቱ ደራሲ ለጥበባት ላደረገው አስተዋጽኦ በባሕር ዳር ከተማ 500 ካሬ ሜትር መሬት በሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
* * *
"ጥይት ስለ ውሃ ማነው የሚጠጣ? ቴዎድሮስ ብቻ ነው ጥሙን የሚወጣ፣"
የመጨረሻው የመቅደላ ግብግብ ሰኞ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ወደ ማቆሙ ተቃረበ፡፡ በጄኔራል ናፒር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ቴዎድሮስን አድኖ ለመያዝ በየአቅጣጫው መሯሯጥ ጀመረ፡፡ ግርማ ኪዳኔ እንዳተቱት የቴዎድሮስን ሁኔታ አስመልክቶ የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርተር እስታንሊ ሲናገር ሰኞ ከቀኑ አሥር ሰዓት አካባቢ እንግሊዝ በመቅደላ ላይ ካሰማራቻቸው ወታደሮች መካከል ሁለት የአየርላንድ ወታደሮች የተኩስ ድምፅ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተክለፈለፉ እንደደረሱ አንድ ያልታወቀ ኢትዮጵያዊ ከመሬት ላይ ተዘርሮ ለመሞት በማጣጣር ላይ እንዳለ ያገኙታል፡፡
እነሱ ወዲያው አላወቁትም እንጂ ግለሰቡ ተራ አይደለም፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ ዳግማዊ ናቸው፡፡ አፄ ቴዎድሮስን በሕይወት ሳሉ የሚያውቃቸው ራሳም መጥቶ እሳቸው ስለመሆናቸው እንዲያረጋግጥ ተደረገ፡፡ እየሮጠ መጥቶ ሲያያቸው አፄው ሆነው አገኛቸው፡፡ በእርሱና በንጉሡ መካከል አልፎ አልፎ አለመግባባት ቢፈጠርም ቆራጥ መሪ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ሁኔታውን እንደተመለከተ መንፈሱ ተረበሸ፡፡ በተለይም ከመሞታቸው በፊት የተናገሩት ቃል ትዝ አለው፡፡ ይኸውም "አንድ ቀን እኔ ስሞት ታየኝ ይሆናል፤ ከዚያም በሬሳዬ ላይ ቆመህ ይህን ደካማ ሰው በመቅበር ፋንታ ከሜዳው ላይ እንደ ወደቀ በስብሶ መቅረት አለበት በማለት ትረግመኝ ይሆናል" ብለው የተናገሩት ትዝ እያለው በሐዘን ተውጦ ይታይ ነበር፡፡ በወቅቱ የዓይን ምስክር በመሆን ያረጋገጠው አሜሪካዊ ሪፖርተር ሕይወታቸው ስላለፈችው የመቅደላ ጀግና ሲያብራራ "የተለየ ክብር ሳይደረግላቸው፣ ጠባቂ ዘብ በአጠገባቸው ሳይቆም፣ በቃሬዛ ላይ ለብዙ ሰዓት ያህል ከመሬት ተዘርረው ፀጉራቸው ተሸልቶ፣ ልብሳቸው ተገፍፎና ተቀዳዶ ከፊል እርቃነ ሥጋቸው በማየቴ የቀድሞው ቴዎድሮስ መሆናቸው አጠራጠረኝ" ይልና፣ "ራቅ ብዬ ስመለከት ብዙ መኰንኖች በደም የተበከለውን የቴዎድሮስን ሸሚዝ ለእኔ ይገባኛል በማለት ሲጓተቱና ሲጣሉ ተመልክቼ ነበር" ብሏል፡፡
እንደ ግርማ ኪዳኔ ማብራሪያ ቴዎድሮስ ሲነግሱ ለብሰውት የነበረው የክብር ልብስና በአንፃሩ ደግሞ ከሞቱ በኋላ የተወሰደባቸው በደም የተበከለችው ሸሚዝ በእንግሊዝ ሰሜናዊ ክፍል ባንክ ፊልድ ሙዚየም ሀሊፋክስ ዩክሼር ተብሎ በሚጠራው መዘክር፣ የተሸለተው ጸጉራቸው ግን በለንደን ከተማ ናሽናል ዎር ሙዚየም ውስጥ እንግሊዞች አስቀምጠውታል፡፡
አባ ታጠቅ ካሳ ተብለው የሚታወቁት አፄ ቴዎድሮስ በተለያዩ የጥበባት ዘርፎች ለባለሙያዎች ርእሰ ጉዳይ በመሆን ይወሳሉ፡፡ በልብ ወለድ "የቴዎድሮስ እንባ" እና "የታንጉት ምስጢር" ድርሰቶችን በተለያዩ ዘመኖች የጻፈው ብርሃኑ ዘሪሁን ይጠቀሳል፡፡ ደራሲ ብርሃኑ በ1958 ዓ.ም "የቴዎድሮስ እንባ"ን፣ ካሳተመ በኋላ እንደገና ልብ ወለዱን ከልሶና አስፋፍቶ በመጻፍ በ1979 ዓ.ም "የታንጉት ምስጢር"ን አውጥቷል፡፡ ቴዎድሮስ ለታሪካዊ ልብ ወለድ መነሻ ከሆናቸው ደራስያን አንዱ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነማርያም በ"አፍሪካን ራይቲንግ ሲርየስ" ውስጥ የተመዘገበላቸው "ዘ ዋርየር ኪንግ" ይታወቃል፡፡ በተውኔት ረገድ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት የደረሱት "ቴዎድሮስ"፣ የጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረመድኅን "ቴዎድሮስ" ተውኔትና "የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ" ግጥም ይጠቀሳል፡፡
"ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም፣ ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም" የሚለው የበገና መዝሙር ንጉሠ ነገሥቱ ኢየሩሳሌምን ከቱርክ ቀንበር ነፃ አወጣለሁ ይሉ ነበር የሚለውን አስተሳሰብ በበገና ደርዳሪዎች እስካሁን ድረስ የሚቀነቀን ነው፡፡ አማርኛ ከግእዝ ይልቅ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ እንዲሆን ይጥሩ እንደነበር ታሪካቸው ከግእዝ ይልቅ በአማርኛ እንዲጻፍ ያስደረጉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የአማርኛ ትርጉም ለኅብረተሰቡ እንዲሰራጭ በማድረግ "ይጠቀሳሉ፡፡
የቴዎድሮስ ጀግንነት በሳይንስና ጥበብ ውስጥ ልዩ ስፍራ እንደሚይዝ የሰባስቶፖል መድፍ ሥራ ውጥን አንዱ መሆኑና በዘመናችን "ጋፋት ኢንጂነሪንግ" ለሚለው ስያሜ ንቡር ተጠቃሽ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡
የሥነ ጥበብ ሐያሲ የነበረው ሥዩም ወልዴ ቴዎድሮስን ባህላዊ ጀግና የሚል መጠርያ ሰጥቶታል፡፡ የቴዎድሮስ ባህላዊ ጀግንነት ሰፋ ባለ መልኩ የሚታይና በሕዝባዊ ግጥሞች፣ በዘፈኖች፣ በተውኔቶች፣ በልብ ወለዶች፣ በግጥሞች በቅርጻ ቅርጾች በሥዕሎችና በጥበባት ዕድ ሥራዎች ውስጥ ጎልቶ ገጽታው ይታያል፡፡
በቴዎድሮስ ዙሪያ በርካታ ትውፊታዊና ዘመናዊ ሥዕሎች በተለያዩ ጥበባውያን ተሥለዋል፡፡ የቴዎድሮስ ምስል ከእውነታው ተገልብጦ መሳሉ ይነገራል፡፡ አንድ እንግሊዛዊ መኰንን በሠራቸው በርካታ ንድፎች በአንዳንዶቹ የቴዎድሮስ ገጽታ የሚታይባቸው ሲሆኑ በሌሎቹ የመቅደላ ተራራና የሴባስቶፖል መድፍ በብዙ ሕዝብ ሲጎተት የሚታይባቸው ናቸው፡፡
ሥዩም እንደሚተነትነው በጊዮም ለዣን ከታተመው ጉርድ ምስል ሌላ ሁለተኛ ጉርድ ምስል ይገኛል፡፡ በተለይ ደራሲው ግርማቸው ተክለሐዋርያት "ቴዎድሮስ" የተሰኘው ተውኔት በመጽሐፍነት ታትሞ በወጣ ጊዜ የመጽሐፉ ሽፋን በመሆኑ በሀገር ውስጥ ሊታወቅ ቻለ እንጂ ከዚያ በፊት የሚታወቅ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡
ሁለቱ ጉርድ ምስሎች በኤትሞግራፊያዊ ይዘቶቻችው፣ በፀጉር አሠራር ፈሊጥና በአለባበሳቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ በጊዮም የታተመው ጉርድ ምስል ለአብዛኞቻችን የቴዎድሮስና የዮሐንስ መታወቂያ የሆነው የፀጉር አሠራር ፈሊጥ (ባለሹሩባው) ሲሆን ሁለተኛው ጉርድ ምስል ግን ወደ ኋላ የተሰበሰበ ጎፈሬ የሚታይበት ምስል ነው፡፡ በሔኖክ ያሬድ |