| የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች... |
|
|
| Sunday, 20 April 2008 | |
|
የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር አመራሮቹን በአዲስ ተካ
- ለመንግሥት ያቀረባቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች መልስ አላገኙም የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ለ14 አመታት በአመራርነት ሲሰሩ የቆዩትና ሌሎች ስድስት የሥራ አስፈፃሚዎች በአዲስ ተተኩ፡፡ ማኅበሩ አባላቱን ለማበራከት አለመቻሉና ለመንግሥት ያቀረባቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች እስካሁን መልስ አለማግኘታቸው ተገለፀ፡፡ ማኅበሩ ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ባካሄደው አመታዊ ስብሰባና ምርጫ ማህበሩን ለተከታዩ ሦስት አመታት የሚመሩትን ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መርጧል፡፡ ከዘጠኙ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መካከል ሰባቱ አዳዲስ ሲሆኑ ሁለቱ በቀድሞ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ሲሠሩ የቆዩ ናቸው፡፡ በምርጫው መሠረትም ማህበሩ ከተቋቋመበት 1984 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ አስፈፃሚነት በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት ኮሎኔል እምላሉ ወረደ በአዲስ እንዲተኩ ተደርጓል፡፡ ኢንጂነር እምላሉን ወረደን እንዲተኩ የተደረጉት አቶ ደምሰው አባተ (ኢኳቶር ኢንጂነሪንግ) ሲሆኑ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጡት ደግሞ የፊሊንስቶን ኤንጂነሪንግ ባለቤት አቶ ፀደቀ ይሁኔ ናቸው፡፡ እስከ ምርጫው እለት ድረስ የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት የበርታ ኮንስትራክሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢንጅነር ብርሃኔ አባተ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በአዲሱ የሥራ አስፈፃሚ ውስጥ የተካተቱት አቶ ሲሳይ ደስታ፣ አቶ በቀለ ምንዳ፣ አቶ ዋሴ፣ አቶ አብርሃም ደምሴ፣ አቶ መለሠ ጌታቸው፣ አቶ ካሱ ገብረፃዲቅና አቶ ግርማ ኃይለማሪያም ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር አባላት መካከል ተፈጥሮ በነበረ አለመግባባት በማህበሩ ውስጥ አባል ሆነው የቆዩ አንዳንድ የደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ማህበሩን ለቀው የራሳቸው የሆነውን የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ማህበር አቋቁመዋል፡፡ ማህበሩ እንዳይከፋፈል በማህበሩና ተገንጥለው የራሳቸው ማህበር ያቋቋሙት ኮንትራክተሮችን ለማስማማትና በአንድ ማህበር ጥላ ሥር ሆነው እንዲሠሩ ለማድረግ የተሞከሩ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በርካታ የደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች አዲስ ወደተቋቋመው ማህበር የሄዱ ሲሆን አንዳንድ የደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ግን አሁንም በቀድሞ ማህበር ውስጥ እንዳሉ ታውቋል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በተደረገው የማህበሩ ስብሰባ ላይ ኮሎኔል እምላሉ ወረደ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደገለፁት፣ የማበራከት ሥራ አልተሰራም፡ “አዳዲስ አባላት እንደጠበቀው ወደ ማህበሩ አልገቡም፡፡ ነባሮቹም አመታዊ ክፍያቸውን ፈፅሞ በወቅቱ አይከፍሉም” ያሉት ኮሎኔል እምላሉ በዚህ ምክንያት የማህበሩ ጽ/ቤትም ሆነ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን ለመስራት ገንዘብ አስፈላጊ በመሆኑ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ተካሂዶ 288ሺህ 382 ገቢ ለማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ማህበሩ ከሰራቸው ሥራዎች ውስጥ በአቅም ግንባታ ሚኒስቴርና በጂቲዜድ በሚገነቡ የ13 ዩኒቨርስቲ ግንባታዎች ከደረጃ 1-3 ብቻ የነበረውን እንዲሻሻልና ደረጃ አራት ኮንትራክተሮችንም እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ በአገሪቱ ውስጥ የሽርክና (Joint Venter) አሠራር በግልፅ የተቀመጠ ባለመሆኑ ኮንትራክተሩ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ባለሃብት ጋር በሽርክና ሊያሠራ አዋጅ እንዲወጣ ተደጋሚ ጥረት ቢደረግም አዋጁ ሊወጣ ከጥቂት ወራት ወዲህ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከሥራና ከተማ ልማት ሚኒስትር ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በመመሪያ መልክ በሽርክና ሊሠራ የሚያስችል መመሪያ ሊተላፍ መቻሉን አመልክተዋል፡፡ በዚሁ መመሪያ መሰረት ኮንትራክተሩ እንዲጠቁሙት መረጃዎችን እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ኮሎኔል እምላሉ ማህበሩ በእስከዛሬው እንቅስቃሴው በመንግሥት በኩል መሻሻል እንዲደረግባቸው ፈጣን ምላሽ ይሹ የነበሩ ጥያቄዎቻቸው መልስ ሊሰጥባቸው አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ማህበሩ ለመንግሥት አቅርቧቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል የኮንትራት አስተዳደር መሻሻል፣ የዋጋ ንረትን የተመለከተው አንቀፅ እንዲሻሻል፣ ለአለም አቀፍም ሆነ ለአገር ውስጥ ጨረታ መተዳደሪያ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲሻሻሉ ማድረግ በዘርፉ ለሚነሱ አለመግባባቶች አማራጭ መፍቻ ዘዴዎችን እንዲፈለጉ የሚሉ ናቸው፡፡ ኮሎኔል እምላሉ እንዳሉት በእነዚህ ዙሪያ ከመሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር ብዙ ቢነጋገርባቸውም አሁን ድረስ መፍትሄ ስላልተገኘላቸው አዲሱ አመራር ጠንክሮ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |