Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምግብ እርዳታን ይሻሉ
በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምግብ እርዳታን ይሻሉ Print E-mail
Sunday, 20 April 2008
ጐል ምላሽ ይሰጣል

ኢትዮጵያ በተመጣጠነ ምግብና በጤና አቅርቦት እጥረት በተከታታይ የምትጠቃ ሆናለች፡፡ ጥሩ የምርት ዘመን በተባለበት በ2ዐዐ6/2ዐዐ7 እንዲሁም 2007/2008 ባሉት ጊዜያት እንኳን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል እየተባለ ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሪሊፍ ድረ ገፅ ጐል ኢትዮጵያ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅትን ጠቅሶ እንደዘገበው ጐል በአገሪቱ ለተከሰተው የምግብ እጥረት ምላሽ ለመስጠት የወሰነው በቅርቡ ከዝናብ እጥረት ጋር በተለይ በገጠራማው አካባቢ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ከግምት በማስገባት ነው፡፡

 

ዘገባው ያመለከተው ኢትዮጵያ እስካሁንም ድረስ ከድሃ አገሮች የምትመደብ መሆኗንና 77 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ በቀን ከ2 ዶላር በታች ገቢ እንዳለው ነው፡፡ በሂውማን ዴቨሎኘመንት ኢንዴክስ 2ዐዐ6 ሪፖርት መሠረት ከ177 አገሮች በ17ዐኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ደግሞ ከድህነቱ በተጨማሪ ድርቅ እየታየባት ነው፡፡

የጤና አገልግሎት በአግባቡ አለማግኘት፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ ጥበቃ ካለመሰማት የሚመነጩ ግጭቶች እንዲሁም በዋና መሠረታዊ ምግቦች ላይ የዋጋ መናር ቀድሞውንም እየተጐዳ የነበረውን ህብረተሰብ አደጋ ላይ የሚጥል ሆኗል፡፡ በመሆኑም የተከሰተውን ሁኔታ ለመወጣት ለተጐጂዎቹ የተጠናና ልዩ የሆነ የምግብ ኘሮግራም አሊያም ደግሞ አጠቃላይ የሆነ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋል፡፡

በጤና፣ በተመጣጠነ ምግብና በውሃ አቅርቦት የሚሠራው ጐል በሚሰራባቸው አካባቢዎች ለተከሰተው የምግብ እጥረት ችግር ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅና በ2ዐዐ7 የተከሰተው የዝናብ እጥረት የአርብቶ አደሩን የመቋቋም አቅም የፈተነና የምግብ ዋስትናውን አደጋ ላይ የጣለ ሆኗል፡፡
 
በዞኑ አብዛኞቹ የግጦሽ መሬቶች ደርቀዋል፣ የቁም ከብቶች ተክለ ሰውነት ከስቷል፡፡ ወተት ሰጪ ላሞችን ጨምሮ ብዙ ከብቶች መሞታቸውም ታውቋል፡፡ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘታቸውም ትኩረት የሚሻ ሆኗል፡፡

ከተደረጉ ዳሰሳዎች በጤናው ዘርፍ የሚታዩ የመድኃኒትና የህክምና አቅርቦት እጥረት በዋናነት የታየ ችግር ነው፡፡ በመሆኑም የውሃ አቅርቦት፣ የከብቶች ምግብና የጤና ተቋማት ላይ የሚደረጉ እርዳታዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
 
ጐል በሚንቀሳቀስበት ቦረና አካባቢ በውሃ እጥረት ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ የቁም ከብቶች ውሃ የሚጠጡባቸው ስፍራዎችም ደርቀዋል፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብ ደግሞ ኑሮውን በከብቶቹ ተዋፅኦ ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ንብረቱም ከብቶቹ ናቸው፡፡ ሆኖም ከብቶች መሞት ጀምረዋል፡፡

ከየካቲት ጀምሮ ዝናብ በሚጠበቅበት በሲዳማ የሚንቀሳቀሰው ጐል እስካሁንም ድረስ በአካባቢው ዝናብ አለመጣሉን ገልጿል፡፡ የሚቀጥለው የዝናብ ወቅት መቼ ሊመጣ እንደሚችልም አይታወቅም፡፡

መንግሥት ሦስት የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ቢመድብም ሁለቱ በሜካኒካል ችግር ምክንያት አይሰሩም፡፡በመንግሥት መኪና አማካይነት የሚመጣውን ውሃም ለመጠቀም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቀን ለ18 ሰዓታት ያህል የሚሰለፉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

እንደ ጐል ገለፃ ከሆነ በደቡብ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች ውሃ የማቅረብ ሥራ፣ ከጤና ጥበቃ ጋር በመተባበር ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን መፍታት እንዲሁም በመድኃኒት አቅርቦትና ሊፈጠሩ በሚችሉ አፋጣኝ የጤና ችግሮች ላይ ትኩረት አድርጐ መስራትን አቅዶበታል፡፡

ውሃ በውሃ ማጠራቀሚያ ማቅረብ ዘላቂ ያልሆነና ውድ ቢሆንም የውሃ ምንጫቸው ለደረቀባቸው አካባቢዎች ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ በመሆኑም ጐል የውሃ ማጠራቀሚያዎችን በመከራየት በውሃ ችግር ለተጐዱ ህብረተሰቦች ያቀርባል፡፡ ለወደፊቱ ደግሞ ከውሃ ሃብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዘላቂነት ያለውን የቧንቧ ውሃ ለማስገባት ይሠራል፡፡ የተበላሹ የውሃ መስመሮችንም ይጠግናል፡፡

ለአፋጣኝ የጤና ችግር ምላሽ ለመስጠትም ከድርቅ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ ለሚችሉ እንደ ወባ፣ አፋጣኝ ተቅማጥ፣ ኮሌራና ለመሳሰሉት ወረርሽኞች መድኃኒት የመግዛትና የማከፋፈል ሥራን ይሰራል፡፡

የኘሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑትም በገጠራማው አካባቢ በድርቅና ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተጐዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ነው፡፡ ኘሮግራሙ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብና ሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችን እንደሚያቅፍ መረጃው አመልክቷል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር

 
< Prev   Next >