| ባንኩ የቀረበለትን ተጨማሪ... |
|
|
| Sunday, 20 April 2008 | |
|
ባንኩ የቀረበለትን ተጨማሪ የበጀት ጥያቄ ሳይቀበለው ቀረ
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለሁለት ፕሮጀክቶች ጥናት ማስፈፀሚያ ከኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበለትን ተጨማሪ የበጀት ጥያቄ ሳይቀበለው ቀረ፡፡ የውሃ ሀብት ሚኒስትር የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው የአፍሪካ ልማት ባንክ የከለከለው ተጨማሪ በጀት ለገናሌ መስኖ ልማትና ለነገሌ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ጥናት ማካሄጃ ነበር፡፡ የገናሌ ዳዋ ወንዝ ተፋሰስ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት የሆኑትን ለነዚህ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ጥናት የሚያስፈልገው ተጨማሪ በጀት በባንኩ በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱም ዝርዝር ጥናቱን ሲያካሂድ የነበረው አማካሪ ድርጅት ሥራውን በማቋረጡ ሥራው በእቅዱ መሠረት ሊከናወን አልቻለም፡፡ የተጠየቀው ተጨማሪ በጀት ባለመፈቀዱ የተፈጠረውን የሥራ መስተጓጎል በጋራ ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና አማካሪ ድርጅቱ ባደረጉት መግባባት፣ የሚያስፈልገው ተጨማሪ በጀት ከመንግሥት ለመመደብ ስምምነት ላይ በመደረሱ አማካሪ ድርጅቱ ከረዥም ጊዜ በኋላ እንዲመለስ መደረጉን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በዚሁ ስምምነት መሠረት በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ቀሪውን የዝርዝር ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው በበጀት ዓመቱ የሚያካሄዳቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ ካልቻለባቸው ምክንያቶች ውስጥ የውጭ እርዳታና ብድር ፋይናንስ ፍሠቱ አሁንም ከችግር ያልተላቀቀ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የሥራ ተቋራጮችና አማካሪ ድርጅቶች አቅም ውስንነት፣ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናር፣ የሲሚንቶና የግንባታ ብረት አቅርቦት በሚፈለገው መጠን በገበያ ላይ ባለመገኘቱ የተነሳ በግንባታ ፕሮጀክቶች የሥራ ሂደት ላይ መጓተት የጂኦ ቴክኒካል የሚያካሄዱ የአማካሪ ድርጅቶች ብዛት ውስን መሆንና ያሉትም አቅማቸው ያልተጠናከረ መሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያቀረባቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን በውሃ ነክ ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ለ96 ድርጅቶች፣ ለ15 አማካሪ ድርጅቶችና ለ675 ባለሙያዎች በድምሩ ለ786 ፈቃድ ጠያቂዎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ለ12 ድርጅቶችና ለ54 ባለሙያዎች በድምሩ ለ66 የውሀ ጉድጓድ ቁፋሮና ጠረጋ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መስጠቱንም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |