Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ስኬት
ስኬት Print E-mail
Sunday, 20 April 2008
Image
ሲ/ር ደብሪቱ አማረ
የልጅነት ህልማቸው ነርስ መሆን እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ለህክምና ሙያ ከነበራቸው ፍቅር የተነሳ የወጣቶች ቀይ መስቀል አባል ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡ በቀይ መስቀል አባል በነበሩበት ወቅት ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ከመስጠትና ከመንከባከብ ያለፈ ለሙያው የሚያቀርብ ሥራ ያልነበረ ቢሆንም ያስደስታቸው ነበር፡፡ ሲ/ር ደብሪቱ አማረ ዲግሪያቸውን ይዘው በጉለሌ ጤና ጣቢያ የእናቶችና ህፃናት ሕክምና ክፍል አስተባባሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ እዚህ ደረጃ የደረሱት ከጤና ጣቢያ ደረጃ የካርድ መዝጋቢ ሆነው በመጀመር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

 

"በ1967 አካባቢ በሃገራችን በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በተማሪዎች በኩልም መረጋጋት አልነበረም፡፡ በ1968 የ11ኛ ክፍል ተማሪ ብሆንም ለትምህርት የሚመች ሁኔታ ባለመኖሩ ትምህርቴን አቋርጬ ነበር" ይላሉ፡፡

በወቅቱ በጉለሌ ጤና ጣቢያ ሥራውን የሚያካሂደው በኢትዮ ሲዊዲሽና በማዘጋጃ ቤት ትብብር ነበር፡፡ ጤና ጣቢያው "ረዳት አዋላጆችን እንፈልጋለን" የሚል ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ሲስተር ደብሪቱ ያኔ የ16 ዓመት ልጅና የ11ኛ ክፍል ተማሪ ቢሆኑም እድሜያቸውን 18 ብለው ለሥራው ውድድር ተመዘገቡ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በወቅቱ ረዳት አዋላጅ ማለት ምንም የሙያ ሥልጠና ያልተሰጠው ግን ለአዋላጅ ነርሶቹ እቃ በማቅረብና ሙያዊ ያልሆኑ ሥራዎችን በማገዝ የሚሰራ ነው፡፡ ህልማቸው ነርስ መሆን ነበርና አጋጣሚውን ተጠቀሙበት፡፡ በወድድሩ አሸንፈው አሁን በኃላፊነት እየሰሩ ባሉበት ጤና ጣቢያ በረዳት አዋላጅነት በ7ዐ ብር ደመወዝ (በ1969 ዓ.ም". ተቀጠሩ፡፡ በውስጣቸው አንድ ቀን እቃ እንደሚያቀርቡላቸው ሙያውን የተማሩ ነርሶች እንደሚሆኑ እያለሙ ያቋረጡትን ትምህርት ለማጠናቀቅ በማታው ኘሮግራም 11ኛ ክፍል ገብተው መማር ጀመሩ፡፡ ቀን ይሰራሉ ማታ ይማራሉ፡፡

በወቅቱ በረዳት አዋላጅነት ሲሰሩ ምንም ሙያዊ ስልጠና ያልተሰጣቸው ቢሆንም የሚያግዟቸው ነርሶች የሚያደርጉትን በማየትና በመጠየቅ ልምድ አካብተዋል፡፡ በመሆኑም እቃ ከማቀራረብ አልፈው የሚያዋልዱበት ወቅት ነበረ፡፡ "ሙያዊ ስልጠና ባይሰጠኝም የልምድ አዋላጆች እንደሚያዋልዱት ሀኪም ቤት ውስጥ ንፅህናው በተጠበቀ መልኩ በልምድ የማዋለድ ሥራ እንሰራ ነበር" ይላሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ በውስጥ እድገት የካርድ መዝጋቢነት ሥራን አገኙ፡፡ እድገቱ እውን ለማድረግ አንድ እርምጃ እንደሆነ አሰቡ፡፡ ነርስ የመሆን ህልማቸውን በ1970 ዓ.ም. 12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን የወሰዱ ቢሆንም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት አልነበራቸውም፡፡ በተቀጠሩበት ሥራ ቀጠሉ፡፡ ይሁንና በየዓመቱ ጤና ጥበቃ በሚያወጣው የነርስነት ሥልጠና ውድድር ይከታተላሉ ነበር፡፡ የተሳካላቸው በ1974 ዓ.ም. ነበር፡፡ የ12ኛ ክፍል ውጤታቸውና የሥራ ልምዳቸውም ተደማምሮ አብረዋቸው የተወዳደሩትን አሸንፈው ለነርስነት የመሰልጠን እድል አግኝተዋል፡፡ ለሁለት ዓመት ያህል ደሞዛቸውን ለቀው ነርሲንግ ትምህርት ቤት በመግባት የልጅነት ህልማቸው የነበረውን ሙያ በእጃቸው አደረጉ፡፡

ጤና ጣቢያ ውስጥ በረዳትነት በመቀጠር ህልማቸውን ለማሳካት ደፋ ቀና ማለት የጀመሩት ሲስተር ዘውዲቱ ከስምንት ዓመት በኋላ በ1976 ዓ.ም. ሃሳባቸው ሞላ፡፡ አጠቃላይ የነርስነት ሥልጠና ወስደው ተመረቁ፡፡ "ያኔ በእጣ ነበር የሥራ ምደባ፡፡ የመጨረሻውን የመስክ ሥራ ሰርቼ ስመለስ የምድባችን እጣ ወጥቶ ነበር፡፡ ኤርትራ እንደደረሰኝ አወቅሁ፡፡ ሻንጣዬን ጠቅልዬ ቤተሰቦቼን ተሰናብቼ ለመጀመሪያ ጊዜ የምወደው ሙያ ባለቤት ሆኜ ነጭ ጋዋን ለብሼ ለመሥራት ወደ ኤርትራ ተጓዝኩ"

ከወላጅ መራቃቸው ግን እረፍት አልሰጣቸውም፡፡ የቤቱ ትልቅ ሴት ልጅ ነበሩና ቤተሰብ የመንከባከብ ኃላፊነት ነበረባቸው፡፡ አባታቸው ቤተሰቡን የመንከባከብ አቅም አልነበራቸውም፡፡ እንዲያውም ሲስተር እንደሚሉት አባታቸው ሽማግሌ ነበሩና እንክብካቤ ይፈልጉ ነበር፡፡ በመሆኑም እቤት ወስጥ የነበሩ ትንንሽ ልጆችንና አባታቸውን የመንከባከቡን ኃላፊነት ለመወጣት ወደ አዲስ አበባ መመለስ ነበረባቸው፡፡

"ከሁለት ዓመት በኋላ በብዙ ውጣ ውረድ ወደ አዲስ አበባ ተዛወርኩ፡፡ ገና መጀመሪያ ወደ ነርስነት ሳኮበኩብ በረዳትነትና በካርድ መዝጋቢነት ተቀጥሬ እሰራበት ወደነበረው ጉለሌ ጤና ጣቢያ ተመልሼ ማገልገል ጀመርኩ"

በፊት በውስጣቸው አንድ ቀን ነርስ የመሆን ራዕያቸው እንደሚሳካ ተስፋ እያደረጉ ለነርሶች እቃ ባቀበሉበት፣ በካርድ መዝጋቢነት በሰሩበት ጤና ጣቢያ ነርስ ሆነው ለማገልገል ቻሉ፡፡ ህልማቸውን ለማሳካት ዓመታትን ቢፈጁም በመጨረሻ ነጭ ጋዋናቸውን አጥልቀው በሽተኛ ለመመርመር በቁ፡፡

ሲስተር ዘውዲቱ አሁንም የመማርና በሙያው የማደረግ ህልማቸው አልቆመም፡፡ በ1983 ዓ.ም. የአዋላጅ ነርስነት ስልጠና እድል አገኙና ሰለጠኑ፡፡ ከጠቅላላ ነርስነት ወደ አዋላጅ ነርስነት ተሸጋገሩ፡፡ ያስተማራቸው መንግሥት ስለነበረ ይሰሩበት ወደነበረው ጉለሌ ጤና ጣቢያ ተመልሰው በአዋላጅ ነርስነት ማገልገል ጀምረዋል፡፡

በአዋላጅ ነርስነት ሙያቸው የሁለት ዓመት ትምህርት አግኝተው በ1999 ዓ.ም. ዲግሪያቸውን ለመያዝ በቅተዋል፡፡ አሁን ለ30 ዓመት ያህል ባገለገሉበት ጤና ጣቢያ የእናቶችና ህፃናት ክፍል ኃላፊ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የህክምና ሙያን ፈልገውና አልመውት የገቡበት እንዲሁም በፍቅር የሚሰሩት ሙያ ቢሆንም አንዳንዴ የሚገጥሟቸው ነገሮች "ለምን ነርስ ሆንኩ?" ያሉባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ከብዙዎቹ መካከል እንደዛ እንዲሉ ያደርጋቸውን የአንድ ቀን ገጠመኝ አጫውተውኛል፡፡

"የነርስነት ሙያ ሰልጥኜ ከተመለስኩ በኋላ ነው፡፡ አንዲት እናት ምጥ ይዟት መጣች፡፡ በጣም ትጮሃለች፣ ትረብሻለች፡፡ አልጋ ላይ መተኛት አልቻለችም፡፡ በጣም ትወራጫለች፡፡ ከአልጋ ላይ እንዳትወድቅብኝ ፈራሁና መሬት ላይ አንጥፌ አስተኛኋት፡፡ ሴትየዋ የምትመክሪያትን አትሰማም፤ ህመሟን ብቻ እያዳመጠች ትወራጫለች፡፡ ይባስ ብሎ ምጡ ተፋፍሞ የልጁ ጭንቅላት እየታየ ተነስታ ትሯሯጣለች፡፡ የማዋለጃ ክፍሉን ለቃ ወጣች፡፡ የግቢው ሰራተኞች ሁሉ ወጥተው ተባበሩኝ፤ ግን አልቻልናትም፡፡ በግድ ይዘን ማስተኛት አቃተን፡፡ በመጨረሻም በስንት ሰው ትግል ተይዛ ተኝታ እግሮቿ ተይዘው ወለደች፡፡ ያን እለት በጣም አልቅሻለሁ፡፡ ለምን ወደዚህ ሙያ ገባሁ? ብዬም ተፀፅቻለሁ"

በአዋላጅነት ከሰሩበት እድሜ አንዴ ብቻ በህይወት የሌለው ልጅ አዋልደዋል፡፡ አጋጣሚው የተፈጠረው እናትየው ለረዥም ጊዜ በማማጧ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ "ደክማ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ልጇ ሲወጣ እትብቱ እላዩ ላይ ተጠምጥሞ በጣም አጥብቆት ነበር፡፡ ያኔ በህይወቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡ የጠፋ ልጅ ማዋለድ በጣም ያሳዝናል፡፡ የእናትየው ልፋትና ሃዘንም ያሳዝንሻል" ይላሉ፡፡

አንዲት አዋላጅ ነርስ ምጥ ከያዛት ሴት ጋር ሁሉ አብራ እንደምታምጥ የሚናገሩት ሲስተር ዘውዲቱ ከእያንዳንዷ ሴት ጋር አብረው ሲያምጡና ሲጨነቁ እንደሚውሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ሙያው በጥረት የተሳካ የልጅነት ህልማቸው ነውና በጭንቀታቸው ውስጥም እርካታ ይሰማቸዋል፡፡ የማዋለድ ሥራቸውን ጨርሰው እናት ልጇን ስታቅፍ ሲያዩ ደስታቸው የላቀ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

 
< Prev   Next >