| ቅንጅት ሁለት አባላቱን አሰናበተ |
|
|
| Wednesday, 23 April 2008 | |
|
ቅንጀት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በፓርቲው ውስጥ በስውር ተልዕኮ ሲንቀሳቀሱ ተገኙ ያላቸውን አንድ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና አንድ አባል ከፓርቲው ማገዱን አስታወቀ፡፡ ከታገዱት መካከል አቶ ግርማ አጋ የአቶ አየለ ጫሚሶ አመራርን በመቃወማቸው ምክንያት የፈጠራ ውንጀላ እንደቀረበባቸው ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ሚያዚያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ አቶ ግርማ አጋና አቶ ተስፋዬ አድማሴ ከፓርቲው አባልነት መታገዳቸውን ፓርቲው ትላንትና ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡ የፓርቲውን የውስጥ ሚስጢር ለሌላ አካል አሳልፈው ሰጥተዋል፣ በፓርቲው ውስጥ አሉባልታ አናፍሰዋል፣ የቅንጅትን ሰነዶችን በጥቅማ ጥቅም ሲሸጡ ተገኝተዋል እንዲሁም ፓርቲው ማሟያ ምርጫ ላይ ያደረገውን እንቅስቃሴ አደናቅፈዋል በማለት፤ ፓርቲው ግለሰቦቹን ወንጅሏል፡፡ የፓርቲው መግለጫ አቶ ግርማ አጋ በተለይ በአደራ ከአባላት የተላከ የፓርቲውን ገንዘብ ለግል ጥቅም አውለዋል ሲል ኮንኗል፡፡ በመግለጫው መሰረት ፓርቲው ባደረገው የአስቸኳይ ስብሰባ ሰርጎ ገብ ያላቸውን ሁለቱንም አባላት ከስራ አስፈፃሚነትና ከአባልነት ያገዳቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡ እገዳውም ለፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 45 ንዑስ አንቀፅ 45/1 መሰረት መሆኑን መግለጫው አትቷል፡፡ መግለጫው ሁለቱ ግለሰቦች ከሚያዚያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በቅንጅት ስም ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችሉ አስታውቋል፡፡ እገዳውን አስመልክቶ ለግለሰቦቹ በደብዳቤ እንደተገለፀላቸው የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ሳሳለሁልህ ከበደ ገልፀዋል፡፡ ከታገዱት አባላት መካከል አቶ ግርማ አጋ፤ በደብዳቤ የተገለፀላቸው ነገር አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡ አቶ ግርማ በፓርቲው ውስጥ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ማገልገላቸውንና የፓርቲው ህልውና በማቆየት በኩል ሰፊ ሚና መጫወታቸውን ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን ይላሉ ግርማ፣ “አቶ አየለ ጫሚሶ እንደ ሎተሪ ያገኙትን ፓርቲ የመምራት ብቃትም ችሎታም የላቸውም” ሲሉ የፕሬዚዳንቱን አመራር እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ ከመነሻውም የፓርቲውን ህልውና በማቆየት “በእስር ላይ ለሚገኙት የፓርቲው አመራር አካላት እናስረክባለን የሚል እንጂ አቶ አየለ ጫሚሶ ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት ይመራሉ የሚል አልነበረም” ብለዋል፡፡ ግርማ ከአቶ አየለ ጋር መዝለቅ እንደማይችሉ አስታውቀዋል፡፡ ይህንኑ በተመለከተ በስብሰባ ላይ ብዙ ጊዜ መግለፃቸውንና የፓርቲውን አመራር ስልጣን ለቀድሞ አመራር አካላት እንዲመልሱ በመጠየቃቸው በፓርቲው ጥቂት አባላት ውንጀላ እንደተመሰረተባቸው አብራርተዋል፡፡ “አቶ አየለ ጫሚሶና አቶ ሳሳሁልህ ከበደ እንዲሁም አንዳንድ ተከታታዮቻቸው የሚሰሩት ሥራ በሙሉ ፍፁም አፍራሽና የሚሰሩትን የማያውቁ ናቸው” ሲሉ ወንጅለዋል፡፡ አቶ ግርማ የፓርቲው አመራር አካላት በገንዘብ ፍላጎት ላይ ተመስርተው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ “አቶ አየለ በገንዘብና በሥልጣን ፍቅር የሚንቀሳቀሱ እንጂ ለዴሞክራሲ ግንባታ ወይም የቅንጅትን አላማ ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ አይደሉም” ሲሉ አቶ ግርማ ገልፀዋል፡፡ በማያያዝም “አቶ አየለ ምን አይነት ተልዕኮ እንዳላቸው ሊገባን አልቻለም” ብለዋል፡፡ ማድረግ የሚችል የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑን ጠቅሰው “እነሱ እኛን ለማባረር ብቃትም ሆነ ሞራል የላቸውም” ብለዋል፡፡ አስቸኳይ ስብሰባ የተባለው ውሸት መሆኑን የፓርቲው አባላትን በእማኝነት በመጥቀስ ገልፀዋል፡፡ አቶ ግርማ ከሟሟያ ምርጫ በኋላ በራሳቸው ፈቃድ ፓርቲውን ለመልቀቅ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከአቶ አየለ ጋር ትግል ማድረግ እንደሰለቻቸው ገልፀው፤ “አቶ አየለ እንደ ሎተሪ ያገኙትን የፓርቲ ስልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት የላቸውም” ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ አድማሴን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልሳካም፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |