Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ዲያስፖራው ከቀድሞው...
ዲያስፖራው ከቀድሞው... Print E-mail
Sunday, 20 April 2008
Image
ወ/ት ዘነበች ኃይሌ
ዲያስፖራው ከቀድሞው በተሻለ መልኩ እየተስተናገደ ነው


በኦሮሚያ ክልል ዲያስፖራው ለመኖሪያም ሆነ ለኢንቨስትመንት መሬት ማግኘት እንዲችል መመሪያዎች ተዘጋጅተው ከበፊቱ በተሻለ መልኩ እየተስተናገደ መሆኑን በክልሉ የዲያስፖራ ጉዳዮች መከታተያና ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ት ዘነበች ኃይሌ ገለፁ፡፡

 

ኘሮግራሙ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለዲያስፖራው ታስበው የተዘጋጁና የሃገሪቱ ዜጐች መሳተፍ በሚችለባቸው መስኮች መሳተፍ እንዲችሉ አዳዲስ የአሰራር ስልቶች በመቀየስ፣ መመሪያና ደንብ በማውጣት ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ተመቻችቷል፡፡

የመኖሪያ ቤቱ አሰጣጥ የክልሉ መንግሥት የሚያወጣውን ሕግ መሠረት ያደረገ ሲሆን አሰራሩን ፍትሃዊ ለማድረግ በተቻለ መጠን እየሰሩ መሆኑን ወ/ት ዘነበች ገልፀው ዲያስፖራውም በመመሪያው መሠረት የታደሰ ፓስፖርት፣ ዜግነት የቀየሩ ከሆኑ የኢትዮጵያ ተወላጅነት መታወቂያ፣ በኢትዮጵያ ዜግነት ያሉ ከሆኑ በሚኖሩበት አገር የተሰጣቸው የመኖሪያ ፈቃድና ከኤምባሲ ነዋሪነታቸውን የሚያረጋግጥ የድጋፍ ደብዳቤ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፤ በአካል መምጣት የማይችሉም ከሆነ ለቤተሰባቸው ውክልና ሰጥተው ሊሠራላቸው ይችላል ብለዋል፡፡

ለመኖሪያ ቤት የሚሰጠው የቦታ ይዞታ በፅህፈት ቤቱ ደረጃ የሚወሰን ባይሆንም በመንግሥት ካቢኔ እንደ ከተሞች ደረጃ ከተደለደሉት ቦታዎች እስከ 2ዐዐ ካሬ ሜትር ከፍተኛው እንዲሁም ከ1ዐ5 እስከ 16ዐ ዝቅተኛው ይሰጣል፡፡ በአንደኛ ደረጃ ከተማ ካሉ ቦታዎች ጥበትና ፍላጐት የተነሳ 2ዐዐ ካሬ ሜትር አይሰጥም፡፡

ኢንቨስትመንትን በተለከተ በሁሉም ዘርፎች የተለያዩ እድሎች ያሉ በመሆኑ ዲያስፖራው አቅሙ በፈቀደና ፍላጐቱ በሆነው ዘርፍ ሊሠማራ ይችላል፡፡ ካለው በአንድ አካባቢ የመከማቸት አንፃር የአብዛኛው ዲያስፖራ ትኩረት በአዲስ አበባ ዙሪያ ነው፡፡ ሆኖም የትኛውም ቦታ ለሥራ አመቺ እስከሆነና አስፈላጊው ሃብት በቦታው እስከተገኘ በሁሉም ቦታ መስራት ተገቢ ነው፡፡ እንደ ዲያስፖራ ፅህፈት ቤትም ልማት በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች እንዲሠሩ እያስተዋወቁ ይገኛሉ፡፡

ኢንቨስትመንቱን ሳያስብ መኖሪያ ቤቱን ብቻ አልሞም የሚመጣ ዲያስፖራ መኖሩን የገለፁት ዳይሬክተሯ ለኢንቨስትመንቱ አቅም ያላቸው ከመረጃ እጥረት የተነሳ ኢንቨስትመንቱ ላይ ባያተኩሩም አገር ከገቡ በኋላ በሚያዩት ለውጥ ወደ ኢንቨስትመንቱ ለመግባት ስለሚያስቡ በየት መንገድና እንዴት የሚለውን በተመለከተ ቢሮው ድረስ በመምጣት መረጃ ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡

ለሃገሪቱ የሥራ እድል እስከፈጠረና እስከጠቀመ ድረስ ዲያስፖራው ተሳታፊ እንዲሆን ቢሮው ያበረታታል፡፡ ከኢንቨስትመንት ቢሮም ዝርዝር መረጃ እንዲያገኙ፣ ጥናት እንዲያደርጉ፣ አካባቢው ምን እንደሚመስል እንዲያዩ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ዲያስፖራው ሊሰራ ያሰበውን ነገር ቆም ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በግብርና በእህል፣ በከብትና የከብት ተዋፅኦ፣ በአበባ፣ በሆቴልና በመዝናኛ ስፍራዎች ሱፐርማርኬትን ጨምሮ አብዛኛው ዲያስፖራ የሚሠራበት ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ምን ያህል ዲያስፖራ በክልሉ ወደ ሥራ እንደገባ ማወቅ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም መሬት የሚጠይቀውና ቢሮው ደብዳቤ ፅፎ የሚሸኘው ሁሉ ወደ ሥራው ገብቷል ለማለት ያስቸግራልና፡፡ መሃል ቤት የሚቀሩም አሉ፡፡ በሚያዩት ነገር ብቻ ተነሳስተው ብዙም ሳይዘጋጁበት ይወስኑና የተወሰነ ደረጃ ሄደው የሚቀሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም የሚያበረታታ ተነሳሽነት እንዳላቸውና ወደፊት ሊሠሩ እንደሚችሉ ተስፋ መኖሩን ወ/ት ዘነበች ገልፀውልናል፡፡

ከሐምሌ 1999 ጀምሮ ባለው ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ 436 የሚሆኑ ዲያስፖራዎች ደብዳቤ ተፅፎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቀጥታ በኢንቨስትመንት ቢሮ በኩል የሚስተናገዱ አሉ፡፡ በአግሮ አንዱስትሪ፣ በትምህርት ዘርፍ በጤና መስክ፣ በሆስፒታልና ክሊኒክ እንዲሁም ሥልጠና፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በፋብሪካ በምግብ፣ የኮንስትራክሽን እቃዎች፣ ሳሙና፣ የምግብ ዘይት፣ የትምህርት መሳሪያዎች ምርትና በመሳሰሉት ለመሰማራት በጠየቁት መሠረት ወደ ኢንቨስትመንት ቢሮም ተልከዋል፡፡

ወ/ት ዘነበች እንደሚሉት አብዛኞቹ ባለጉዳዮች መሬት የወሰዱ አይደሉም፡፡ ተራ እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ በከተሞች ወይም በዞኖች አካባቢ ያለው ችግር የተከሰተው ከተዘጋጁበት በላይ ዲያስፖራው እየመጣ በመሆኑ ነው፡፡ በክልሎች አካባቢ የተዘጋጀው መሬት አልቆ ግዴታ ሌላ ለማዘጋጀት የራሱን ሂደት ይጠብቃል፡፡ የሚዘጋጀው መሬት በገበሬ እጅ ያለ ሊሆን ይችላል፣ ወደ ከተማ የሚጠቃለሉ መሬቶች አሉ፡፡ ገበሬዎችን አሳምኖ ማንሳት፣ ካሳ መክፈል፣ መተመን የራሱ የሥራ ሂደትና ጊዜ አለወ፡፡ ይህ ዲያስፖራውን ወረፋ እንዲጠብቅ ያደርገዋል፡፡

ዲያስፖራው ችግር ብሎ የሚያነሳው የተቀላጠፈ መስተንግዶ አለመኖር ነው፡፡ በዲያስፖራውና በአገልግሎት ሰጪው መካከል እኩል ግንዛቤ አለመኖሩ ለዚህ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ለዲያስፖራ ተብሎ የተቀረፀው ኘሮግራም አዲስ ነው፡፡ አገር ውስጥ እስከታች ካለው የመንግሥት መዋቅርና ከህዝቡ ጋር የተዋሃደ አይደለም፡፡ ሰፊ የቅስቀሳ ሥራም አልተሠራበትም፡፡ በቀጣይ ግን ክፍተቶቹን ለመሙላት የሚያስችሉ ዶክመንቶች ስላሉ በአሰራሩ ላይ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት አላቸው፡፡ አሁንም ሲጀመር ከነበረው መስተንግዶ በተሻለ እያገለገሉ ነው፡፡

የግንዛቤው አለመመጣጠን ከዋና ፅህፈት ቤት ወደ ዞኖች በሚወርድበት ጊዜም የሚከሰት በመሆኑ ዲያስፖራው የጀመረው ሥራ የማይሳካለት እየመሰለው የሚፈራበትና የሚያቆምበት ሁኔታም አለ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የሚያጋጥማቸውን ችግር ሁሉ ተቋቁመው ወደ ሥራም የገቡ አሉ፡፡

ዲያስፖራው ኢንቨስትመንቱንም ሆነ የመኖሪያ ቤቱን እድል ለመጠቀም በፍርሃት የተነሳ የማይመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ ልሞክረው ብለው የሚመጡም አሉ፡፡ "ችግሮቹ ግን ለዲያስፖራው ብቻ የተቀመጡ አይደሉም፡፡ አገር ውስጥ ላለው ነዋሪ በተለይ ይብሳል፡፡ ሆኖም በመንግሥት መስሪያ ቤት ያለው አገልግሎት እየተሻሻለ ነው" ብለዋል፡፡

መንግሥት የዲያስፖራውን ጉዳይ አስቦ በጀመረበት ጊዜ ውስብስብ የነበሩ ጉዳዮች መፍትሄ እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡ ለዚህም የዲያስፖራን ጉዳይ ለማየት በፅህፈት ቤት ደረጃ መቋቋሙ በራሱ ለውጥ ነው፡፡

በፅህፈት ቤት ደረጃ የወረቀት ሥራ ነው የሚሠራው፡፡ ሆኖም ተጨባጩ ሥራ የሚሠራበት ታች ሲደርስ (መሬት መስጠት) ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው በቦታ ጥበት፣ ተዘጋጅቶ የነበረ ቦታ የማለቅና እስከሚዘጋጅ የአሰራር ሂደቱ ጊዜ የመውሰድ ባህሪ ስላለው ነው፡፡ በቦታውም ምን ያህል አቅሙ ያለው ሰው አለ፣ በቂ የሰው ሃይል አለ ወይ የሚለው ነገሩ እንዲከብድ ያደርገዋል፡፡

የታክስ ጭማሪ ተደርጐብናል የሚሉ ዲያስፖራዎች ቢኖሩም የኦሮሚያ ክልል ከአገሪቱ ህግ በተለየ ታክስ እንደማይጨምር ወ/ት ዘነበች ተናግረዋል፡፡ የተወረሱ የዲያስፖራ መሬቶችን በተመለከተ ግን አግባብ ባለውና በውሉ መሠረት የሚፈፀም ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ወ/ት ዘነበች እንደሚሉት ዲያስፖራው በሚፈልገው መስክና አካባቢ ለመሥራት በጠየቀው መሠረት መሬት እንዲያገኝ ሲወሰንለት የሚገባው ውል አለ፡፡ የመሬት ሰጪና ተቀባዩ ውል ከመፈፀማቸው በፊት ውል ተቀባይ ያሉትን ግዴታዎች ሁሉ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡ ውል ተቀባዩ ግዴታውን ለመፈፀም ሲያምን ውሉን ይዋዋላል፡፡ የሚከፍለውም ክፍያ ይኖራል፡፡ ክፍያው እንደየአካባቢው ይለያያል፡፡ የሊዝ መሬት ሆኖ ከገበሬ የተወሰደ ከሆነ የካሳና የሊዝ ተደምሮ ይከፍላል፡፡ የኪራይ መሬት ሆኖ ከገበሬ የተወሰደ ከሆነ ኪራዩን እንደገባበት ዓመት ርዝማኔ አምስት ወይም አስርና ከዛም በላይ ይሆናል ካሳን ጨምሮ ይከፍላል፡፡ ካሳን በተመለከተ የሚከፍለው ለመንግሥት እንጂ ቀጥታ ለገበሬዎች አይደለም፡፡

የሊዝም ሆነ የኪራይ መሬት ክፍያው ከካሳው በተጨማሪ እንደ ዓመቱ ብዛት 1ዐ በመቶ ይከፍላል፡፡ የክፍያው መጠን እንደየመሬቱ ስፋት ልክ ይጨምራል፡፡ ውሉን ተዋውሎ ሲከፍል የባለቤትነት ማረጋጫና ካርታ ያገኛል፡፡

በውሉ መሠረት ባለሀብቱ የተረከበው መሬት ላይ እስከ ስድስት ወራት ድረስ የኘሮጀክቱ አካል የሆነ መሠረታዊ ሥራ መጀመር አለበት፡፡ ይህ አጥር ማጠር ማለት አይደለም፡፡ መሠረታዊ ሥራ ካልተጀመረ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ ችግሩ ከመንግሥት አካል ከሆነም ይታያል፡፡ ይፈታል፡፡ ከባለሀብቱ ከሆነ አስተያየት ጭምር ይሠጣል፡፡

"ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ፅህፈት ቤቱ ድረስ የመጡበት ሁኔታም አለ፡፡ ከዓመት በፊት ከገበሬ መሬት ተሰጥቶ ምንም ሳይሰራበት ይቀመጣል፡፡ ገበሬው እጅ ቢሆን ምን ያህል ሊያመርት እንደሚችል መታሰብ አለበት፡፡ ገበሬው ከነቤተሰቡ ከቦታው ተነስቶና ካሳ ተሰጥቶት ነው መሬቱ ለሌላ የተሰጠው፡፡ መሬቱን የተረከበው ሥራ ቢጀምርበት የሚቀጥረው ሰው፣ ልማቱ ታስቦ ወይም አቅሙ ላለው ሰው ተሰጥቶ ቢሆን ሊከናወን የሚችለውን ሥራ ከግምት በማስገባት ነው ህጋዊ እርምጃው የሚወሰደው፡፡ እውቀት፣ ገንዘብ፣ ልምድ ይዞ የሚጠይቅ እያለ መሬት ይዞ አላግባብ ማስቀመጥም ተገቢ አይደለም፡፡ እርምጃው የሚወሰደው ጥናት ተደርጐ፣ በኢንቨስትመንት ቦርድ ታይቶ ነው፡፡ አስተዳዳራዊ ችግሮችንም የሚፈታው ቦርዱ ነው፡፡ ከውላቸው፣ ከእውቅናቸውና ካለው መመሪያና ደንብ ውጪ የተወረሰባቸው ዲያስፖራዎች የሉም" በማለት ገልፀዋል፡፡

ዲያስፖራው በእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን አገሩ ገብቶ ሥራ ከጀመረ በኋላ የሚያቆምበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህ የሚሆነው በትንሹም በትልቁም ፈተና ሲገጥማቸው ቶሎ ተስፋ በመቁረጣቸው ነው፡፡ ከራስ የዝግጅት ማነስም የሚፈጠር ችግር አለ፡፡ ወሳኝ ነገር ላይ ሲደርሱ በራስ የመተማመን ኃይላቸው ይሟጠጣል፡፡ ለምሳሌ ከአቅም ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ ትልቅ ነገር ጠይቀው ሲፈቀድላቸው አቅም ያንሳቸዋል፡፡

በአንዳንድ ዲያስፖራ በኩል የሚታየው ችግር የአብዛኞቹ ፍላጐት የመኖሪያ ቤት ቦታ ማግኘት መሆኑ፣ ፍላጐታቸው በአዲስ አበባ ዙሪያ ማተኮሩ፣ ለኢንቨስትመንት ርቀው መሄድ አለመፈለጋቸውና ለዲያስፖራው የተሰጠውን መብት አላግባብ ለመጠቀም መሞከራቸው ነው፡፡
በምህረት ሞገስ

 
< Prev   Next >