|
Sunday, 20 April 2008 |
"ሐዲዱን የሳተውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ሐዲዱ ለመመለስ በጎ ፈቃደኝነትን ይጠይቃል" ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ የቀድሞ የቅንጅት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልበቀድሞ ቅንጅት መሪዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ልዩነቶች ተፈጥረው ቆይተዋል፡፡ መከፋፈሉን በሚመለከትና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ ብርሃነ ዓለሙ ከዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዳንድ ወገኖች ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ በፖለቲካ ተስፋ መቁረጥ ይቻላል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በእርግጥ ብዙ እንቅፋቶች ከፊታችን ተጋርጠዋል፡፡ በፖለቲካው ሂደት ብዙ ተስፋ ሊያስቆርጡ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡ ከምርጫ 97 ጀምሮ በቀድሞው ቅንጅት ላይ የደረሰው ወከባ፣ የደረሰው እንግልት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስታውሰው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ግን በፖለቲካ፣ በአገር ዴሞክራሲያዊ ሂደት፣ በአገር ልማት ላይ ተስፋ መቁረጥ አይቻልም፡፡ ትግሉ እየከረረ ሲመጣ ለትግሉ የሚሰጠውም አፀፋ አጠንክሮ መቀጠል እንጂ ተሸንፌያለሁ ብሎ እጅን አጣምሮ መቀመጥ አይቻልም፡፡ ይኼ በብዙ አገሮች የታየ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያም ይህ መታየት የለበትም፡፡ የአገር ጉዳይ ነው፣ የዴሞክራሲ ጉዳይ፣ የልማት ጉዳይ፣ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ትግሉ ከበደ፣ እንቅፋቶች በዙ፣ በደሎች አየሉ ተብሎ ተስፋ ሊቆረጥ አይገባም፡፡ ብዙዎቻችንም ቃል የገባንበት ጉዳይ ነው፡፡ ተስፋ ቆርጠን ወደ ቤታችን አንገባም፡፡ ሕይወታችን እስካለ ድረስ የምንችለውን ያህል፣ አቅማችን የፈቀደውን ያህል ለአገራችን ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ልማት የምናደርገው አስተዋጽኦ፣ የምናደርገው ትግል መቼም ቢሆን አንተውም፡፡
ሪፖርተር፡- በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት አይቻልም ብለው ተስፋ የቆረጡ ወደ ትጥቅ ትግል ይገባ የሚሉ አሉ፡፡ ይደግፏቸዋል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይኼ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ የመቁረጥ ምልክት ነው፡፡ በደረሱ ወከባዎች ምክንያት አንዳንድ ሰዎች የያዝነው ሰላማዊ መንገድ የትም አያደርሰንም፡፡ ሰላም፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲ መጎናፀፍ የሚቻለው ካለው መንግሥት በኃይል ስልጣን በመንጠቅ ወይም ደግሞ አስገድዶ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ አምጥቶ መነጋገር ሲቻል ነው ብለው የደመደሙ አሉ፡፡ በቀድሞ ቅንጅት ወይም በአሁኑ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በተደጋጋሚ እንደገለፅነው እኛ የትግል ስልታችን ኃይልን ያዘለ አይደለም፡፡ ትግላችን ሰላማዊ ነው፡፡ ይህንን እንድንል ያደረገን የትጥቅ ትግሉ ቢካሄድ አይሳካም በሚል ብቻም አይደለም፡፡ የትጥቅ ትግል ስልጣን ላይ ያለውን አንድን መንግሥት ያስወግድ እንደሆነ ነው እንጂ መሠረታዊ ለውጥ እንደማያመጣ በተደጋጋሚ ተናግረናል፡፡ ከሆችሚን ጊዜ አንስቶ፣ ኢምፔሪያሊስቶችን ከጫንቃቸው ላይ ከማውረድ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊመሰርቱ አልቻሉም፡፡ ከዚህ ቀደም ብለን በካስትሮ የተመራው የትጥቅ ትግል እንደዚሁ ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም መንጋጋ ለመውጣት ካልሆነ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዳላሰፈነ ማየት ችለናል፡፡ ወደ አፍሪካም ብንመጣ የሙሴቪኒ፣ የኢሣያስ፣ የመለስም ሁኔታ ይኸው ነው፡፡ የትጥቅ ትግል በተካሄደባቸው አገሮች ዘላቂነትና ቀጣይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አልተመሠረተም፡፡ እርግጥ በጊዜው የነበሩ ጨቋኝ መሪዎችን ለማስወገድ ተችሏል፡፡
ሪፖርተር፡- የተቃዋሚ ኃይሎች ደክሞ መገኘትስ አይስተዋልም ወይ? ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የማምጣት ብቃት አላቸው? ቀድሞ እናንተ ትመሩት የነበረው ቅንጅትን በምሣሌነት እየጠቀሱ የሚተቹ አሉ፤
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በፖለቲካ፣ በትግል ሂደት መዳከምም መጠናከርም አለ፡፡ ይኸ በየትኛውም አገር የታየ ነው፡፡ በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ውስጥም ብዙ ጊዜ ተከስቷል፡፡ አሁን በገጠመን እክል ምክንያት አንደኛ በገዢው ፓርቲ በደረሰብን ወከባ ሁለተኛ በመካከላችን በተፈጠረው አለመግባባት ጫና አልተፈጠረም ማለት አልችልም፡፡ ያም ሆኖ የቀድሞው ቅንጅት በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ እንዳለ ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡ በድርጅቱ አመራር በኩል ድክመት ሊታይ ይችላል፡፡ አሁን ፓርቲ የለንም፡፡ በማቋቋም ላይ ነን፡፡ አዲሱ ፓርቲ እንደተቋቋመ ቀድሞ የነበረው እንደሚመለስ አልጠራጠርም፡፡ ዋናው የሕዝቡ ድጋፍ ነው፡፡ መሠረታችን ሕዝብ ነው፡፡ ፍቅሩ እንዳለ ስለሆነ በተሻለ መልኩ ተደራጅተን፣ ተጠናክረን ወደ ሕዝባችን እንቀርባለን፡፡
ሪፖርተር፡- የቀድሞ ቅንጅት እንዲዳከም፣ እንዲከፋፈል መንግሥት ወይም ገዢው ፓርቲ ጣልቃ ገብቷል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ወይም ገዢው ፓርቲ እጁ ይኑርበት አይኑርበት የምናውቀው ነገር የለም፡፡ እስካሁን የሚታወቀው በቀድሞ ቅንጅት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ የተፈጠረ መከፋፈል ነው፡፡ ወከባዎች በፊትም ቢኖሩም ነገር ግን ኃላፊነቱን ወደሚገባው ማላከክ እንጂ ሌላውን መውቀስ አይገባም፡፡ በተፈጠረው መከፋፈልና ይህን ተከትሎ በደረሰው ችግር ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግሥት እጃቸው ነበረበት የሚል ማስረጃ የለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- የቀድሞ ቅንጅት እርሱ ባለው መንገድ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን ይዞ ቢሆን ኖሮ መሪዎቹ ከእሥር ከተፈቱ በኋላ ያጋመውን መከፋፈል አይከሰትም ነበር ለማለት ምን ዋስትና ይኖራል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ምን ይሆን ነበር ብሎ መተንበይ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስልጣን ብንረከብ ኖሮ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር አንችልም ነበር የሚል ማረጋገጫም ሆነ ማስረጃ የለም፡፡ በክርክሩ ጊዜ እንደታየው፣ ሕዝቡም እንደተገነዘበው ከገዢው ፓርቲ የተሻለ ዕውቀትና ችሎታ ያላቸው ሰዎች እንደነበሩ አስመስክረናል፡፡ ሕዝብ በሚመርጥበት ጊዜ ሞኝ አይደለም፡፡ የሚሠራውን ያውቃል፡፡ ቅንጅትን መርጦ የነበረው ተማምኖ ያስተዳድረኛል፣ ዴሞክራሲን ያጎናጽፈኛል፣ በልማት ወደፊት ያራምደኛል ብሎ ነው፡፡ ለዚያ ብቁ የማንሆንበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ከኢህአዴግ በተሻለ ሁኔታ እንሰራለን በሚል እምነት ነበር ምርጫ ውስጥ የገባነው፡፡ እኛ ብቻችንን የኢትዮያን ሕዝብ ከችግር እናወጣዋለን፣ ዴሞክራሲ እናጎናጽፈዋለን የሚል ብዥታም አልነበረንም፡፡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን (ኢሕአዴግም ጭምር) ጋር እንጂ ብቻችን ተገንጥለን ወጥተን፣ ሌላውን አግልለን ስልጣን እንይዛለን የሚል ፍላጎት አልነበረንም፡፡ ከመጀመሪያውኑ ይህንን አመላክተናል፡፡ በቅንጅት መሪነት ቢሆንም ሌሎችም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢሕአዴግም ጭምር የሚሳተፍበት መንግሥት ይሆን ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ከእስር ቤት ከወጣችሁ በኋላ በታየው መከፋፈል ምክንያት "እንኳንም ሥልጣን አልያዙ" ያሉ አሉ፡፡ ቅንጅት ሥልጣን ይዞ ቢሆን ኖሮ የሚደርሰው ጥፋት ከፍተኛ ይሆን ነበር በማለት ስጋታቸውን የገለፁም አሉ፤
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይሄ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ከእስር ከተፈታን በኋላ በማናቸውም ፓርቲ የሚታይ መከፋፈል፣ አለመግባባት፣ አለመጣጣም አጋጥሞናል፡፡ መከፋፈሉ፣ አለመግባባቱ ሊታረቅ የሚችል ነበር፡፡ አገርን የመምራት ኃላፊነት ብንረከብ እነዚህ እልባት የማያገኙ አልነበሩም፡፡ ቀላል ጉዳዮች ናቸው፡፡ የግለሰቦች አለመጣጣም እንጂ መሠረታዊ ነገር አይደለም፡፡ በፖሊሲ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ የሚያጣላም አልነበረም፡፡ እንኳን ስልጣን አልያዙም የሚሉ ሰዎች ሌላ ዓላማ ቢኖራቸው ነው እንጂ አገሪቱን ማስተዳደር አይችሉም ነበር ከሚል እምነት አይመስለኝም፡፡ የተለያየ ዓላማ ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ይሆናሉ፡፡ ይህም ቢሉ ግን የሚያስወቅሳቸው አይደለም፡፡ እኛን የሚቃወሙ ናቸውና፡፡ አገሪቱን አሁን ካለችበት በተሻለ እንመራታለን የሚል እምነት ነበረን፡፡
ሪፖርተር፡- ከመንግሥት (ከገዢው ፓርቲ) ጋር በመደራደር ከእስር ቤት መውጣት እየቻላችሁ በእናንተ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት እንዴት አቃታችሁ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ለዚህ መልስ ለመስጠት በጣም ይቸግረኛል፡፡ ቅድም እንዳልኩት በመካከላችን መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ እርቅ ለማውረድ ብዙ ሙከራ ተደርጓል፡፡ እኔ በግሌም ብዙ ጥረት አድርጌ ነበር፤ ነገር ግን አልሆነም፡፡ ከግለሰቦች ፀባይም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱ ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ስልት ለመፍታት ሳይሆን በአምባገነንነት ለመፍታት በመሞከሩ ይሆናል፡፡ ያም ሆነ ይህ በውስጣችን የተከሰተው አለመግባባት መፍታት አልተቻለም፡፡ ከማዘን ውጪ ለዚህ አጥጋቢ መልስ የለኝም፡፡ አሁን ዋናው የጠፋው ጠፍቶ፤ የተበላሸው ተበላሽቶ ከእንግዲህ ፓርቲያችንን አፅድተን ወደፊት መገስገስ ነው ያለን አማራጭ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ቃል የገባነው ይኸው ነው፡፡ በዚህ እንቀጥልበታለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከእስር ቤት እንደወጣችሁ የተከሰቱት ችግሮችን በወቅቱ መፍታት አልቻላችሁም፡፡ አሁን ከተረጋጋችሁ በኋላስ እርስ በርስ ተገናኝታችሁ ለመነጋገር አልሞከራችሁም?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ሁለት አቋም ይዘን አንቀሳቀስም፡፡ ነገር ግን ሁለት አካላት አሉ፡፡ እነኚህን ማገናኘት አልተቻለም፡፡ አዲሱ ፓርቲ ለማቋቋም የምንጥር ሰዎች ሌሎቹም ወደ ስብሰባ እንዲመጡ ብዙ ጊዜ ጋብዘናል፣ ጥሪ አድርገናል፡፡ ከእኛ የተለዩ ወደ ሕጋዊ መስመር እንመጣለን ካሉ ቦታቸው እንዳለ ነው፡፡ በሂደት የሚፈታ ይሆን ይሆናል፡፡ አንዳንዶች ስህተታቸውን ተረድተው የሚመለሱበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ጊዜ መድሃኒት ነው፡፡ ኃይልና ጥንካሬ የምናገኘው በኅብረት መሆኑን ተገንዝበው ወደ ቀድሞው ፓርቲያቸው እንደሚቀላቀሉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- አፅድተን አዲስ ፓርቲ እንመሰርታለን ብላችኋል፡፡ የቀድሞ መከፋፈል እንዳያጋጥማችሁ ምን ማረጋገጫ አለ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ዋስትናው የፓርቲው አባላት ንቃተ ኅሊና መዳበር፣ የአመራሩ ብቃት፣ በዴሞክራሲያዊ ሂደት ፅኑ እምነት እንዲኖር ጥረት እናደርጋለን፡፡ በአንድ ሰው ኃላፊነት አንድ ፓርቲ ሊመራ አይችልም፡፡ አመራሩ የጋራ እንዲሆን እያዋቀርነው ነው፡፡ የነበረው መተዳደሪያ ደንብ እየተሻሻለ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ ማሠሪያዎች እየተበጀለት ነው፡፡ ከማሠሪያዎች አንዱ ውሳኔዎችን ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑ፣ ማንኛውም ሰው በግሉ የሚወስነው ምንም ነገር እንዳይኖር የጋራ ውሳኔና የጋራ አመራር እንዲኖር በመተዳደሪያ ደንቡ ተካትቷል፡፡ ያካተትናቸው ማሠሪያዎችና ገደቦች ያለፈውን ዓይነት ችግር ወደፊት እንዳይከሰት ይረዳሉ የሚል እምነት አለን፡፡ በተጨማሪም ለራሳችንም ሆነ ለአባላት ዴሞክራሲያው አካሄድ እንዲዳብር ሥልጠናዎችን ለማካሄድ እቅዶች አሉን፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ የምታቋቁሙት ፓርቲ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የፓርቲዎች የምዝገባ ሕግ በሚጠይቀው መሠረት ከአራት ክልሎች ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ፊርማዎች በላይ አሰባስበናል፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ አንዳንድ መሻሻሎች እየተደረጉበት ነው፡፡ ጠቅላላ ጉባዔ ለመጥራት ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ በዚህ ሂደት የገጠመን እንቅፋት የለም፡፡ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በምርጫ ቦርድ በኩልም እየተስተናገድን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከእስር ቤት እንደወጣችሁ በየፊናችሁ ወደ ውጭ አገር ሄዳችሁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያካሄዳችሁ ነበር፡፡ ወቀሳም ድጋፍም ነበር፤
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በውጭ ባደረግነው እንቅስቃሴ በጣም ረክተን ነው የተመለስነው፡፡ ሁለት ተግባራት ነበሩን፡፡ አንደኛ ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስለ ፓርቲያችንና ስለወቅቱ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለማስረዳት ነበር፡፡ በታሰርን ጊዜ በረዶ፣ ፀሐይ ሳይሉ መንግሥታትን በመማፀን የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ስለከፈሉ ለዚህ ምስጋናችንን ለማቅረብ ነው፡፡ ሁለተኛ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የፓርቲያችንን ሂደት ለማስረዳት፣ የወደፊት እቅዳችንን፣ ለአገራችን የሚደረጉ ልማታዊ ዕርዳታዎች እንዲጨምሩ ለማሳሰብ ነበር፡፡ በሁለቱም በኩል በጣም ተሳክቶልናል፡፡ ከኢትዮጵያውያኑ ይልቅ በጣም ያስገረመን ከተለያዩ አገሮች ባለስልጣናት የተደረገልን አቀባበል ነው፡፡ ብዙዎቹ ስለቅንጅት ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ በአንዳንድ አገሮች በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደረጃ ነው የተቀበሉን፡፡
ሪፖርተር፡- በተለይ እርስዎ ለአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ንግግር ሲያደርጉ ሚስ አናጎሚዝን አወድሰዋል፤
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የተናገርኩት ሚስ አናጎሚዝ እኛን ለማስፈታት ላደረጉት ጥረት እናመሰግናለን የሚል ነው፡፡ በሪፖርተር ጋዜጣ ግን ሚስ አናጎሜዝ ስላስፈታቻቸው እጅ ነሱ፣ ከርቤ አቀረቡ ነው የተባለው፡፡ ለዚህ መልስ ጽፌ ነበር ነገር ግን አልወጣም፡፡
ሪፖርተር፡- ሚስ አናጎሜዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢወዳደሩ ሕዝቡ ለፕሬዚዳንትነት ይመርጥዎት ነበርም ብለዋል፤
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ሚስ አናጎሜዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ተወዳጅ ስለሆኑ ለፕሬዚዳንትነት ቢወዳደሩ ኖሮ ይመረጡ ነበር ብያለሁ፡፡ ይኼ ከቀልድ ያለፈም አይደለም፡፡ በአገራችን ፕሬዚዳንት በሕዝብ አይመረጥም፡፡ የውጭ አገር ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ፕሬዚዳንት አይሆንም፡፡ ከቀልድ ያለፈ አልነበረም፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣም ሆነ ሌሎች ባለስልጣናት ይህንን እየጠቀሱ ሲያፍተለትሉት ነበር፡፡ በንግግሬ መካከል ጣል ያደረግኩት እንጂ ከዚህ ያለፈ አልነበረም፡፡ ቀልድ መሆኑን ማንም ሊገነዘበው የሚችል ነው፡፡ ሌላው ያሳዘነኝ ከሻዕቢያ እርዳታ ያገኛሉ፣ ሞላጮች ያሉበት ፓርቲ ነው በሚል የተፃፈው ነው፡፡ በቀድሞ ቅንጅት ውስጥ የነበሩ አንዳንዶቹ በአገርም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ሰዎች ናቸው፡፡ አያቶችም የሚሆኑ አሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ዝቅ አድርጎ መሳደብ በባህላችንም ነውር ነው፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ አንዱን ፓርቲ ሊደግፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን ለፃፈው ጉዳይ መልስ ሲላክለት መልሱን አላወጣም ማለት ከሥነ ምግባር ውጪ ነው፡፡ ይኼ መሠረታዊ መብት ነው፡፡ ይህን መብት ተነፍገናል፡፡
ሪፖርተር፡- ጋዜጣው መብት ነፍጎናል ሲሉ እንዴት አረጋገጡ? ደብዳቤ ልከው ለምን እንዳልወጣ ማንን ጠየቁ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ለጋዜጣው ባልደረባ በእጅ ነው የሰጠሁት፡፡ ለምን እንዳልወጣ ስጠይቀው አዘጋጁ ሊወጣ ፈቃደኛ አልሆነም ነው ያለኝ፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ ከምርጫ 97 በፊት ለኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጣ ያደረገው አስተዋፅኦ የሚረሳ አይደለም፡፡ ትልቅ ከበሬታም አግኝቶ ነበር፡፡ ከምርጫው ወዲህ ያለውን ግን እናንተም ጠይቃችሁ ከሕዝቡ ተረዱ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ የት የሚያመራ ይመስልዎታል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሐዲዱ ወጥቷል፡፡ ከ97 ምርጫ በፊት በአገራችን ተፈጥሮ የነበረው አየር፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ መሻሻል አሁን በአብዛኛው ተቀልብሷል፡፡ ለዚህ የነበሩት ነፃ ጋዜጦች ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ፡፡ ያኔ ይፃፉ የነበሩ ርዕሰ አንቀፆች፣ አርቲክሎች ከአሁኖቹ ጋር ሳነፃፅራቸው በጣም ነው የማዝነው፡፡ የፕሬስ ነፃነትን በሚመለከት ምን ያህል ወደታች እንዳዘቀጥን መመልከት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል የተወሰኑ ጋዜጦች በተለያዩ መንገዶች ታግደዋል፡፡ አሁን ደግሞ አዳዲስ ጋዜጦች እየወጡ ነው፡፡ አንዳንዶች የተቀለበሰ ነገር የለም፤ ሳንሱር አልተጀመረም ይላሉ፤
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ከዚያ በፊት በደረሰባቸው እስራትና እንግልት ምክንያት እነኚህ ጋዜጦች በፍርሃት እንደተሸበቡ በግልፅ ይታያል፡፡ አፃፃፋቸው በጣም ጥንቃቄን የተሞላበትና ሊሉት የፈለጉትን በግልፅ ላለማለት የሚጨነቁበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በፍርሃት ተሸብበው ነው የሚፅፉት፡፡ የሚፅፏቸው ርዕሰ አንቀፆች ፍሬ ርስኪ ናቸው፡፡ ልታመዛዝኑ ትችላላችሁ፡፡ ከ97 በፊት እንዲህ አልነበረም፡፡
ሪፖርተር፡- የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት አስገድዶ ቢሆንስ? አሁን ፖለቲካው በረድ ያለ ይመስላል፤
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ትኩሳቱ የነበረው አየሩ ነፃ ስለነበረ ነው እንጂ የተለወጠበት ሁኔታ የለም፡፡ በክርክሩ ጊዜ ያላንዳች ሳንካ በግልፅ ነበር የተናገርነው፡፡ በግልፅ ነው የተከራከርነው፡፡ ጋዜጦችም ያለምንም መሸማቀቅ ነው ሕግን ሳይጥሱ ሲፅፉ የነበረው፡፡ አሁን ይኼ የለም፡፡ ፖለቲካው ሐዲዱን ስቷል፡፡ አሁን የሚታየው የዴሞክራሲ ሁኔታ በፍርሃት የተሸበበ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተለይ እሥር ቤት የነበራችሁና ውጭ አገር ደርሳችሁ የተመለሳችሁ የቀድሞ ቅንጅት አመራር አባላት አሁን የሚደርስባችሁ የመናገርም ሆነ የመፃፍ ተፅዕኖ አለ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የለም፡፡ እኔ እስካሁን ድረስ የደረሰብኝ ወከባም ሆነ ለመፃፍ የተከለከልኩበት ሁኔታ የለም፡፡ ለሪፖርተር ጋዜጣ የፃፍኩት ግን በማን ከልካይነት እንደቀረ አላወቅኩም፡፡
ሪፖርተር፡- ጽሑፍዎ ለምን እንደቀረ ዋና አዘጋጁን ወይም ምክትል አዘጋጁን ለመጠየቅ ሞክረዋል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ጽሑፉን የሰጠሁት ጋዜጠኛ ነው ያገኘሁት፡፡ አጥጋቢ መልስ አልመለሰልኝም፡፡ ዋና አዘጋጁ ጽሑፉን እንዳዩት ግን ነግሮኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ውጭ የነበረዎትን ሥራ ትተው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በፖለቲካው በመሳተፍዎ ይቆጭዎታል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አሜሪካ የዕድሜ ልክ ፕሬፌሰር ነበርኩ፡፡ ፕሮፌሰርነቱን ትቼ በተባበሩት መንግሥታት በናይጄሪያና በካሜሩን መካከል ያለውን የድንበር ግጭት በሚመለከት በሕግ አማካሪነት ተቀጥሬ ስሠራ ነበር፡፡ በዚህ ላይ እንዳለሁ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በኢትዮጵያ ውስጥ እንከን የለሽ ምርጫ ይካሄዳል ሲሉ ሥራዬን ትቼ ነው የመጣሁት፡፡ እስከ ዛሬ በደረሱብኝ እንግልቶች ምክንያት አንድም ቀን ተፀፅቼ አላውቅም፡፡ ከዚህ የባሰውንም ቢደርስብኝ አልፀፀትም፡፡ እንደ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካው መንቀሳቀስ ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፡፡ በዐፄ ኃይልሥላሴ ጊዜ የተማሪዎች ፕሬዚዳንት ነበርኩ፡፡ ከዚያም በውጭ አገር ደርግን ስታገል ቆየሁ፡፡ የአቅሜን ያህል አስተዋፅኦ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ አገራችንን ከጦርነትና ከችግር አዙሪት ማውጣት እንዳለብን ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ ዕድሉ ሲገኝ መጣሁ፡፡ በዚህ አልፀፀትም፡፡ በእርግጥ ሥራ የለኝም፡፡ አዲሱን ፓርቲ በማቋቋም ሂደት ላይ ነን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ዕድሎችን ሰጥቶኛል፡፡ እስከ ፒ ኤች ዲ ለመማር ዕድሉን አመቻችቶልኛል፡፡ ይህንን ለመካስ ነበር የመጣሁት፡፡ ለመካስም ሞክሬያለሁ፡፡ ካሳውን ግን አልከፈልኩም፡፡ በእኔ ጥፋት ሳይሆን በሌላ ወገን ምክንያት ካሳውን መክፈል አልቻልኩም፡፡ ሪፖርተር፡- ቤተሰቦችዎ እዚህ ናቸው?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ሁለት ልጆቼና ባለቤቴ አሜሪካ ናቸው፡፡ ባለቤቴ በቅርብ እንድትመጣ ተነጋግረናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከቀድሞ የቅንጅት አመራር አባላት ጋር ትገናኛላችሁ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አብረን ነን፡፡ ባለፈው አንድ ጋዜጣ የተሳሳተ ነገር ጽፏል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ አሜሪካ ሆኖ የትጥቅ ትግሉን እንዲመራ እኔ ደግሞ እዚህ እንዳስተባብር ተልኬ እንደመጣሁ ጽፎ ነበር፡፡ ይኼ በፍፁም ሀሰት ነው፡፡ በትጥቅ ትግል አላምንም፡፡ ይቅርታ ተደርጎልን ስንወጣ በተመሳሳይ ተግባር ከተሰማራችሁ ይቅርታው ተሰርዞ ወህኒ ቤት ትገባላችሁ የሚል ጽሑፍ አለ፡፡ እኔን ወህኒ ቤት ለመዶል ተፈልጎ እንደሁ አላውቅም፡፡ ኦነግም ይሁን ኦብነግን አይቻቸውም አላውቅም፡፡ እነማን እንደሆኑም አላውቃቸውም፡፡ በእርግጥ ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር እንገናኝ ነበር፡፡ የቆየ ወዳጄ፣ ጓደኛዬ ነው፡፡ በቅንጅት ውስጥም አብረን እንንቀሳቀስ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ቅድም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሐዲዱ ስቷል ብለውኛል፡፡ ወደ ሐዲዱ እንዴት መመለስ ይቻላል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ወደ ሐዲዱ ለመመለስ በጎ ፈቃደኝነትን ይጠይቃል፡፡ የኢሕአዴግ በጎ ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ እኛ የሚፈለገውን ለመርዳት ዝግጁ ነን፡፡ ማንም ሊክደው የማይችል ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አለን፡፡ በልማቱም በዴሞክራሲውም ለማንቀሳቀስ ችሎታው አለን፡፡ በምርጫው የታየ ነው፡፡ በአንድ ቀን ከሁለት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለድጋፍ ሰልፍ ወጥቶ በሰላም ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡ አንድ ሞባይል ጠፍቶ መጨረሻ ላይ ባለቤቱ ተገኝቷል፡፡ ቅጠል አልተበጠሰም፡፡ እኛ የጠራናቸው እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ ነበሩ፡፡ ያ ሕዝብ ከእኛ ጋር ነው፡፡ አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን፡፡ ለጋራ አገራችን አብረን መሥራት ይኖርብናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከእሥር ቤት ከወጡ በኋላ ከመንግሥት (ከገዢው ፓርቲ) ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ያውቃሉ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በፍፁም ተገናኝቼ አላውቅም፡፡ የጠራንም የለም፡፡ እኛም አልጠየቅንም፡፡ የሚያገናኘንም ነገር የለም፡፡ ከወህኒ ቤት ስንወጣ ከሽማግሌዎች ቃል የተገባልን በእኛና በኢሕአዴግ መካከል ሁሉ አቀፍ የሆነ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ነበር፡፡ ያ ውይይት አልተደረገም፡፡ ፓርቲም የለንም፡፡ ውይይትም ልናደርግ አንችልም፡፡ ማንንም አንወክልም፡፡
ሪፖርተር፡- ከሽማግሌዎቹ ጋር አልተገናኛችሁም?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ከሽማግሌዎቹ ጋር ተገናኝተናል፡፡ ይህንን በሚመለከት ምን እንዳደረጉ አናውቅም፡፡ በቅንጅት ስም ታስረው በነበሩ ሰዎች ጉዳይ ከሽማግሌዎች ጋር በተደጋጋሚ ተገናኝተናል፡፡ ውይይቱ ወደፊት ፓርቲ ስናቋቁም ቢደረግ በጣም ፈቃደኞች ነን፡፡
ሪፖርተር፡- ከአዲሱ ፓርቲ ምስረታ ውጪ ያለው ጊዜዎትን በምን ያሳልፋሉ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ፓርቲውን ለማቋቋም ብዙ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ብዙ ስብሰባዎች ይደረጋሉ፡፡ የተቀረው ጊዜ በማንበብና በመፃፍ ነው የማሳልፈው፡፡
ሪፖርተር፡- መዝናናት አይወዱም?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- መዝናናት የማይወድ ማን አለ? ስፖርት እሠራለሁ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር እገናኛለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የመዘዋወር ተፅዕኖ አለብዎት?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ምንም መሰናክል የለም፡፡ |